የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ
ሃይማኖቶች ተከታይ እያጡ ነው?
በቱርክ የተወለደው ጃፋር ሃይማኖቱ በሚያስተምረው ‘አምላክ ተበቃይ ነው’ በሚለው ትምህርት ይረበሽ ነበር። ባለቤቱ ሄዲዬም ብትሆን ስለ ሃይማኖቷ ጥርጣሬ ያደረባት ገና የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሳለች ነው። “የሰዎች ዕድል አስቀድሞ የተወሰነ እንደሆነ ተምሬ ነበር” ብላለች። “ወላጆቼ በልጅነቴ ስለሞቱ ‘ይህ ሁሉ የሚደርስብኝ ምን አጥፍቼ ነው?’ ብዬ አስብ ነበር። ብዙ ጊዜ ሌሊቱን ሙሉ ሳለቅስ አድር ነበር። አሥራ አምስት ዓመት ሲሆነኝ በሃይማኖቴ ተስፋ ቆረጥኩ።”
አንተስ በሃይማኖት ድርጅቶች ተስፋ ቆርጠሃል? ከሆነ እንደዚህ የሚሰማህ አንተ ብቻ አይደለህም። በብዙ አገሮች ሃይማኖተኛ እንዳልሆኑ የሚናገሩ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፤ ይህም የሃይማኖት ድርጅቶች የወደፊት ዕጣ አስጊ እንደሆነ የሚያሳይ ነው። እስቲ ጥቂት አገሮችን እንደ ምሳሌ እንውሰድ።
ብዙዎች ጥለው እየወጡ ያሉት ለምንድን ነው?
ሰዎች በሃይማኖት ድርጅቶች ተስፋ እንዲቆርጡ የሚያደርጓቸው የተለያዩ ምክንያቶች አሉ። ከእነዚህ መካከል የሃይማኖት ድርጅቶች የሚቆሰቁሷቸውና የሚደግፏቸው የዓመፅና የሽብር ተግባሮች፣ የሃይማኖት መሪዎች የፆታ ቅሌት እንዲሁም ብዙም ትኩረት የማይሰጣቸው ሆኖም ትልቅ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ሌሎች ምክንያቶች ይገኙበታል። ትኩረት ከማይሰጣቸው ምክንያቶች መካከል የሚከተሉት ተጠቃሽ ናቸው፦
-
ሀብት፦ “ሀብታም እየሆንክ በሄድክ መጠን ለሃይማኖት የምትሰጠው ቦታ እየቀነሰ ይመጣል” በማለት ግሎባል ኢንዴክስ ኦቭ ሪሊጅን ኤንድ ኤቲይዝም ገልጿል። በብዙ አገሮች ውስጥ ያሉ ሰዎች ብልጽግና እየጨመረ በመሆኑ ይህ አስተያየት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው። በአንዳንድ አገሮች፣ “ከሁለት መቶ ዓመታት በፊት ይኖር የነበረን ታላቅ ንጉሥ እንኳ በጣም ሊያስቀና የሚችል የቅንጦት ኑሮ” የሚመሩ ሰዎች እንዳሉ ጆን ኒ የተባሉ የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር ገልጸዋል።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? መጽሐፍ ቅዱስ “በመጨረሻዎቹ ቀናት” ሰዎች ለገንዘብና ለሥጋዊ ደስታ ያላቸው ፍቅር ለአምላክና ለሰዎች ካላቸው ፍቅር እንደሚበልጥ አስቀድሞ ተናግሯል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ሀብት የሚያስከትለውን አደጋ የተረዳ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ “ባለጸጋ አታድርገኝ” በማለት ይሖዋ አምላክን ለምኗል። ለምን? “አለዚያ እጠግብና እክድሃለሁ” ሲል ምክንያቱን ተናግሯል።—ምሳሌ 30:8, 9
-
ሃይማኖታዊ ወጎችና ሥነ ምግባር፦ ብዙ ሰዎች፣ በተለይ ደግሞ ወጣቶች የአንድ ሃይማኖት ድርጅት አባል መሆናቸው በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ላይ ምንም ለውጥ እንደማያመጣ ይሰማቸዋል። ሌሎች ደግሞ በሃይማኖት ላይ ያላቸውን እምነት አጥተዋል። የሂዩማኒስት ሶሳይቲ ስኮትላንድ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት ቲም ማጓየር እንዲህ ብለዋል፦ “ባለፉት መቶ ዓመታት አብያተ ክርስትያናት የፈጸሙትን ድርጊት ከተመለከትን ሰዎች ለሃይማኖት ተቋማት ጀርባቸውን የሰጡት እነዚህ ድርጅቶች፣ የሥነ ምግባር መሥፈርት ለማውጣት ብቁ እንዳልሆኑ ስለተሰማቸው እንደሆነ እንረዳለን።”
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? ኢየሱስ ክርስቶስ ሐሰተኛ አስተማሪዎችን በተመለከተ “ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። . . . ጥሩ ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያፈራል፤ የበሰበሰ ዛፍ ሁሉ ግን መጥፎ ፍሬ ያፈራል” ሲል አስጠንቅቋል። (ማቴዎስ 7:15-18) ይህ “መጥፎ ፍሬ” ፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ መግባትንና እንደ ግብረሰዶም ያሉ አምላክ የሚጠላቸውን ድርጊቶች መደገፍን ያካትታል። (ዮሐንስ 15:19፤ ሮም 1:25-27) እንዲሁም በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ያሉትን ጠቃሚ ትምህርቶች ትርጉም የለሽ በሆኑ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችና ወጎች መተካትን ይጨምራል። (ማቴዎስ 15:3, 9) ኢየሱስ ‘ግልገሎቼን መግቡ’ በማለት አዝዞ ነበር። (ዮሐንስ 21:17) በአሁኑ ጊዜ ግን ብዙዎች በመንፈሳዊ ተርበዋል።
-
ሃይማኖትና ገንዘብ፦ ፒው የምርምር ማዕከል እንደገለጸው ብዙ ሰዎች፣ የሃይማኖት ድርጅቶች ለገንዘብ ከሚገባው በላይ ትኩረት እንደሚሰጡ ይሰማቸዋል። ይባስ ብሎም አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች ከመንጎቻቸው በተለየ የተንደላቀቀ ሕይወት ይመራሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ምዕመናኑ ኑሮን ማሸነፍ አቅቷቸው እየታገሉ ባሉበት አንድ የጀርመን ከተማ ውስጥ ጳጳሱ የቅንጦት ኑሮ በመኖሩ ተተችቷል። ይህ አኗኗሩ በዚያ የሚኖሩ ብዙ የካቶሊክ እምነት ተከታዮችን ቅር አሰኝቷል። በተጨማሪም ጂኦ መጽሔት እንደዘገበው “መቶ ሚሊዮን ያህል ሰዎች በቀን ከአንድ ዩሮ በታች በሚያገኙባት በናይጄሪያ አንዳንድ ፓስተሮች የሚመሩት የቅንጦት ሕይወት ችግር እየፈጠረ ነው።”
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ጳውሎስ “የአምላክን ቃል አንነግድም” ሲል ጽፏል። (2 ቆሮንቶስ 2:17 የግርጌ ማስታወሻ) ጳውሎስ በጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለው አገልጋይ ቢሆንም እንኳ በሌሎች ላይ ሸክም ላለመሆን ሲል ብዙ ጊዜ የጉልበት ሥራ ይሠራ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 20:34) እንዲህ ማድረጉ “በነፃ እንደተቀበላችሁ በነፃ ስጡ” በማለት ኢየሱስ የሰጠውን ትእዛዝ እንደሠራበት ያሳያል።—ማቴዎስ 10:7, 8
የይሖዋ ምሥክሮች እነዚህን መመሪያዎች ተግባራዊ ስለሚያደርጉ ለጽሑፎቻቸውም ሆነ መጽሐፍ ቅዱስን ለማስተማር ክፍያ አይጠይቁም። እንዲሁም አሥራት አይቀበሉም ወይም በስብሰባዎቻቸው ላይ ሙዳየ ምጽዋት አያዞሩም። ከዚህ ይልቅ ለሥራቸው የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ የሚያገኙት እያንዳንዱ ግለሰብ በራሱ ተነሳሽነት በሚያደርገው መዋጮ ነው።—ማቴዎስ 6:2, 3
ብዙዎች ጥለው እንደሚወጡ ተተንብዮአል!
ከጥቂት አሥርተ ዓመታት በፊት፣ የሃይማኖት ድርጅቶች እንዲህ ዓይነት አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገቡ ማንም ሊገምት አይችልም ነበር። በሌላ በኩል ግን አምላክ እንዲህ ዓይነት ለውጥ እንደሚከሰት ስላወቀ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይህ ሐሳብ እንዲሰፍር አድርጓል። አምላክ፣ ምሳሌያዊ አገላለጽ በመጠቀም ለእሱ ታማኝ ያልሆኑትን ሃይማኖቶች በሙሉ “ታላቂቱ ባቢሎን” ከምትባል የተቀማጠለች አመንዝራ ጋር አመሳስሏቸዋል።—ራእይ 17:1, 5
ለሐሰት ሃይማኖት የተሰጠው ይህ ምሳሌያዊ አገላለጽ ተስማሚ ነው፤ ምክንያቱም እነዚህ የሃይማኖት ድርጅቶች ለአምላክ ታማኝ እንደሆኑ ቢናገሩም ሥልጣንና ሀብት ለማግኘት ሲሉ ከዓለም የፖለቲካ ባለሥልጣናት ጋር ተወዳጅተዋል። ራእይ 18:9 ‘የምድር ነገሥታት ከእሷ ጋር እንዳመነዘሩ’ ይናገራል። “ባቢሎን” የሚለው ስያሜ የተሰጣቸው መሆኑም የተገባ ነው፤ ምክንያቱም አብዛኞቹ የሐሰት ሃይማኖት ትምህርቶችና ልማዶች የመነጩት ከጥንቷ የባቢሎን ከተማ ነው፤ ከእነዚህ መካከል ነፍስ አትሞትም እንዲሁም አምላክ አንድም ሦስትም ነው እንደሚሉት ያሉ ትምህርቶችና የአስማት ድርጊቶች ይገኙበታል። ይህች ከተማ በሐሰት ሃይማኖትና በአጉል እምነት የተተበተበች ነበረች። *—ኢሳይያስ 47:1, 8-11
ኃያል የነበረችው ባቢሎን የወደቀችው ከጥቃት ይጠብቃት የነበረው በዙሪያዋ ያለው ከኤፍራጥስ ወንዝ የሚመጣው ውኃ ‘በደረቀ’ ጊዜ ነበር፤ ይህም የሜዶንና የፋርስ ሠራዊት ከተማዋን በቀላሉ ድል እንዲያደርግ አስችሎታል። (ኤርምያስ 50:1, 2, 38) እንዲያውም ባቢሎን በቁጥጥር ሥር የዋለችው በአንድ ሌሊት ብቻ ነው!—ዳንኤል 5:7, 28, 30
ታላቂቱ ባቢሎንም “በብዙ ውኃዎች ላይ” ተቀምጣለች። እነዚህ “ውኃዎች” የሚያመለክቱት ‘ወገኖችንና ብዙ ሕዝብን’ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፤ ራእይ 17:1, 15) መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ ምሳሌያዊ ውኃዎች እንደሚደርቁ ተንብዮአል፤ ይህ ደግሞ በዘመናችን ባለችው ባቢሎን ላይ የሚደርሰውን ፈጣንና አይቀሬ ጥፋት ያመለክታል። (ራእይ 16:12፤ 18:8) ለመሆኑ ባቢሎንን የሚያጠፋት ማን ነው? የፖለቲካ አጋሮቿ ናቸው፤ ቀደም ሲል ለእሷ የነበራቸው ፍቅር በጥላቻ ይተካል። እንዲሁም ይበዘብዟታል ወይም በምሳሌያዊ ሁኔታ ሥጋዋን ይበላሉ።—ራእይ 17:16, 17 *
በሌላ አባባል ‘ውኃዎቹ’ የሐሰት ሃይማኖትን የሚደግፉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ያመለክታሉ። (“ከእሷ ውጡ”!
ታላቂቱ ባቢሎን በቅርቡ ጥፋት ስለሚጠብቃት አምላክ በፍቅር ተነሳስቶ “ሕዝቤ ሆይ፣ የኃጢአቷ ተባባሪ መሆን የማትፈልጉና የሚደርስባት መቅሰፍት ተካፋይ መሆን የማትፈልጉ ከሆነ ከእሷ ውጡ” የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። (ራእይ 18:4) በእርግጥም፣ አምላክ ይህን ማሳሰቢያ የሰጠው ቀደም ሲል እንደተጠቀሱት እንደ ጃፋርና ሄዲዬ ላሉ፣ ከአምላክ በሚያርቁ ትምህርቶች ስሜታቸው ለተረበሸና የእሱን ሞገስ ማግኘት ለሚፈልጉ ሰዎች ነው።
ጃፋር መጽሐፍ ቅዱስን መማር ከመጀመሩ በፊት አምላክን ለመታዘዝ የሚያነሳሳው ዋነኛ ምክንያት ፍርሃት እንደሆነ ይሰማው ነበር። “ይሖዋ የፍቅር አምላክ እንደሆነና በፍቅር ተነሳስተን እንድንታዘዘው የሚፈልግ መሆኑን ማወቄ እፎይታ ሰጥቶኛል” ብሏል። (1 ዮሐንስ 4:8፤ 5:3) ሄዲዬ ደግሞ ወላጆቿን የነጠቃት አምላክ እንዳልሆነና ዕድሏ አስቀድሞ እንዳልተወሰነ ስታውቅ ውስጣዊ ሰላም አግኝታለች። እንደ ያዕቆብ 1:13 ያሉ አምላክ ማንንም በክፉ ነገር እንደማይፈትን የሚናገሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አጽናንተዋታል። እሷና ጃፋር የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የተቀበሉ ሲሆን ‘ከባቢሎን’ ሸሽተው ወጥተዋል።—ዮሐንስ 17:17
“አብን በመንፈስና በእውነት [ለማምለክ]” ሲሉ በታዛዥነት ከታላቂቱ ባቢሎን ሸሽተው የወጡ ሰዎች እሷ በምትጠፋበት ጊዜ ምንም ጉዳት አያገኛቸውም። (ዮሐንስ 4:23) እነዚህ ሰዎች “ውኃ ባሕርን እንደሚሸፍን ምድርም በይሖዋ እውቀት ትሞላለች” የሚለው ትንቢት ሲፈጸም ለማየት ተስፋ ያደርጋሉ።—ኢሳይያስ 11:9
አዎ፣ አምላክ ‘ሊዋሽ ስለማይችል’ የሐሰት አምልኮና ያፈራቸው መጥፎ ፍሬዎች በሙሉ ተጠራርገው ይጠፋሉ። (ቲቶ 1:2) በሌላ በኩል ደግሞ እውነተኛው አምልኮ ለዘላለም ያብባል!
^ አን.16 ስለ ታላቂቱ ባቢሎን፣ ሙታን ስላሉበት ሁኔታ፣ ስለ አምላክ ማንነትና ስለ አስማት ድርጊቶች መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ተመልከት። ይህ መጽሐፍ www.mt1130.com/am ላይ ይገኛል።
^ አን.18 በዚህ እትም ውስጥ የሚገኘውን “መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?—የዓለም መጨረሻ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።