የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ
ለገንዘብ ሚዛናዊ አመለካከት ይኑርህ
“ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ” የሚል አባባል አለ። ይህ አባባል በተወሰነ ደረጃ እውነትነት አለው። ደግሞም ምግብ፣ ልብስና ቤት ለመግዛት ወይም የቤት ኪራይ ለመክፈል ገንዘብ ያስፈልጋል። አንድ የመጽሔት አዘጋጅ “ገንዘብ በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚጫወተው ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው” ሲሉ ጽፈዋል። አክለውም “እርስ በርስ ለመገበያየት የምንጠቀምበት ገንዘብ እንዲወገድ ቢደረግ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሽብርና ጦርነት ይነግሣል” ብለዋል።
እርግጥ ገንዘብ ሁሉን ነገር ማድረግ ያስችላል ማለት አይደለም። አርነ ጋርቦርግ የተባሉ ኖርዌጂያዊ ጸሐፊ ተውኔት ስለ ገንዘብ እንደሚከተለው ብለዋል፦ “[በገንዘብ] ምግብ መግዛት እንችላለን፣ የምግብ ፍላጎት ግን መግዛት አንችልም፤ መድኃኒት መግዛት እንችላለን፣ ጤናን ግን መግዛት አንችልም፤ ምቹ አልጋ መግዛት እንችላለን፣ እንቅልፍን ግን መግዛት አንችልም፤ እውቀትን መግዛት እንችላለን፣ ጥበብን ግን መግዛት አንችልም፤ ብልጭልጭ ነገሮችን መግዛት እንችላለን፣ ውበትን ግን መግዛት አንችልም፤ ራሳችንን ግርማ ሞገስ ማላበስ እንችላለን፣ አፍቃሪነትን ግን መግዛት አንችልም፤ ሊያስቁን የሚችሉ ነገሮችን መግዛት እንችላለን፣ ደስታን ግን መግዛት አንችልም፤ ጓደኛ ማፍራት እንችላለን፣ እውነተኛ ወዳጅነትን ግን መግዛት አንችልም፤ አገልጋዮችን መቅጠር እንችላለን፣ ታማኝነትን ግን መግዛት አንችልም።”
አንድ ሰው ለገንዘብ ሚዛናዊ አመለካከት ካለው ገንዘብን ግቡ ላይ ለመድረስ እንደሚረዳው ነገር እንጂ የሕይወቱ ዋና ግብ አድርጎ አይመለከተውም፤ እንዲህ ዓይነት አመለካከት ያለው ሰው ባለው ነገር ረክቶ መኖር ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ያስጠነቅቃል፦ “የገንዘብ ፍቅር የብዙ ዓይነት ጎጂ ነገሮች ሥር ነውና፤ አንዳንዶች በዚህ ፍቅር ተሸንፈው . . . ሁለንተናቸውን በብዙ ሥቃይ ወግተዋል።”—1 ጢሞቴዎስ 6:10
ለጉዳት የሚዳርገው ገንዘብ ራሱ ሳይሆን የገንዘብ ፍቅር መሆኑን ልብ በል። ለገንዘብ ተገቢ ያልሆነ አመለካከት ማዳበር በጓደኛሞች መካከል ሌላው ቀርቶ በቤተሰብ አባላት መካከል ከፍተኛ ቅራኔ እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።
* “ቶማስ የተባለውን ጓደኛዬን ሁሌም ጥሩና ሐቀኛ ሰው እንደሆነ አድርጌ እመለከተው ነበር። መኪናዬን እስከሸጥኩለት ጊዜ ድረስ ጥሩ ግንኙነት ነበረን። መኪናው ችግር ይኑርበት አይኑርበት የማውቀው ነገር አልነበረም። ያም ሆኖ መኪናውን ባለበት ሁኔታ ለመግዛት ስለተስማማ በጽሑፍ ተዋዋልን። ከሦስት ወር በኋላ መኪናው ተበላሸ። በዚህ ጊዜ ቶማስ እንዳታለልኩት ስለተሰማው በጣም ተበሳጭቶ ገንዘቡን እንድመልስለት ይጨቀጭቀኝ ጀመር። ፈጽሞ ያልጠበቅኩት ነገር ሆነብኝ! ላስረዳው ብሞክርም ቁጣው ሊበርድለት አልቻለም። ገንዘብ በመካከላችን ስለገባ ቶማስ ያ የማውቀው ጥሩ ጓደኛዬ ሊሆንልኝ አልቻለም።”
ዳንኤል፦ኢሲን፦ “በቤተሰባችን ውስጥ ያለነው ልጆች ሁለት ብቻ ነን። እኔና እህቴ ኔስሪም እንዋደድ ነበር፤ በመሆኑም በገንዘብ እንጣላለን ብዬ ፈጽሞ አስቤ አላውቅም። የሚያሳዝነው ግን ይህ ነገር ተከሰተ። ወላጆቻችን ሲሞቱ የተወሰነ ነገር ያወረሱን ሲሆን ገንዘቡንም እኩል እንድንካፈል ተናዘው ነበር። እህቴ ግን ከወላጆቻችን ኑዛዜ ውጭ ብዙ ድርሻ መውሰድ ፈለገች። እኔ የወላጆቻችን ኑዛዜ እንዲከበር ፍላጎት ነበረኝ፤ እሷ ግን በንዴት ገንፍላ ጭራሽ ትዝትብኝ ጀመር። እስከ ዛሬም ድረስ ንዴቷ አልበረደላትም።”
ገንዘብ አመለካከትን ያዛባል
ሰዎች ለገንዘብ ያላቸው የተዛባ አመለካከት ለሰዎችም የተዛባ አመለካከት እንዲኖራቸው ሊያደርግ ይችላል። ለምሳሌ ሀብታም ሰው፣ ድሆችን ራሳቸውን ማሻሻል የማይፈልጉ ሰነፎች አድርጎ ሊመለከታቸው ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ድሃ ሰው ሀብታሞችን ፍቅረ ነዋይ የተጠናወታቸው ወይም ስግብግቦች እንደሆኑ አድርጎ ሊያስብ ይችላል። ደህና ኑሮ ባለው ቤተሰብ ውስጥ ያደገች ሊያን የተባለች ወጣት እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ደርሶባታል። እንዲህ በማለት ተናግራለች፦
መጽሐፍ ቅዱስ ገንዘብን አስመልክቶ የሚሰጠው ምክር ጥንት ጠቃሚ እንደነበረ ሁሉ ዛሬም ጠቃሚ ነው
“ሰዎች አባቴ ገንዘብ ሞልቶ የተረፈው ሰው እንደሆነ አድርገው ይናገራሉ። ብዙ ጊዜ ‘አንቺ ምን አለብሽ፣ አባትሽን የፈለግሽውን ነገር እንዲያደርግልሽ መጠየቅ ትችያለሽ’ ወይም ‘ይቅርታ፣ እኛ እንደ እናንተ ሀብታሞች አይደለንም፤ አሪፍ አሪፍ መኪና መግዛት አንችልም’ የሚሉ አስተያየቶችን ሲሰነዝሩ እሰማለሁ። ጓደኞቼን ከአሁን በኋላ እንዲህ እንዳይሉኝ ነገርኳቸው፤ እንዲህ ያለው አስተያየት ስሜቴን ምን ያህል እንደሚጎዳውም ገለጽኩላቸው። ምክንያቱም ሰዎች እንዲያውቁኝ የምፈልገው በሀብታምነቴ ሳይሆን ለሌሎች በማደርገው መልካም ነገር ነው።”
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
መጽሐፍ ቅዱስ ገንዘብንም ሆነ ገንዘብ ያላቸውን ሰዎች፣ ሌላው ቀርቶ ብዙ ገንዘብ ያላቸውንም ቢሆን አያወግዝም። ዋናው ነጥብ፣ አንድ ሰው ያለው የገንዘብ መጠን ሳይሆን ስላለው ገንዘብም ሆነ ገንዘብ ስለማግኘት ያለው አመለካከት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ገንዘብን አስመልክቶ የሚሰጠው ምክር ሚዛናዊ ሲሆን ምክሩ ጥንት ጠቃሚ እንደነበረ ሁሉ ዛሬም ጠቃሚ ነው። አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ሀብት ለማግኘት አትልፋ።”—ምሳሌ 23:4
ዘ ናርሲሲዝም ኤፒደሚክ የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው ከሆነ ሀብት የሚያሳድዱ ሰዎች በአብዛኛው “የአእምሯቸው ጤንነት ሊታወክ ይችላል፤ እንዲሁም እንደ ጉሮሮ ቁስለት፣ የወገብ በሽታና ራስ ምታት የመሳሰሉ የጤና እክሎች ያጋጥሟቸዋል፤ በተጨማሪም ከልክ በላይ አልኮል የመጠጣትና ዕፅ የመውሰድ አዝማሚያ ይኖራቸዋል። ብዙ ገንዘብ ለማካበት መጣር ሰዎች ደስታ እንዲርቃቸው እያደረገ ያለ ይመስላል።”
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “አኗኗራችሁ ከገንዘብ ፍቅር ነፃ ይሁን፤ ባሏችሁ ነገሮች ረክታችሁ ኑሩ።”—ባሉት ነገሮች ረክቶ የሚኖር ሰው ከገንዘብ ጋር የተያያዘ ጭንቀት አያጋጥመውም ማለት አይደለም፤ ሆኖም ይህ ጭንቀት እንዲቆጣጠረው አይፈቅድም። ለምሳሌ ገንዘቡን በሆነ መንገድ ቢያጣ ከልክ በላይ ስሜታዊ አይሆንም። ከዚህ ይልቅ እንደሚከተለው ብሎ የጻፈውን የሐዋርያው ጳውሎስን አመለካከት ያንጸባርቃል፦ “በትንሽ ነገር እንዴት መኖር እንደሚቻልም ሆነ ብዙ አግኝቶ እንዴት መኖር እንደሚቻል አውቃለሁ። በማንኛውም ነገርና በሁሉም ሁኔታ ጠግቦም ሆነ ተርቦ፣ ብዙ አግኝቶም ሆነ አጥቶ መኖር የሚቻልበትን ሚስጥር ተምሬአለሁ።”—ፊልጵስዩስ 4:12
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “በሀብቱ የሚታመን ሰው ይወድቃል።”—ምሳሌ 11:28
ብዙ ትዳሮችን ለፍቺ ከሚዳርጉ ችግሮች መካከል በዋነኝነት የሚጠቀሰው በገንዘብ የተነሳ የሚፈጠር አለመግባባት እንደሆነ አንዳንድ ተመራማሪዎች ይናገራሉ። በተጨማሪም ሰዎች ራሳቸውን እንዲያጠፉ ከሚያደርጉት ምክንያቶች መካከል አንዱ ከገንዘብ ጋር የተያያዘ ችግር ነው። አንዳንዶች ገንዘብን ከትዳራቸው አልፎ ተርፎም ከሕይወታቸው አስበልጠው ይመለከቱታል! ከዚህ በተቃራኒ ለገንዘብ ሚዛናዊ አመለካከት ያላቸው ሰዎች እምነታቸውን በገንዘብ ላይ አይጥሉም። እንዲያውም “አንድ ሰው ሀብታም ቢሆንም እንኳ ንብረቱ ሕይወት ሊያስገኝለት አይችልም” በማለት ኢየሱስ የሰጠውን ጥበብ ያዘለ ምክር ይከተላሉ።—ሉቃስ 12:15
አንተ ለገንዘብ ምን አመለካከት አለህ?
በዚህ ረገድ ራስህን መመርመርህ ለገንዘብ ሚዛናዊ አመለካከት ማዳበር ያስፈልግህ እንደሆነና እንዳልሆነ እንድትገነዘብ ሊረዳህ ይችላል። ለምሳሌ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ራስህን መጠየቅ ትችላለህ፦
-
በአጭር ጊዜ ሀብታም ለመሆን ያስችላሉ የሚባሉ ውጥኖች ያጓጉኛል?
-
ገንዘቤን በልግስና መስጠት ያሳሳኛል?
-
ስለ ገንዘብና ስላፈሩት ንብረት ማውራት ከሚቀናቸው ሰዎች ጋር መወዳጀት ያስደስተኛል?
-
ገንዘብ ለማግኘት ስል እዋሻለሁ ወይም ጨዋነት የጎደለው ድርጊት እፈጽማለሁ?
-
ገንዘብ ስላለኝ ተፈላጊ ሰው እንደሆንኩ ይሰማኛል?
-
ሁልጊዜ የማስበው ስለ ገንዘብ ነው?
-
ለገንዘብ ያለኝ አመለካከት በጤንነቴም ሆነ በቤተሰብ ሕይወቴ ላይ መጥፎ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው?
ለሌሎች በመስጠት የልግስና መንፈስ አዳብር
ከእነዚህ ጥያቄዎች መካከል ለአንዱም እንኳ ‘አዎ’ የሚል መልስ ከሰጠህ እንዲህ ያለውን አስተሳሰብ ለማስወገድና ፈታኝ ከሆኑ ሁኔታዎች ለመራቅ ጥረት አድርግ። ለገንዘብና ለቁሳዊ ሀብት ትልቅ ግምት ከሚሰጡ ሰዎች ጋር አትወዳጅ። ከቁሳዊ ሀብት ይልቅ ላቅ ላሉ የሥነ ምግባር መመሪያዎች ትልቅ ቦታ ከሚሰጡ ሰዎች ጋር ወዳጅነት መሥርት።
የገንዘብ ፍቅር በልብህ ውስጥ ሥር እንዲሰድ ፈጽሞ አትፍቀድ። ለገንዘብ ትክክለኛ አመለካከት ይኑርህ፤ መቼም ቢሆን ከጓደኞችህ፣ ከቤተሰብህ እንዲሁም ከስሜታዊም ሆነ ከአካላዊ ጤንነትህ አስበልጠህ እንዳትመለከተው ተጠንቀቅ። እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ለገንዘብ ሚዛናዊ አመለካከት እንዳለህ ታሳያለህ።
^ አን.7 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።