የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ
ጥሩ ጓደኛ የሚባለው ምን ዓይነት ሰው ነው?
ታኅሣሥ 25, 2010 በብሪታንያ የምትኖር አንዲት የ42 ዓመት ሴት ራሷን እንደምታጠፋ የሚገልጽ መልእክት ታዋቂ በሆነ አንድ ማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ አወጣች። መልእክቷ የድረሱልኝ ጥሪ ይመስል ነበር። ሴትየዋ በማኅበራዊ ድረ ገጹ ላይ ከአንድ ሺህ የሚበልጡ “ጓደኞች” ቢኖሯትም ሊረዳት የመጣ አንድም ሰው አልነበረም። ከአንድ ቀን በኋላ ፖሊሶች ቤቷ ሲሄዱ ሞታ አገኟት። ይህች ሴት የሞተችው ከመጠን ያለፈ መድኃኒት በመውሰዷ ነበር።
በዛሬው ጊዜ ዘመናዊ የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ በመስፋፋቱ በማኅበራዊ ድረ ገጾች አማካኝነት በመቶዎች እንዲያውም በሺዎች የሚቆጠሩ “ጓደኞች” ማፍራት እንችላለን፤ ይህን ለማድረግ የሚጠይቅብን ነገር ቢኖር የሰዎቹን ስም በጓደኛ ዝርዝር ውስጥ ማስገባት ብቻ ነው። ከእነዚህ ሰዎች መካከል ከአንዱ ጋር ያለንን “ጓደኝነት” ማቋረጥ ከፈለግን የሚጠይቅብን ነገር ቢኖር የግለሰቡን ስም ከዝርዝራችን ውስጥ መሰረዝ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ በብሪታንያ ትኖር በነበረችው ሴት ላይ የደረሰው አሳዛኝ ሁኔታ አንድን እውነታ በግልጽ ይጠቁማል፤ አሁንም ብዙ ሰዎች እውነተኛ ጓደኛ ማግኘት አልቻሉም። እንዲያውም አንድ የቅርብ ጊዜ ጥናት እንዳመለከተው ማኅበራዊ ግንኙነታችን እየሰፋ ቢሄድም የእውነተኛ ጓደኞቻችን ቁጥር በእጅጉ ቀንሷል።
እንደ አብዛኞቹ ሰዎች ሁሉ አንተም ጥሩ ጓደኞች አስፈላጊ መሆናቸውን እንደምትስማማ የታወቀ ነው። በተጨማሪም ጥሩ ጓደኝነት መመሥረት በኮምፒውተር ወይም በዘመናዊ ስልክ ላይ የተወሰኑ ቁልፎችን ከመጫን የበለጠ ነገር ማድረግ እንደሚጠይቅ ሳትገነዘብ አትቀርም። ከአንድ ጓደኛህ የምትጠብቀው ነገር ምንድን ነው? አንተስ ጥሩ ጓደኛ ልትሆን የምትችለው እንዴት ነው? ዘላቂ ጓደኝነት ለመመሥረት የሚያስፈልገውስ ምንድን ነው?
እስቲ የሚከተሉትን አራት ጠቃሚ መመሪያዎች ተመልከት፤ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ጠቃሚ ምክር ሰዎች ለጓደኝነት የሚመርጡህ ዓይነት ሰው እንድትሆን የሚረዳህ እንዴት እንደሆነ ልብ በል።
1. ለሰዎች ልባዊ አሳቢነት አሳይ።
እውነተኛ ጓደኝነት ራስን ለሌላው መስጠትን ይጠይቃል። በሌላ አባባል አንድ ጥሩ ጓደኛ ምንጊዜም ከጎንህ መሆን እንዳለበት ይሰማዋል፤ እንዲሁም ከልቡ ያስብልሃል። እርግጥ እንዲህ ያለ ስሜት ሊኖራቸው የሚገባው ሁለቱም ወገኖች ናቸው፤ እንዲሁም ጓደኝነቱ እንዲጠነክር ሁለቱም ጥረት ማድረግና መሥዋዕትነት መክፈል ያስፈልጋቸዋል። ይሁን እንጂ ውጤቱ የሚያስቆጭ አይደለም። ‘ራሴን፣ ጊዜዬንና ንብረቴን ለጓደኛዬ ለመስጠት ፈቃደኛ ነኝ?’ በማለት ራስህን ጠይቅ። ጥሩ ጓደኛ እንዲኖርህ ከፈለግህ አንተ ራስህ በመጀመሪያ ጥሩ ጓደኛ መሆን እንዳለብህ አስታውስ።
ሰዎች ከጓደኞቻቸው ምን ይጠብቃሉ?
ኢሬይን፦ “ጓደኝነትን ጠብቆ ማቆየት እንደ ውብ የአትክልት ስፍራ ብዙ ጊዜና እንክብካቤ ይጠይቃል። አንተ ራስህ ቅድሚያውን ወስደህ ጥሩ ጓደኛ ሁን። ደግነት ለማሳየትና ለሌሎች ትኩረት ለመስጠት ጥረት አድርግ። እንዲሁም ጓደኛህ ሲፈልግህ ጊዜህን መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ ሁን።”
ሉዊስ አልፎንሶ፦ “በዛሬው ጊዜ ያለው ማኅበረሰብ ለሌሎች ከማሰብ ይልቅ ‘ለእኔ ብቻ’ የሚለውን መንፈስ ያበረታታል። በመሆኑም አንድ ሰው ምንም ነገር ሳይጠብቅ አሳቢነት ማሳየቱ ትልቅ ነገር ነው።”
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
“ልክ ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ እንደምትፈልጉት ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉላቸው። ሰጪዎች ሁኑ፤ ሰዎችም ይሰጧችኋል።” (ሉቃስ 6:31, 38) እዚህ ጥቅስ ላይ ኢየሱስ፣ የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግንና ለጋስነትን እያበረታታ ነው። እንዲህ ያለው ልግስና ወዳጅነትን ያጠናክራል። ምንም ዓይነት ምላሽ ሳትጠብቅ ጓደኞችህን የምትረዳ ከሆነ እነሱም ወደ አንተ ይበልጥ ለመቅረብ መፈለጋቸው አይቀርም።
2. የሐሳብ ልውውጥ የማድረግ ችሎታ አዳብር
ዘወትር የሐሳብ ልውውጥ የማይደረግ ከሆነ እውነተኛ ጓደኝነት ሊጠናከር አይችልም። ስለዚህ የሁለታችሁንም ትኩረት የሚስቡ ጉዳዮችን አንስታችሁ ተጨዋወቱ። ጓደኛህ የሚናገረውን አዳምጥ፤ አመለካከቱንም አክብርለት። አጋጣሚውን በምታገኝበት ጊዜ ሁሉ አመስግነው እንዲሁም አበረታታው። አንዳንድ ጊዜ ለጓደኛህ ምክር አልፎ ተርፎም እርማት መስጠት ሊያስፈልግህ ይችላል፤ ይህ ደግሞ ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። ያም ቢሆን ለጓደኛህ ታማኝ ከሆንክ ከባድ ስህተት በሚሠራበት ወቅት ስህተቱን ለመንገርና በዘዴ ምክር ለመስጠት የሚያስችል ድፍረት ይኖርሃል።
ሰዎች ከጓደኞቻቸው ምን ይጠብቃሉ?
ህዋን፦ “እውነተኛ ጓደኛ አመለካከቱን ለመግለጽ ነፃነት ሊሰማው ይገባል፤ በሌላ በኩል ደግሞ በተናገረው ነገር ባትስማማ እንኳ መበሳጨት የለበትም።”
ዩነስ፦ “በተለይ ችግር በሚያጋጥመኝ ጊዜ ከጎኔ ለሚሆኑና ለሚያዳምጡኝ ጓደኞች ትልቅ ቦታ እሰጣለሁ።”
ሲልቪና፦ “እውነተኛ ጓደኞች እንደሚያስከፋህ ቢያውቁም እውነቱን ከመናገር ወደኋላ አይሉም፤ ምክንያቱም ስለ አንተ ከልባቸው ያስባሉ።”
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
“ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየና ለቁጣ የዘገየ መሆን አለበት።” (ያዕቆብ 1:19) ሰዎች ጓደኛቸው ጆሮ ሰጥቶ እንዲያዳምጣቸው ይፈልጋሉ። ይሁን እንጂ ውይይቱን ከተቆጣጠርነው ‘ከእናንተ አመለካከት ይልቅ የእኔ አመለካከት ይበልጣል’ የሚል መልእክት ማስተላለፋችን ነው። ስለዚህ ጓደኛህ የውስጡን አውጥቶ ሲነግርህ እንዲሁም ያሳሰበውን ነገር ሲያጫውትህ ከልብህ አዳምጠው። የተሰማውን ነገር በሐቀኝነት በመናገሩ ቅር አትሰኝ። ምሳሌ 27:6 “የወዳጅ ማቍሰል ይታመናል” ይላል።
3. ከጓደኛህ በምትጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ ሁን
አንድን ሰው እየቀረብከው ስትሄድ ጉድለቶቹን ማስተዋልህ አይቀርም። እኛ ፍጹማን እንዳልሆንን ሁሉ ጓደኞቻችንም ፍጹማን አይደሉም። ስለዚህ ከጓደኞቻችን ፍጽምና መጠበቅም የለብንም። ከዚህ ይልቅ ጥሩ ጎናቸውን ማድነቅና ስህተቶቻቸውን ችለን ማለፍ ይገባናል።
ሰዎች ከጓደኞቻቸው ምን ይጠብቃሉ?
ሳሙኤል፦ “ብዙ ጊዜ ከራሳችን ከምንጠብቀው የበለጠ ነገር ከሌሎች እንጠብቃለን። እኛ እንደምንሳሳትና ይቅርታ እንደሚያስፈልገን ከተገነዘብን ግን ሌሎችን ይቅር ለማለት ይቀለናል።”
ዳንኤል፦ “ጓደኞችህ ሊሳሳቱ እንደሚችሉ አምነህ ተቀበል። ችግር በሚፈጠርበት ወቅት ችግሩን ቶሎ ብለን መፍታታችንና የተፈጠረውን ሁኔታ መርሳታችን ጥሩ ይሆናል።”
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
“ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንሰናከላለን። በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር ይህ ሰው መላ ሰውነቱን ጭምር መቆጣጠር የሚችል ፍጹም ሰው ነው።” (ያዕቆብ 3:2) ይህን ግልጽ እውነታ መገንዘባችን ጓደኞቻችንን ለመረዳት ያስችለናል። ይህን ካደረግን ደግሞ ሊያበሳጩን የሚችሉ ቀላል ጉድለቶችንና ስህተቶችን ችላ ብለን ማለፍ እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖረው እርስ በርስ መቻቻላችሁንና እርስ በርስ በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ። . . . ይሁንና በእነዚህ ነገሮች ሁሉ ላይ ፍቅርን ልበሱ፤ ምክንያቱም ፍቅር ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ ነው።”—ቆላስይስ 3:13, 14
4. ከተለያዩ ዓይነት ሰዎች ጋር ጓደኝነት መሥርቱ
ጓደኛ በምናደርጋቸው ሰዎች ረገድ መራጮች መሆን እንዳለብን የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ የጓደኛ ምርጫችን በዕድሜ ወይም በአስተዳደግ መወሰን የለበትም። የተለያየ ዕድሜ፣ ባሕልና ዜግነት ካላቸው ሰዎች ጋር ጓደኝነት መመሥረታችን ሕይወታችንን አስደሳች ያደርገዋል።
ሰዎች ከጓደኞቻቸው ምን ይጠብቃሉ?
ዩናይ፦ “ከአንተ ጋር ተመሳሳይ ዕድሜና ፍላጎት ካላቸው ሰዎች ጋር ብቻ መወዳጀት ሁልጊዜ ተመሳሳይ ቀለም ያለው ልብስ ከመልበስ ጋር ይመሳሰላል። ይህን ቀለም ምንም ያህል ብትወደው የሆነ ጊዜ ላይ መሰልቸትህ አይቀርም።”
ፉንኬ፦ “ከተለያዩ ዓይነት ሰዎች ጋር ጓደኝነት መመሥረቴ በሳል ሰው እንድሆን ረድቶኛል። የተለያየ ዕድሜና አስተዳደግ ካላቸው ሰዎች ጋር ተስማምቶ መኖር የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ተምሬያለሁ፤ ይህ ደግሞ ይበልጥ ተግባቢ እንድሆንና ከሰዎች ጋር በቀላሉ እንድላመድ አስችሎኛል። ጓደኞቼም ይህን ጠባዬን ይወዱልኛል።”
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
“ስለዚህ ልጆችን እንደማናግር ሆኜ አናግራችኋለሁ፤ እናንተም በአጸፋው ልባችሁን ወለል አድርጋችሁ ክፈቱ።” (2 ቆሮንቶስ 6:13) መጽሐፍ ቅዱስ ከሁሉም ዓይነት ሰዎች ጋር ጓደኝነት እንድንመሠርት ያበረታታናል። እንዲህ ማድረግህ ሕይወትህን አስደሳች የሚያደርገው ከመሆኑም ሌላ በሌሎች ዘንድ ተወዳጅ እንድትሆን ያስችልሃል።