ቃለ ምልልስ | ሃንስ ክርስቲያን ኮትላር
የባዮቴክኖሎጂ ባለሞያ ስለሚያምኑበት ነገር ምን ይላሉ?
ዶክተር ሃንስ ክርስቲያን ኮትለር፣ በሳይንሳዊ ምርምር የመጀመሪያ ሥራቸውን ያካሄዱት በ1978 በኖርዌጅያን ሬድየም ሆስፒታል ነው፤ በዚያም በካንሰርና በሰው ልጆች በሽታ የመከላከል ሥርዓት ላይ ጥናት አድርገዋል። በዚያ ወቅት፣ ሕይወት ስለተገኘበት መንገድ የማወቅ ፍላጎት አደረባቸው። ንቁ! መጽሔት ስለ ምርምር ሥራቸውና ስለ እምነታቸው አነጋግሯቸዋል።
ስለ ሕይወት አመጣጥና ትርጉም የማወቅ ፍላጎት እንዲያድርብዎት ያደረገው ምንድን ነው?
አባቴ ካቶሊክ ሲሆን እናቴ ደግሞ ፕሮቴስታንት ነበረች። ይሁን እንጂ ለሃይማኖት ያን ያህል ቦታ አይሰጡም ነበር። እኔ ግን በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ እያለሁ የሕይወት ትርጉም ምን እንደሆነ የማወቅ ፍላጎት ስለነበረኝ ስለ ቡድሂዝም፣ ሂንዱይዝምና እስልምና የተጻፉ መጻሕፍትን አነበብኩ። አምላክ እውነቱን እንዲገልጽልኝ የጸለይኩበት ጊዜም ነበር።
በ1970ዎቹ ዓመታት የሞለኪውላር ባዮሎጂ መስክ አስደናቂ እድገቶችን አሳይቶ ስለነበር በዚህ መስክ የሚደረገው ጥናት ሕይወት እንዴት እንደተገኘ ለማወቅ ያስችል እንደሆነ ማሰብ ጀመርኩ። ሕይወት ባላቸው ሴሎች ውስጥ ያለው አሠራር በጣም ስላስደነቀኝ ስለ ባዮቴክኖሎጂ ለመማር መረጥኩ። አብዛኞቹ አስተማሪዎቼ ሕይወት ያላቸው ነገሮች የተገኙት በዝግመተ ለውጥ እንደሆነ ይናገሩ ነበር፤ እኔም ይህን ሐሳብ ተቀበልኩ።
ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የማወቅ ፍላጎት ያደረብዎት ለምንድን ነው?
በአንድ ወቅት ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ቤታችን መጥተው ነበር። ያነጋገሩኝ ደስ በሚል መንገድ ቢሆንም ‘አልፈልግም’ በማለት አመናጨኳቸው። ባለቤቴ ከውስጥ ሆና ትሰማ ስለነበር “ሃንስ፣ ያደረግኸው ነገር ተገቢ አይደለም” አለችኝ። አክላም “የሕይወት ትርጉም ምን እንደሆነ ለማወቅ እንደምትፈልግ ትናገር ነበር” አለች። ባለቤቴ ያለችው ነገር ትክክል እንደሆነ ስለማውቅ ኀፍረት ተሰማኝ። በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮቹን ሮጬ ደረስኩባቸው። ከዚያም ከእነሱ ጋር ስወያይ መጽሐፍ ቅዱስ ከሳይንስ ጋር ይስማማ እንደሆነ ማወቅ እንደምፈልግ ገለጽኩላቸው።
ታዲያ ምን መልስ አገኙ?
በአጽናፈ ዓለም ውስጥ የሚታየው ታላቅ ኃይል ምንጭ ማን እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳዩኝ። የሚከተለውን ጥቅስ አነበቡልኝ፦ “ዐይናችሁን አንሡ፤ ወደ ሰማይ ተመልከቱ፤ እነዚህን ሁሉ የፈጠረ ማን ነው? . . . ከኀይሉ ታላቅነትና ከችሎታው ብርታት የተነሣ፣ አንዳቸውም አይጠፉም።” * ይህን ጥቅስ ስመለከት በጣም ተገረምኩ። በተጨማሪም አጽናፈ ዓለም ይህን ያህል ሥርዓት ያለው ሊሆን የቻለው የማሰብ ችሎታ ያለው አካል ስለፈጠረው ነው ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ እንደሆነ ተሰማኝ።
ስለ ዝግመተ ለውጥ ያለዎት አመለካከት ተለውጧል?
የተለያዩ የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳቦች ጠንካራ ሳይንሳዊ ማረጋገጫ እንደሌላቸው እያደር ተገነዘብኩ። እንዲያውም እነዚህ ጽንሰ ሐሳቦች፣ በሕያዋን ፍጥረታት ውስጥ የሚገኙት አስደናቂ ንድፍ ያላቸው ነገሮች (ለምሳሌ የሰውነት በሽታ የመከላከያ ሥርዓት) የማሰብ ችሎታ ባለው አካል የተፈጠሩ እንዳልሆኑ ለማሳመን ሲባል የተፈለሰፉ ተረቶች ናቸው። ስለ ሰውነታችን በሽታ የመከላከል ኃይል ይበልጥ ባወቅሁ መጠን ምን ያህል ውስብስብና ውጤታማ እንደሆነ መገንዘብ ቻልኩ። ያደረግሁት ምርምር፣ ሕይወት ሊገኝ የሚችለው የማሰብ ችሎታ ካለው ፈጣሪ ብቻ እንደሆነ እንዳምን አድርጎኛል።
ያደረግሁት ምርምር፣ ሕይወት ሊገኝ የሚችለው የማሰብ ችሎታ ካለው ፈጣሪ ብቻ እንደሆነ እንዳምን አድርጎኛል
የተራቀቀ ንድፍ መኖሩን የሚያሳይ ማስረጃ መጥቀስ ይችላሉ?
የሰውነታችን በሽታ የመከላከል ሥርዓት፣ ባክቴሪያዎችንና ቫይረሶችን ጨምሮ ወደ ሰውነታችን የሚገቡ የተለያዩ በሽታ አምጪ ሕዋሳትን እንዲከላከሉልን ታስበው የተዘጋጁ የተለያዩ ዘዴዎችን ያካትታል። እነዚህ ዘዴዎች እርስ በርሳቸው በሚደጋገፉ ሁለት ሥርዓቶች ሊከፈሉ ይችላሉ። የመጀመሪያው ሥርዓት፣ በሽታ አምጪ ረቂቅ ተሕዋስያን ወደ ሰውነታችን በገቡ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ እነሱን ለማጥፋት እንቅስቃሴ እንዲጀመር ያደርጋል። ሁለተኛው ሥርዓት ደግሞ ጥቃቱን የሚጀምረው ከቀናት በኋላ ነው፤ ያም ቢሆን ዒላማውን እንደሚመታ ቀስት፣ ወራሪዎቹን ነጥሎ በማጥፋት ረገድ ይበልጥ ውጤታማ ነው። ይህ ሁለተኛው ሥርዓት ጥሩ የማስታወስ ችሎታ ስላለው አንድ ወራሪ ከበርካታ ዓመታት በኋላ እንኳ እንደገና ወደ ሰውነታችን ቢገባ ፈጣን እርምጃ እንዲወሰድበት ያደርጋል። መላው ሥርዓት በጣም በተቀላጠፈ ሁኔታ ስለሚሠራ አብዛኛውን ጊዜ በሽታ አምጪ ተሕዋስያን እንዳጠቁንና የሰውነታችን የመከላከል ሥርዓት ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዳስወገዳቸው እንኳ ላናውቅ እንችላለን። በተጨማሪም የሰውነታችን በሽታ የመከላከል ሥርዓት፣ ሰርገው የገቡ ባዕድ አካላትን በሰውነታችን ውስጥ ከሚገኙት በመቶዎች የሚቆጠሩ የሴል ዓይነቶች የሚለይበት መንገድ በጣም አስደናቂ ነው።
ረቂቅ ተሕዋስያን ወደ ሰውነታችን ሲገቡ ምን ይከሰታል?
ረቂቅ ተሕዋስያን ወደ ሰውነታችን የሚገቡት በትንፋሽና በምግብ አማካኝነት እንዲሁም በመራቢያ ብልቶቻችን ወይም በቆዳችን በኩል ነው። የሰውነታችን በሽታ የመከላከል ሥርዓት፣ ወራሪዎች ሰርገው መግባታቸውን ሲያውቅ እነሱን ለመከላከል የተዘጋጁ ፕሮቲኖች ተከታታይ የሆኑ ሥራዎችን እንዲጀምሩ ያደርጋል። በዚህ ሥርዓት ውስጥ የተካተተው እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ደግሞ ከእሱ ቀጥሎ ያለው እንቅስቃሴ ይበልጥ የተጠናከረ ጥቃት እንዲፈጽም ያደርገዋል። መላው ሂደት ልናስበው ከምንችለው በላይ ውስብስብ ነው።
ታዲያ የሳይንስ እውቀትዎ በአምላክ ላይ ያለዎትን እምነት አጠናክሮታል ማለት ይቻላል?
እንዴታ! በሰውነታችን ውስጥ የሚገኘው በሽታ የመከላከል ሥርዓት ያለው አቅምና ውስብስብ መሆኑ ጥበበኛና አፍቃሪ ፈጣሪ መኖሩን ይጠቁማል። በተጨማሪም ሳይንስ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለኝን እምነት አጠናክሮልኛል ማለት እችላለሁ። ለአብነት ያህል፣ ምሳሌ 17:22 “ደስተኛ ልብ ጥሩ መድኀኒት ነው” ይላል። ስሜታችን በሽታ በመከላከል አቅማችን ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ተመራማሪዎች ደርሰውበታል። ለምሳሌ፣ ውጥረት በሽታ የመከላከል አቅማችንን ያዳክማል።
ብዙዎቹ የሳይንስ ምሁራን በአምላክ አያምኑም። ይህ የሆነው ለምንድን ነው?
ምክንያቶቹ ይለያያሉ። አንዳንዶቹ ልክ እንደ እኔ የተማሩትን ነገር ምርምር ሳያደርጉበት ስለተቀበሉ ነው። ዝግመተ ለውጥ በጠንካራ ሳይንሳዊ መረጃ የተደገፈ ይመስላቸው ይሆናል። ሌሎቹ ደግሞ የሕይወት አመጣጥ ብዙም አያሳስባቸውም። ይህ በጣም ያሳዝናል። ስለዚህ ጉዳይ ይበልጥ ለማወቅ ጥረት ማድረግ ያለባቸው ይመስለኛል።
የይሖዋ ምሥክር የሆኑት ለምንድን ነው?
የይሖዋ ምሥክሮች እንግዳ ተቀባይ መሆናቸው እንዲሁም ፈጣሪ ወደፊት የተሻለ ጊዜ እንደሚያመጣ በሰጠው ተስፋ ላይ ያላቸው እምነት ማረከኝ። * ይህ እምነታቸው የተመሠረተው በአፈ ታሪክ ወይም በግምታዊ አስተሳሰብ ላይ ሳይሆን በምርምርና በአሳማኝ ማስረጃ ላይ ነው። *