በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ዓመፅ

ዓመፅ

የሰው ዘር ታሪክ በዓመፅ የተሞላ ነው። ይህ አሳዛኝ ሁኔታ ለዘላለም ይቀጥል ይሆን?

አምላክ ለዓመፅ ምን አመለካከት አለው?

ሰዎች ምን ይላሉ?

ሃይማኖተኛ ሰዎችን ጨምሮ ብዙዎች በሚያበሳጫቸው ሰው ላይ የዓመፅ ድርጊት መፈጸም ተገቢ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ደግሞም በመገናኛ ብዙኃን የሚቀርቡት የዓመፅ ድርጊቶች በብዙ ሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች እንደ መዝናኛ ተደርገው ይታያሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

በኢራቅ በምትገኘው ሞሱል ከተማ አቅራቢያ በአንድ ወቅት ታላቅ ከተማ የነበረችው የጥንቷ አሦር ዋና ከተማ የነነዌ ፍርስራሽ ይገኛል። ከፍተኛ እንቅስቃሴ ይካሄድባት የነበረችው ይህች ከተማ በማደግ ላይ ሳለች አምላክ ‘ነነዌን ባድማ እንደሚያደርጋት’ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ትንቢት ተነግሮ ነበር። (ሶፎንያስ 2:13) አምላክ ‘ማላገጫ እንድትሆኚ አደርጋለሁ’ ብሎ ነበር። እንዲህ ያለበት ምክንያት ምን ነበር? ነነዌ ‘ደም አፍሳሽ ከተማ’ ስለነበረች ነው። (ናሆም 1:1፤ 3:1, 6) ይሖዋ “ዓመፀኞችን . . . ይጸየፋል” በማለት መዝሙር 5:6 ይናገራል። ነነዌ መፈራረሷ አምላክ ቃሉን እንደፈጸመ ያሳያል።

የዓመፅ ድርጊት የመነጨው የአምላክና የሰው ቀንደኛ ጠላት ከሆነው ከሰይጣን ዲያብሎስ ነው፤ ኢየሱስ ክርስቶስ “ነፍሰ ገዳይ” ብሎ ጠርቶታል። (ዮሐንስ 8:44) ከዚህም በላይ “መላው ዓለም . . . በክፉው ቁጥጥር ሥር” በመሆኑ የሰይጣን ባሕርያት ብዙዎች በመገናኛ ብዙኃን ለሚተላለፍ የዓመፅ ድርጊት ያላቸውን ፍቅር ጨምሮ ዓለም በጠቅላላው ለዓመፅ ባለው አመለካከት ላይ ተንጸባርቀዋል። (1 ዮሐንስ 5:19) አምላክን ለማስደሰት ከፈለግን ዓመፅን መጥላትና አምላክ የሚወደውን መውደድ አለብን። * ይሁንና ይህን ማድረግ ይቻላል?

“ይሖዋ . . . ክፋትን የሚወዱ ሰዎችን ይጠላል።”መዝሙር 11:5

ዓመፀኞች ሊለወጡ ይችላሉ?

ሰዎች ምን ይላሉ?

የዓመፀኝነት ባሕርይ ሊለወጥ የማይችል የሰው ተፈጥሮ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

“ቁጣን፣ ንዴትን፣ ክፋትንና ስድብን ሁሉ ከእናንተ አስወግዱ” ይላል። በተጨማሪም “አሮጌውን ስብዕና ከነልማዶቹ ገፋችሁ ጣሉ፤ እንዲሁም . . . አዲሱን ስብዕና ልበሱ” ይላል። (ቆላስይስ 3:8-10) አምላክ ከእኛ የሚጠብቀው ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር ነው? አይደለም። ሰዎች ሊለወጡ ይችላሉ። * እንዴት?

የመጀመሪያው እርምጃ ስለ አምላክ ትክክለኛ እውቀት መቅሰም ነው። (ቆላስይስ 3:10) ቅን ልብ ያለው አንድ ሰው ስለ ፈጣሪያችን ማራኪ ባሕርያትና የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ሲማር አምላክን በመውደድ ወደ እሱ የሚቀርብ ሲሆን እሱን ማስደሰት ይፈልጋል።—1 ዮሐንስ 5:3

ሁለተኛው እርምጃ የጓደኛ ምርጫችንን የሚመለከት ነው። “ከግልፍተኛ ሰው ጋር አትግጠም፤ በቀላሉ ቱግ ከሚል ሰውም ጋር አትቀራረብ፤ አለዚያ መንገዱን ትማራለህ፤ ለራስህም ወጥመድ ይሆናል።”—ምሳሌ 22:24, 25

ሦስተኛው እርምጃ አስተዋይ ከመሆን ጋር የተያያዘ ነው። የዓመፅ ድርጊት ወደ መፈጸም የሚገፋፋንን ነገር ይኸውም ራሳችንን በመግዛት ረገድ ያለብንን ድክመት ማስተዋል ይኖርብናል። ሰላማዊ የሆኑ ሰዎች ውስጣዊ ጥንካሬ አላቸው። ምሳሌ 16:32 “ቶሎ የማይቆጣ ሰው ከኃያል ሰው . . . ይሻላል” ይላል።

“ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር ጥረት አድርጉ።”ዕብራውያን 12:14

ዓመፅ የማይኖርበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?

ሰዎች ምን ይላሉ?

የጭካኔ ድርጊት አብሮን የኖረ ነገር ነው፤ ወደፊትም ቢሆን ይቀጥላል።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

“ለጥቂት ጊዜ ነው እንጂ ክፉዎች አይኖሩም፤ . . . የዋሆች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በብዙ ሰላምም እጅግ ደስ ይላቸዋል።” (መዝሙር 37:10, 11) አዎ፣ አምላክ የዋህና ሰላማዊ የሆኑ ሰዎችን ለማዳን ሲል ዓመፅ የሚወዱ ሰዎችን ልክ እንደ ጥንቷ ነነዌ ያጠፋል። ከዚያ በኋላ ምድር ዳግመኛ በዓመፅ አትታመስም!—መዝሙር 72:7

“ገሮች . . . ምድርን ይወርሳሉ።” —ማቴዎስ 5:5

በመሆኑም የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ሰላማዊ ለመሆን ጥረት ማድረግ ያለብን አሁን ነው። ሁለተኛ ጴጥሮስ 3:9 “ይሖዋ . . . እናንተን የታገሠው፣ ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ እንጂ ማንም እንዲጠፋ ስለማይፈልግ ነው” ይላል።

“ሰይፋቸውን ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ።”ኢሳይያስ 2:4

^ አን.7 አምላክ የጥንቶቹ እስራኤላውያን ድንበራቸውን ከወራሪዎች ለመከላከል በጦርነት እንዲካፈሉ እንደፈቀደ አይካድም። (2 ዜና መዋዕል 20:15, 17) ይሁን እንጂ አምላክ ከእስራኤል ጋር የገባው ቃል ኪዳን እንዲሻር አድርጎ ድንበር የሌለውን የክርስቲያን ጉባኤ ካቋቋመ ወዲህ ሁኔታው ተለውጧል።

^ አን.11 “መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል” በተሰኘው በመጠበቂያ ግንብ ላይ የሚወጣ ተከታታይ ዓምድ ላይ ባሕርያቸውን የለወጡ ሰዎችን ምሳሌ ማግኘት ይቻላል።