አገሮችና ሕዝቦች
ሆንዱራስን እንጎብኝ
ሆንዱራስ በስፓንኛ ቋንቋ “ጥልቆች” ማለት ሲሆን ክሪስቶፈር ኮሎምበስ አገሪቷ ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ጋር በምትዋሰንበት አካባቢ ያለውን ውኃ ጥልቀት ለመግለጽ የተጠቀመበት ቃል ሳይሆን አይቀርም። ሆንዱራስ ስሟን ያገኘችው በዚህ መንገድ እንደሆነ አንዳንዶች ይናገራሉ።
የሆንዱራስ ተወላጆች ለቤተሰብ ታማኝ መሆንን እንዲሁም ተባብሮ መሥራትን ከፍ አድርገው ይመለከታሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ከቤት ወጪዎች ወይም ከልጆች ትምህርት ጋር የተያያዙ ትላልቅ ውሳኔዎች ብዙውን ጊዜ የሚደረጉት ባልና ሚስት ተመካክረው ነው።
አብዛኞቹ የሆንዱራስ ነዋሪዎች የአገሬው ተወላጆችና የአውሮፓውያን ክልሶች (ሜስቲዞ ተብለው ይጠራሉ) ናቸው። አንዳንዶቹ የአገሬው ተወላጆች እስከ ዛሬም ድረስ አሉ፤ ከእነዚህ መካከል ቾርቲ የተባለው ጎሳ አባላት ይገኙበታል። እንደ ጋሪፉና ያሉት ሌሎቹ የአገሬው ተወላጆች ደግሞ ከሌላ አካባቢ ከመጡ ሕዝቦች የተገኙ ናቸው።
የጋሪፉና ጎሳ አባላት የአፍሪካውያንና በሴንት ቪንሰንት ደሴት ላይ የሚኖሩ የአሜሪካ ሕንዳውያን ዝርያ ናቸው። የጋሪፉና ሕዝቦች
በ1797 ገደማ ወደ ኢዝላስ ዴ ላ ባዪያ (ቤይ ደሴቶች) መጡ። ቆየት ብሎም የማዕከላዊ አሜሪካ ክፍል በሆነው በካሪቢያን የባሕር ዳርቻ ሰፈሩ። ከጊዜ በኋላ ወደ ሌሎች ማዕከላዊና ሰሜን አሜሪካ ክፍሎች ተሰራጩ።የጋሪፉና ጎሳ አባላት ከጠንካራ እንጨቶች የተሠሩ ከበሮዎችን ምት እየተከተሉ መጨፈር ያስደስታቸዋል። ባሕላዊ ልብሳቸው በብሩህ ቀለማት ያሸበረቀ ሲሆን ተረት የማውራት ልማድም አላቸው፤ በተጨማሪም ኤሬባ የተባለውን ከካሳቫ ሥር የሚዘጋጅ ትልቅና ስስ ቂጣ ጨምሮ ሌሎች ባሕላዊ ምግቦች አሏቸው።
በሆንዱራስ 400 የሚያህሉ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች አሉ። ስብሰባዎች የሚካሄዱት በዋነኝነት በስፓንኛ ቢሆንም በሆንዱራስ የምልክት ቋንቋ፣ በሚስኪቶ፣ በማንደሪን ቻይንኛ፣ በእንግሊዝኛ እና በጋሪፉና ቋንቋዎች የሚካሄዱም አሉ።