መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
እንስሳት
ሁላችንም ከእንስሳት ጋር የሚያገናኘን ነገር ይገጥመናል። ታዲያ እንስሳትን የምንይዝበት መንገድ ያስጠይቀናል?
ሰዎች እንስሳትን መያዝ ያለባቸው እንዴት ነው?
ሰዎች ምን ይላሉ?
አንዳንድ ሰዎች፣ እንስሳትን በፈለግነው መንገድ ልንጠቀምባቸው እንችላለን ብለው ያምናሉ። ሌሎች ደግሞ እንስሳት ልክ እንደ ሰዎች ሊያዙ እንደሚገባ ይሰማቸዋል።
-
አንድ የታወቁ የእንስሳት መብት ተሟጋች፣ እንስሳት “እንደ ጥሬ ዕቃ ወይም እንደ ንግድ ሸቀጥ ተደርገው ያለመታየት መሠረታዊ መብታቸው” ሊከበርላቸው እንደሚገባ ተናግረዋል። አክለውም “እንስሳትን እንደ ንብረታችን አድርገን መመልከታችንን ማቆም አለብን” ብለዋል።
-
ብዙዎች ከልክ ያለፈ ድርጊት እንደሆነ አድርገው የሚመለከቱት ቢሆንም ሊዮና ሄልምስሊ የተባሉ አንዲት ቢልየነር ለውሻቸው 12 ሚሊዮን ዶላር በአደራ ትተውላታል፤ እንዲሁም ውሻቸው ስትሞት አፅሟ ከጎናቸው እንዲቀበር ተናዝዘዋል።
ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ እንስሳት እንዴት ያለ አያያዝ ሊደረግላቸው የሚገባ ይመስልሃል?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
የሕይወት ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ አምላክ “የባሕር ዓሣዎችን፣ በሰማያት ላይ የሚበርሩ ፍጥረታትንና በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱ ፍጥረታትን በሙሉ ግዟቸው” በማለት ለሰዎች ተናግሯል። (ዘፍጥረት 1:28) ይህ ከሆነ ደግሞ አምላክ ሰዎችን የሚመለከታቸው የእንስሳት የበላይ እንደሆኑ አድርጎ ነው ብሎ መደምደም ምክንያታዊ ነው።
ቀደም ሲል ከተጠቀሰው ጥቅስ በፊት የሚገኘው ሐሳብ ይህን ድምዳሜ የሚያጠናክር ምክንያት ይሰጠናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “አምላክም ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው፤ በአምላክ መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።”—ዘፍጥረት 1:27
ሰዎች የተፈጠሩት “በአምላክ መልክ” ስለሆነ እንደ ጥበብ፣ ፍትሕና ፍቅር ያሉትን የአምላክ ባሕርያት ማንጸባረቅ ይችላሉ፤ ይህም ከእንስሳት የተለዩ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። በተጨማሪም ሰዎች ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ነገሮችን የመገንዘብ ተፈጥሯዊ ችሎታ አላቸው። እንስሳት የተፈጠሩት “በአምላክ መልክ” ስላልሆነ እንደዚህ ያሉት ችሎታዎች የሏቸውም። እንስሳት ከሰዎች ያነሱ ፍጥረታት ሲሆኑ የተፈጠሩትም ለሰዎች የሚደረገው ዓይነት አያያዝ እንዲደረግላቸው ታስቦ አይደለም።
ታዲያ ሰዎች እንስሳትን የማሠቃየት መብት አላቸው ማለት ነው? አይደለም።
-
አምላክ ለእስራኤላውያን በሰጠው ሕግ ላይ ሕዝቡ እንስሳትን እንዲያሳርፏቸው፣ ምግብ እንዲሰጧቸው፣ ከሚደርስባቸው ሥቃይ እንዲያድኗቸው እንዲሁም ከጉዳት ጥበቃ እንዲያደርጉላቸው የሚያዝዙ መመሪያዎች ነበሩ።—ዘፀአት 23:4, 5፤ ዘዳግም 22:10፤ 25:4
“ለስድስት ቀን ሥራህን ሥራ፤ ሆኖም በሬህና አህያህ እንዲያርፉ . . . በሰባተኛው ቀን ሥራ አትሥራ።”—ዘፀአት 23:12
እንስሳትን መግደል ኃጢአት ነው?
ሰዎች ምን ይላሉ?
አደንን እንደ ስፖርት የሚመለከቱ አንዳንድ አዳኞችና ዓሣ አጥማጆች እንስሳቱን አባርሮ መያዝ ስለሚያስደስታቸው ብቻ አድነው ይገድሏቸዋል። ሌሎች ደግሞ እንስሳትን ገድሎ መብላት “በአጭሩ ነውር” እንደሆነ ከጻፈው ሩሲያዊ የልብ ወለድ ደራሲ ሊዮ ቶልስቶይ ጋር ይስማሙ ይሆናል።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
የሰውን ሕይወት ከአደጋ ለመከላከል ወይም ለልብስነት ሲባል ሰዎች እንስሳትን እንዲገድሉ አምላክ ፈቅዶላቸዋል። (ዘፀአት 21:28፤ ማርቆስ 1:6) በተጨማሪም ሰዎች እንስሳትን በመግደል ለምግብነት ሊጠቀሙባቸው እንደሚችሉ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ዘፍጥረት 9:3 “በሕይወት የሚንቀሳቀስ እያንዳንዱ እንስሳ ምግብ ይሁናችሁ” ይላል። ኢየሱስም እንኳ ደቀ መዛሙርቱን ዓሣ እንዲያጠምዱ የረዳቸው ሲሆን በኋላ ላይ ያጠመዷቸውን ዓሦች በልተዋል።—ዮሐንስ 21:4-13
ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ “ክፋትን የሚወዱ ሰዎችን ይጠላል” በማለት ይናገራል። (መዝሙር 11:5) በመሆኑም አምላክ፣ ለመዝናናት ወይም ለስፖርት ብቻ ብለን እንስሳትን እንድንጎዳ ወይም እንድንገድል እንደማይፈልግ የታወቀ ነው።
አምላክ የእንስሳትን ሕይወት ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት መጽሐፍ ቅዱስ ይጠቁማል።
-
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ፍጥረታት ወደ ሕልውና በመጡበት ወቅት ስለሆነው ነገር ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “[አምላክ] በምድር ላይ ያሉ የዱር እንስሳትን እንደየወገናቸው፣ የቤት እንስሳትን እንደየወገናቸው እንዲሁም መሬት ለመሬት የሚሄዱ ፍጥረታትን ሁሉ እንደየወገናቸው ሠራ። አምላክም ይህ መልካም እንደሆነ አየ።”—ዘፍጥረት 1:25
-
የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት “ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ሰውንና እንስሳን ትጠብቃለህ” በማለት ጸልዮአል። (መዝሙር 36:6) ለምሳሌ ይሖዋ፣ በዓለም ላይ የጥፋት ውኃ ባመጣበት ወቅት ስምንት ሰዎችና የሁሉም ዓይነት እንስሳት ዘሮች ከጥፋቱ እንዲተርፉ አድርጓል።—ዘፍጥረት 6:19
በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ይሖዋ የፈጠራቸውን እንስሳት የሚወድ ሲሆን ሰዎችም እንስሳትን በተገቢው መንገድ እንዲይዙ ይጠብቅባቸዋል።
“ጻድቅ የቤት እንስሳቱን ይንከባከባል።” —ምሳሌ 12:10