ለቤተሰብ | ትዳር
ከአማቶች ጋር ተስማምቶ መኖር
ተፈታታኙ ነገር
“አስቸጋሪ ሁኔታ አጋጥሞን በነበረበት ወቅት ባለቤቴ ስለ ጉዳዩ ለወላጆቿ ነገረቻቸው። ከዚያም አባቷ ደውሎ ጉዳዩን አስመልክቶ ምክር ሰጠኝ። ነገሩ አላስደሰተኝም።”—ጄምስ *
“የባለቤቴ እናት ብዙ ጊዜ ‘ልጄ በጣም ይናፍቀኛል’ ትላለች። ምን ያህል ይቀራረቡ እንደነበረም ትናገራለች፤ በዚህ ጊዜ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማኛል፤ ምክንያቱም እሷን ለዚህ ችግር የዳረጋት እኔ እሱን ማግባቴ እንደሆነ አስባለሁ!”—ናታሻ
ታዲያ ከአማቶቻችሁ ጋር ያላችሁ ግንኙነት በትዳራችሁ ውስጥ ችግር የሚፈጥር ነገር እንዳይሆን ማድረግ ትችላላችሁ?
ማወቅ የሚኖርባችሁ ነገር
ጋብቻ ራሱን የቻለ አንድ ቤተሰብ እንዲፈጠር ያደርጋል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ያገባ ሰው “ከአባትና ከእናቱ ይለያል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል” ይላል። ለሚስትም ቢሆን ሁኔታው ከዚህ የተለየ አይደለም። ትዳር ሲመሠርቱ ሁለቱም “አንድ ሥጋ” እንደሚሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ይህም አንድ አዲስ ቤተሰብ እንዲፈጠር ያደርጋል።—ማቴዎስ 19:5
ከወላጆቻችሁ ይልቅ ለትዳር ጓደኛችሁ ቅድሚያ መስጠት አለባችሁ። ጆን ጎትመን የተባሉ የጋብቻ አማካሪ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “በጋብቻ ውስጥ ሊሠራባቸው ከሚገቡ መሠረታዊ ነገሮች መካከል አንዱ በባልና በሚስት መካከል ‘እኛ’ የሚል ስሜት መፍጠር ነው። . . . ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር የአንድነት ስሜት ለመፍጠር ወይም ይህን ስሜት ለማደስ ከሌሎች የቅርብ ቤተሰባችሁ አባላት ጋር መለየት ሊያስፈልጋችሁ ይችላል።” *
አንዳንድ ወላጆች ማስተካከያ ማድረግ አስቸጋሪ ሊሆንባቸው ይችላል። አንድ ወጣት ባለትዳር እንዲህ ብሏል፦ “ከመጋባታችን በፊት ባለቤቴ ሁልጊዜ ለወላጆቿ ፍላጎት ቅድሚያ ትሰጥ ነበር። ከተጋባን በኋላ እናቷ፣ ባለቤቴ ከእነሱ የበለጠ ቅድሚያ የምትሰጠው ሰው እንዳለ አስተዋለች። ይህን መቀበል ግን ቀላል አልሆነላትም።”
አንዳንድ አዲስ ተጋቢዎችም አስቸጋሪ ሊሆንባቸው ይችላል። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ጄምስ እንዲህ ብሏል፦ “አማቶችህ መርጠህ እንዳገኘሃቸው ጓደኞች አይደሉም። በአንድ ወቅት አንድ ሰው እንደተናገረው ‘ወደድክም ጠላህም ሁለት አዳዲስ ጓደኞች ታገኛለህ።’ በጣም ቢያበሳጩህም እንኳ ቤተሰቦችህ ናቸው።”
ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
ከአማቶች ጋር ባላችሁ ግንኙነት የተነሳ በትዳራችሁ ውስጥ አለመግባባት ተፈጥሮ ከሆነ ጉዳዩን ተባብራችሁ ለመፍታት ጥረት አድርጉ። “ሰላምን ፈልጋት፤ ተከተላትም” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተግባራዊ አድርጉ።—መዝሙር 34:14
ይህን ለማድረግ እንዲረዳችሁ የሚከተሉትን ሁኔታዎች አስቡ። እነዚህ ሁኔታዎች የቀረቡት ከባል ወይም ከሚስት አንጻር ነው። ይሁን እንጂ ችግሮቹ በባልም ሆነ በሚስት ላይ ሊያጋጥሙ ይችላሉ፤ እንዲሁም የቀረቡት መመሪያዎች በአማቶች ምክንያት የሚነሱ ሌሎች በርካታ ችግሮችን ለመፍታት ይረዳሉ።
ባለቤትህ ከእናቷ ጋር ይበልጥ ብትግባቡ ደስ እንደሚላት ነገረችህ። አንተ ግን ከእናቷ ጋር መግባባት ከባድ ይሆንብሃል።
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ ችግሩን ከባለቤትህ ጋር ተወያይ፤ በአንዳንድ ጉዳዮች ረገድ እሷ የምትልህን ለማድረግ ፈቃደኛ ሁን። ዋናው ጉዳይ አንተ ለአማትህ ያለህ ስሜት ሳይሆን ልትወዳት ቃል ለገባህላት ለትዳር ጓደኛህ ያለህ ስሜት ነው። ከባለቤትህ ጋር በምትወያዩበት ወቅት ከእናቷ ጋር ያለህን ግንኙነት ማሻሻል የምትችልባቸውን አንድ ወይም ሁለት አቅጣጫዎች ለማወቅ ሞክር፤ ከዚያም በእነዚህ አቅጣጫዎች ማሻሻያ አድርግ። ባለቤትህ አንተ የምታደርገውን ጥረት ስትመለከት ለአንተ ያላት አክብሮት ይጨምራል።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ 1 ቆሮንቶስ 10:24
ባለቤትሽ ከእሱ ይልቅ ወላጆችሽን ለማስደሰት ይበልጥ ጥረት እንደምታደርጊ ነገረሽ።
እንዲህ ለማድረግ ሞክሪ፦ ሁኔታውን ከባለቤትሽ ጋር ተወያዪ፤ እንዲሁም ጉዳዩን በእሱ ቦታ ሆነሽ ለመመልከት ሞክሪ። እርግጥ፣ ለወላጆችሽ የሚገባቸውን አክብሮት ስላሳየሽ ብቻ ባለቤትሽ ስጋት ሊሰማው አይገባም። (ምሳሌ 23:22) ያም ቢሆን በሕይወትሽ ውስጥ ቅድሚያ የምትሰጪው ከወላጆችሽ ይበልጥ ለእሱ እንደሆነ በቃልም ሆነ በድርጊት ልታረጋግጪለት ይገባል። ባለቤትሽ ስለዚህ ጉዳይ እርግጠኛ ከሆነ የአንቺን ትኩረት ለማግኘት ከወላጆችሽ ጋር መፎካከር እንደሚኖርበት አይሰማውም።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ኤፌሶን 5:33
ባለቤትህ ከአንተ ይልቅ ወላጆቿን ምክር ትጠይቃለች።
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ ከባለቤትህ ጋር ስለ ጉዳዩ በመነጋገር የቱ ጋ ገደብ ማበጀት እንዳለባችሁ ስምምነት ላይ ድረሱ። ምክንያታዊ ለመሆን ጥረት አድርግ። አንድን የሚያሳስብ ጉዳይ ለወላጅ ማማከር ሁልጊዜ ስህተት ነው? ይህን ማድረግ ተገቢ ሊሆን የሚችለው መቼ ነው? ሁለታችሁም ተስማምታችሁ ምክንያታዊ የሆነ ገደብ ካወጣችሁ ይህ ጉዳይ ችግር አይፈጥርም።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ፊልጵስዩስ 4:5