በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ዝግመተ ለውጥ

ዝግመተ ለውጥ

አንዳንድ ሰዎች ሕይወት የተገኘው በዝግመተ ለውጥ ነው ይላሉ። ሌሎች ደግሞ አምላክ መፍጠር ከጀመረ በኋላ በዝግመተ ለውጥ አማካኝነት ሂደቱ እንዲጠናቀቅ አድርጓል የሚል ጠንካራ አቋም አላቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል?

‘ጽንፈ ዓለም የተገኘው በአንድ ታላቅ ፍንዳታ ነው’ የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይጋጫል?

መጽሐፍ ቅዱስ “በመጀመሪያ አምላክ ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ” ይላል። (ዘፍጥረት 1:1) መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ እያንዳንዱን ነገር የፈጠረው እንዴት እንደሆነ በዝርዝር አይገልጽም። በመሆኑም ጽንፈ ዓለማችን የተገኘው በሕዋ ውስጥ በተከሰተ ታላቅ ፍንዳታ (ቢግ ባንግ) አማካኝነት ቢሆን እንኳ ይህ ሐሳብ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚናገረው ነገር ጋር አይጋጭም። እንዲያውም ዘፍጥረት 1:1 ይህ ፍንዳታ እንዲከሰት ያደረገው ማን ነው? ለሚለው ጥያቄ መልስ ይሰጣል።

እርግጥ ነው፣ ብዙ የሳይንስ ሊቃውንት ይህ ታላቅ ፍንዳታ ድንገተኛና ምንም ዓላማ የሌለው እንደሆነ ያምናሉ፤ በተጨማሪም በዚህ ፍንዳታ ምክንያት የተለያዩ ንጥረ ነገሮች በራሳቸው አንድ ላይ ተገጣጥመው በጊዜ ሂደት ከዋክብትና ፕላኔቶች እንደተገኙ ይሰማቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን አመለካከት አይደግፍም፤ ከዚህ ይልቅ ጽንፈ ዓለምን የሠራው አምላክ እንደሆነ ይናገራል፤ አምላክ ጽንፈ ዓለምን የፈጠረው በሕዋ ውስጥ አንድ ዓይነት ፍንዳታ እንዲከሰት በማድረግ ወይም በሌላ መንገድ ሊሆን ይችላል።

“በመጀመሪያ አምላክ ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ።”ዘፍጥረት 1:1

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወት ያላቸው ነገሮች በጊዜ ሂደት ሊለወጡ እንደሚችሉ የሚጠቁም ሐሳብ ይዟል?

አዎ። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ሕይወት ያላቸውን ነገሮች የፈጠረው “እንደየወገናቸው” እንደሆነ ይናገራል። (ዘፍጥረት 1:11, 12, 21, 24, 25) ታዲያ በአንድ ወገን ወይም ዝርያ ውስጥ ልዩነት ሊፈጠር ይችላል? አዎ ይችላል። ይሁንና በአንድ ወገን ውስጥ ያሉ ሕያዋን ፍጥረታት ከአካባቢያቸው ጋር ለመላመድ ለውጥ ማድረጋቸው በዝግመተ ለውጥ አማካኝነት ቀስ በቀስ አዲስ ዓይነት ዝርያ እንደሚገኝ ያረጋግጣል? አያረጋግጥም።

ተመራማሪዎች በ1970ዎቹ በጋላፓጎስ ደሴቶች በሚገኙ ፊንች የሚባሉ የአእዋፍ ዝርያዎች ላይ ያካሄዱትን ጥናት እንደ ምሳሌ እንመልከት። ተመራማሪዎቹ ተለቅ ያለ ምንቃር ያላቸው ፊንቾች የአየር ንብረቱ በመለወጡ ምክንያት ከሌሎቹ ይልቅ በሕይወት የመትረፍ አጋጣሚያቸው ሰፋ ያለ እንደነበር አስተዋሉ። አንዳንዶች ይህ ዝግመተ ለውጥን የሚደግፍ ማስረጃ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ ይህ የዝግመተ ለውጥ ማስረጃ ነው? ወይስ ከአካባቢያቸው ጋር ለመላመድ የሚያደርጉት ለውጥ? የሚገርመው፣ ከዓመታት በኋላ ትናንሽ ምንቃር ያላቸው ፊንቾች ከሌሎቹ ፊንቾች በልጠው ተገኙ። ይህ ሁኔታ የአንትሮፖሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑትን ጄፍሪ ሽዋርዝን የሚከተለው መደምደሚያ ላይ እንዲደርሱ አድርጓቸዋል፦ ከአካባቢው ጋር የመላመድ ችሎታ አንድን ዝርያ ተለዋዋጭ የሆኑ ሁኔታዎችን መቋቋም እንዲችል ይረዳዋል እንጂ “አዲስ ዝርያ እንዲፈጠር አያደርግም።”

መጽሐፍ ቅዱስና የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ሊስማሙ ይችላሉ?

መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሁሉንም ነገሮች የፈጠረው አምላክ’ እንደሆነ ይናገራል። (ራእይ 4:11) አምላክ የፍጥረት ሥራዎቹን እስኪያጠናቅቅ ድረስ ‘አላረፈም።’ (ዘፍጥረት 2:2) መልእክቱ ግልጽ ነው፦ አምላክ አንድ ውስብስብ ያልሆነ ሕይወት ያለው ነገር ፈጥሮ አላረፈም፤ ወይም ይህ ፍጥረት በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ዓመታት ውስጥ በዝግመተ ለውጥ አማካኝነት ወደተለያዩ የዓሣ፣ የዝንጀሮና የሰው ዝርያዎች እንዲለወጥ አላደረገም። * የማክሮኢቮሉሽን (የትልቅ ለውጥ) አራማጆች መጽሐፍ ቅዱስ ፈጣሪ “ሰማያትን፣ ምድርን፣ ባሕርንና በውስጣቸው ያሉትን ነገሮች ሁሉ” እንደሠራ የሚናገረውን ሐሳብ አይቀበሉም።—ዘፀአት 20:11፤ ራእይ 10:6

“ይሖዋ አምላካችን፣ ሁሉንም ነገሮች ስለፈጠርክ . . . ግርማ፣ ክብርና ኃይል ልትቀበል ይገባሃል።”ራእይ 4:11

ተጨማሪ ነገር ለማወቅ፦ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “የማይታዩት [የአምላክ ባሕርያት] . . . ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ በግልጽ ይታያሉ፤ ምክንያቱም ባሕርያቱን ከተሠሩት ነገሮች ማስተዋል ይቻላል።” (ሮም 1:20) አምላክ እሱን ከልብ የሚፈልጉትን ጨምሮ ለሁሉም ሰዎች በፍቅር ተነሳስቶ ያዘጋጀላቸው መልካም ነገር አለ፤ በመሆኑም ስለ አምላክ መማር ሕይወት እውነተኛ ትርጉም እንዲኖረው ያደርጋል። (መክብብ 12:13፤ ዕብራውያን 11:6) ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ከፈለግክ www.mt1130.com/am የተባለውን ድረ ገጽ መመልከት ወይም በአካባቢህ ያሉትን የይሖዋ ምሥክሮች ማናገር ትችላለህ። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች > የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው የሚለውን ተመልከት።

^ አን.12 ክሪኤሽኒስት ተብለው የሚጠሩት የፍጥረት አማኞች ‘አምላክ ምድርን የፈጠረው የ24 ሰዓት ርዝማኔ ባላቸው ስድስት ቀናት ውስጥ ነው’ ቢሉም መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ሐሳብ አይደግፍም። ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው? የሚለውን ብሮሹር ከገጽ 24-27 ተመልከት። በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ይህን ብሮሹር ከwww.mt1130.com/am ላይ በነፃ ማውረድ ይቻላል።