በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

የሥነ ምግባር እሴቶች—ለተሻለ ሕይወት

የሥነ ምግባር እሴቶች—ለተሻለ ሕይወት

ክርስቲና ዓይኗን ማመን አልቻለችም! በጥቁር ፌስታል የተቀመጠ በጣም ብዙ ገንዘብ አግኝታለች፤ ያገኘችው ገንዘብ ከ20 ዓመት በላይ ሠርታ ከምታገኘው ደሞዝ የሚበልጥ ነው። ገንዘቡን የጣለው ማን እንደሆነ ታውቃለች። ታዲያ ምን ማድረግ ይኖርባታል? አንተ ብትሆን ኖሮ ምን ታደርግ ነበር? ለዚህ ጥያቄ የምትሰጠው መልስ ለሐቀኝነት ያለህን አመለካከትና ይህን የሥነ ምግባር እሴት ለመጠበቅ ያለህን ቁርጠኝነት የሚያንጸባርቅ ይሆናል።

እሴት ሲባል ምን ማለት ነው? ጥሩና አስፈላጊ እንደሆኑ አድርገን የምንመለከታቸው የሥነ ምግባር መመሪያዎች ወይም ደንቦች ማለት ነው። ከእነዚህ መካከል ይቅር ባይነት፣ ሐቀኝነት፣ የሌላውን ነፃነት ማክበር፣ ፍቅር፣ ለሕይወት አክብሮት ማሳየትና ራስን መግዛት ይገኙበታል። በመሆኑም የምንመራባቸው የሥነ ምግባር እሴቶች በባሕርያችን፣ ቅድሚያ በምንሰጣቸው ነገሮች፣ ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት እንዲሁም ለልጆቻችን በምናስተላልፋቸው የሥነ ምግባር መመሪያዎች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። እነዚህ እሴቶች በጣም አስፈላጊ ቢሆኑም ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን የሰዎች ሥነ ምግባር እያዘቀጠ መጥቷል።

የሥነ ምግባር እሴቶች እየጠፉ መጥተዋል

በ2008 በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ተመራማሪዎች ለሥነ ምግባር እሴቶች ያላቸውን አመለካከት ለማወቅ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶች ቃለ መጠይቅ አድርገውላቸው ነበር። ዴቪድ ብሩክስ በኒው ዮርክ ታይምስ ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “የእነዚህ ወጣቶች አስተሳሰብና አነጋገር ለሥነ ምግባር ያላቸው አመለካከት ምን ያህል የወረደ እንደሆነ ያሳያል፤ ይህ ደግሞ ልብ የሚሰብር ነው።” አብዛኞቹ አስገድዶ መድፈርና ነፍስ ግድያ መጥፎ እንደሆኑ ተሰምቷቸዋል፤ “ከእነዚህ የከፉ ድርጊቶች ውጭ ግን ሌላው ቀርቶ ሰክሮ እንደማሽከርከር፣ በትምህርት ቤት ውስጥ እንደማታለል ወይም ከጓደኛቸው ሌላ የፆታ  ግንኙነት እንደመፈጸም ስላሉ ጉዳዮች ሲያስቡ የሥነ ምግባር እሴቶች ትዝ አይሏቸውም።” አንዲት ወጣት “አንድ ነገር ትክክል ነው ወይስ አይደለም ብዬ ለማሰብ ያን ያህል አልሞክርም” ብላለች። ብዙዎች “ትክክል መስሎ ከተሰማህ አድርገው። ልብህ የሚልህን አዳምጥ” የሚል አመለካከት አላቸው። እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ጥበብ ነው?

የሰው ልብ ጥልቅ ፍቅርና ሐዘኔታ የማሳየት ችሎታ ቢኖረውም የዚያኑ ያህል ‘ተንኮለኛና አታላይም’ ሊሆን ይችላል። (ኤርምያስ 17፡9) የዓለም የሥነ ምግባር ገጽታ እየተለወጠ መምጣቱ ይህን አሳዛኝ እውነታ የሚያንጸባርቅ ነው። ይህ እንደሚሆን መጽሐፍ ቅዱስ ከረጅም ጊዜ በፊት እንደሚከተለው በማለት ትንቢት ተናግሯል፦ ‘በመጨረሻዎቹ ቀኖች ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብ የሚወዱ፣ ጉረኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ጨካኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጥሩ ነገር የማይወዱና አምላክን ከመውደድ ይልቅ ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ ይሆናሉ።’—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5

ይህን እውነታ መገንዘባችን የገዛ ልባችንን በጭፍን ከማመን ይልቅ እንድንጠረጥረው ሊያነሳሳን ይገባል! መጽሐፍ ቅዱስ “በራሱ የሚታመን ተላላ ነው” በማለት በግልጽ ይናገራል። (ምሳሌ 28:26) ልባችን በጥሩ ሁኔታ እንዲያገለግለን ከፈለግን ጠቃሚ በሆኑ የሥነ ምግባር እሴቶች መሠረት ልክ እንደ ኮምፓስ መስተካከል ይኖርበታል። እንዲህ ያሉ እሴቶችን ከየት ማግኘት እንችላለን? መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛና ግልጽ በመሆኑ ብዙዎች እነዚህን እሴቶች ለማግኘት ወደ አምላክ ቃል ዘወር ይላሉ።

ልንተማመንባቸው የምንችል የሥነ ምግባር እሴቶች!

የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር እሴቶች ለሰው ልጆች ተብለው የተዘጋጁ መሆናቸውን የሚያሳዩ ብዙ ማስረጃዎች አሉ። እስቲ ፍቅርን፣ ደግነትን፣ ልግስናንና ሐቀኝነትን እንደ ምሳሌ እንውሰድ።

ለሰዎች ፍቅር ማሳየት።

ኢንጂኒየሪንግ ሃፒነስ—ኤ ኒው አፕሮች ፎር ቢልዲንግ ኤ ጆይፉል ላይፍ የተባለው መጽሐፍ “መውደድን ከተማርክ ደስታ በርህን ያንኳኳል” ብሏል። በእርግጥም ሰዎች እንደመሆናችን ፍቅር ያስፈልገናል። ያለ ፍቅር እውነተኛ ደስታ ልናገኝ አንችልም።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ፍቅርን ልበሱ፤ ምክንያቱም ፍቅር ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ ነው።” (ቆላስይስ 3:14) ይኸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ “ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ” ብሏል።—1 ቆሮንቶስ 13:2

እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር ከፆታ ጋር የተያያዘ ወይም በስሜት ብቻ የሚመራ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ በመሠረታዊ ሥርዓት የሚመራ ነው። ችግር ውስጥ የወደቀን የማናውቀውን ሰው ብድር ይመልስልናል ብለን ተስፋ ሳናደርግ ግለሰቡን እንድንረዳው የሚገፋፋን የፍቅር ዓይነት ነው። አንደኛ ቆሮንቶስ 13:4-7 እንዲህ ይላል፦ “ፍቅር ታጋሽና ደግ ነው። ፍቅር አይቀናም፣ ጉራ አይነዛም፣ አይታበይም፣ ተገቢ ያልሆነ ምግባር አያሳይም፣ የራሱን ፍላጎት አያስቀድምም፣ አይበሳጭም። ፍቅር የበደል መዝገብ የለውም። ፍቅር በዓመፅ አይደሰትም፤ ከዚህ ይልቅ ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል። ሁሉን ችሎ ያልፋል፣ . . . ሁሉን ነገር በጽናት ይቋቋማል።”

በቤተሰብ መካከል እንዲህ ያለው ፍቅር ሲጠፋ ሁሉም የቤተሰቡ አባላት በተለይ ደግሞ ልጆች ይጎዳሉ። ሞኒካ የተባለች አንዲት ሴት በልጅነቷ አካላዊ፣ ስሜታዊና ፆታዊ በደል ተፈጽሞባት እንደነበረ ጽፋለች። “ያደግኩት ፍቅር ተነፍጌና ተስፋ ቢስ ሆኜ ነው” ብላለች። ከዚያም 15 ዓመት ሲሞላት የይሖዋ ምሥክሮች ከሆኑት አያቶቿ ጋር መኖር ጀመረች።

 ሞኒካ እንዲህ ብላለች፦ “ከአያቶቼ ጋር በኖርኩባቸው ሁለት ዓመታት ዓይን አፋር የነበርኩትን ልጅ ተጫዋች፣ አፍቃሪና ለሌሎች አሳቢ እንድሆን አስተማሩኝ። በሰዎች ዘንድ ክብር ያለኝ ወጣት እንድሆን ረዱኝ።” አሁን ጥሩ ትዳር ያላት ሞኒካ ከባለቤቷና ከሦስት ልጆቿ ጋር በመሆን የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በማካፈል ለሰዎች ፍቅሯን ታሳያለች።

የፍቅር መሠሪ ጠላት ፍቅረ ንዋይ ነው፤ ፍቅረ ንዋይ ሲባል ለቁሳዊ ብልጽግናና ደስታ ከሁሉ የበለጠ ዋጋ መስጠት ማለት ነው። ዓለማዊ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ግን ከመሠረታዊ ነገሮች ያለፈ ሀብት ማካበት ደስታ አያመጣም። እንዲያውም ለቁሳዊ ነገሮች ትልቅ ቦታ የሚሰጡ ሰዎች ደስታ በሚያሳጣቸው ነገር ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ ነው ሊባል ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስም ይህ እውነት እንደሆነ ያረጋግጣል፤ መክብብ 5:10 “ገንዘብን የሚወድ፣ ገንዘብ አይበቃውም፤ ብልጽግናም የሚወድ፣ በትርፉ አይረካም፤ ይህም ከንቱ ነው” ይላል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “አኗኗራችሁ ከገንዘብ ፍቅር ነፃ ይሁን” ይላል።—ዕብራውያን 13:5

ደግነትና ልግስና።

በዩናይትድ ስቴትስ፣ በርክሌይ የሚገኘው ዘ ግሬተር ጉድ ሳይንስ ሴንተር አት ዩኒቨርሲቲ ኦቭ ካሊፎርኒያ የተባለ ተቋም ባወጣው ጽሑፍ ላይ “ወደ አንድ ሱቅ ገብተህ የዕድሜ ልክ ደስታ መሸመት ብትችል ኖሮ ጥሩ አይሆንም ነበር?” በማለት ጠይቋል። አክሎም “ይህ ሐሳብ ሊሆን የማይችል ነገር ቢመስልም የምትገዛው ነገር ለሌላ ሰው እስከሆነ ድረስ ግን በእርግጥ የሚሆን ነገር ነው” ይላል። ዋናው ነጥብ ምንድን ነው? መስጠት ከመቀበል የበለጠ ደስተኛ ያደርገናል።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል።”—የሐዋርያት ሥራ 20:35

ብዙ ጊዜ ከሁሉ የተሻለውና ከሁሉም ይልቅ የሚክሰው ስጦታ ራስን ማለትም ጊዜንና ጉልበትን መስጠት ነው። ለምሳሌ ካረን የተባለች አንዲት ሴት መኪና ውስጥ ሁለት ሴቶች ከእናታቸው ጋር ተቀምጠው አየች፤ የመኪናው ኮፈን ተከፍቶ ነበር። እናትየውና አንደኛዋ ሴት አውሮፕላን የሚሳፈሩበት ሰዓት ቢደርስባቸውም መኪናቸው አልነሳ ብሏቸዋል፤ የጠሩትም ታክሲ ዘግይቶባቸዋል። ወደ አውሮፕላን ማረፊያው ለመሄድ 45 ደቂቃ የሚወስድ ቢሆንም ካረን ልታደርሳቸው እንደምትችል ነገረቻቸው። እነሱም በሐሳቡ ተስማሙ። ካረን ደርሳ ስትመለስ ሌላኛዋ ሴት አሁንም መኪናው ውስጥ ተቀምጣ አየቻት።

በዚህ ጊዜ ይህች ሴት “ባለቤቴ እየመጣ ነው” አለች።

ካረንም “አይ እንደዚያ ከሆነ ጥሩ ነው። እኔም በመንግሥት አዳራሻችን ማለቴ ቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ያለውን አትክልት ልንከባከብ መሄዴ ነው” ስትል መለሰችላት።

ሴቲቱም “የይሖዋ ምሥክር ነሽ እንዴ?” አለቻት።

ካረን “አዎን” በማለት ከመለሰችላት በኋላ ትንሽ ተጨዋወቱ።

ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ካረን አንድ ፖስታ ደረሳት። ደብዳቤው በከፊል እንዲህ ይላል፦ “እኔና እናቴ ያደረግሽልንን አስደናቂ ነገር ዛሬም አልረሳነውም። ዕድሜ ላንቺ፣ አውሮፕላኑ ሳያመልጠን መድረስ ችለናል! እህቴ የይሖዋ ምሥክር እንደሆንሽ ስትነግረን ምክንያቱ ገባን። እናቴ የይሖዋ ምሥክር ናት፤ እኔም ስለቀዘቀዝኩ ነው እንጂ የይሖዋ ምሥክር ነኝ። በቅርቡ ግን አቋሜን ለማስተካከል ቆርጫለሁ!” ካረን ሁለት የእምነት ባልንጀሮቿን መርዳት በመቻሏ እጅግ ተደሰተች። “በደስታ አለቀስኩ” በማለት ተናግራለች።

ቻርልስ ድ ዎርነር የተባሉ ጸሐፊ እንዲህ ብለዋል፦ “ማንም ሰው ሌላውን ከልቡ ሲረዳ ራሱንም የሚረዳ መሆኑ፣ ይህ በሕይወታችን ውስጥ ከምንካስባቸው አስደናቂ  መንገዶች አንዱ ነው።” ይህ ሊሆን የቻለው አምላክ የሰው ልጆችን የፈጠረው ራስ ወዳዶች እንዲሆኑ ሳይሆን የእሱን ውድ ባሕርያት እንዲያንጸባርቁ አድርጎ በመሆኑ ነው።—ዘፍጥረት 1:27

ሐቀኝነት።

ይህ የሥነ ምግባር እሴት በማንኛውም የሠለጠነ ኅብረተሰብ ውስጥ አስፈላጊ ነገር ነው። ሐቀኛ አለመሆን ፍርሃትን፣ አለመተማመንንና ማኅበራዊ ዝቅጠትን ያስከትላል።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? መዝሙራዊው እግዚአብሔር ሆይ፤ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል?” በማለት ከጠየቀ በኋላ “አካሄዱ ንጹሕ የሆነ፣ . . . ከልቡ እውነትን የሚናገር” በማለት መልሱን ተናግሯል። (መዝሙር 15:1, 2) አዎ፣ በሁሉም መንገድ ሐቀኛ መሆን እስካሁን እንደተመለከትናቸው ሌሎች የሥነ ምግባር እሴቶች ሁሉ ሰዎች ሊኖሯቸው ከሚገቡ ባሕርያት አንዱ ነው። ይህ የሥነ ምግባር እሴት እንደሁኔታው የሚለዋወጥ ወይም የሚያዋጣ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ተግባራዊ የሚደረግ አይደለም።

ገንዘብ የያዘ ቦርሳ አግኝታ የነበረችውን ክርስቲናን እስቲ እንመልከት። ፍላጎቷ አምላክን ማስደሰት እንጂ ሀብታም መሆን አልነበረም። በመሆኑም በጭንቀት የተዋጠው የገንዘቡ ባለቤት ተመልሶ ሲመጣ ገንዘቡ እንደተገኘ ነገረችው። እሱም በሐቀኝነቷ በጣም ተደነቀ። አሠሪዋም በጣም በመደነቅ በኋላ ላይ፣ ከፍተኛ ታማኝነት ወደሚጠይቀው የመጋዘን ኃላፊነት በማዘዋወር እድገት እንድታገኝ አደረገ። “ሕይወትን የሚወድና መልካም ቀኖችን ማየት የሚፈልግ ሰው . . . ከንፈሮቹንም የማታለያ ቃላት ከመናገር ይከልክል” የሚለው በ1 ጴጥሮስ 3:10 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ምንኛ እውነት ነው!

‘በደጋግ ሰዎች ጐዳና ሂድ’

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት የሥነ ምግባር እሴቶች ፈጣሪያችን ለእኛ ያለውን ጥልቅ ፍቅር የሚያንጸባርቁ ናቸው፤ ምክንያቱም እነዚህ እሴቶች ‘በደጋግ ሰዎች ጎዳና እንድንሄድ’ ያስችሉናል። (ምሳሌ 2:20፤ ኢሳይያስ 48:17, 18) ይህን መመሪያ ስንከተል እኛም በተራችን ለአምላክ ያለንን ፍቅር እናሳያለን፤ ይህ ደግሞ ብዙ በረከት ያስገኝልናል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔርን ደጅ ጥና፤ መንገዱንም ጠብቅ፤ ምድሪቱን ትወርስ ዘንድ ከፍ ከፍ ያደርግሃል፤ ክፉዎችም ሲጠፉ ታያለህ” የሚል ተስፋ ይሰጠናል።—መዝሙር 37:34

አዎ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን መሥፈርቶች የሚከተሉ ሰዎች በጣም ግሩም የሆነ የወደፊት ተስፋ ይኸውም ከክፋት በጸዳች ሰላማዊ ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር በረከት ይጠብቃቸዋል። በእርግጥም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን የሥነ ምግባር እሴቶች በደንብ ልንመረምራቸው ይገባል።