የአንባቢያን ጥያቄዎች
የአንባቢያን ጥያቄዎች
ከምሳሌ 24:27 የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው?
የምሳሌ መጽሐፍ ጸሐፊ ለአንድ ወጣት ምክር ሲሰጥ እንዲህ ብሏል፦ “በደጅ ያለውን ሥራህን ፈጽም፤ ዕርሻህን አዘጋጅ፤ ከዚያም በኋላ ቤትህን ሥራ።” በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ይህ ምሳሌ የያዘው ትምህርት ምንድን ነው? አንድ ሰው ከማግባትና ቤተሰብ ከመመሥረት ጋር ተያይዞ የሚመጣውን ኃላፊነት በመገንዘብ እንዲህ ዓይነቱን እርምጃ ከመውሰዱ በፊት በደንብ መዘጋጀት እንዳለበት የሚገልጽ ነው።
ከዚህ ቀደም ይህ ጥቅስ፣ ባልና አባት የሆነ አንድ ሰው ስለ ሰብዓዊ ሥራው ብቻ ከማሰብ ይልቅ ቤተሰቡን ‘ለመሥራት’ ወይም ለማበረታታት (ለምሳሌ፣ ለቤተሰቡ መንፈሳዊ መመሪያ ለመስጠት) መጣር እንዳለበት የሚያመለክት እንደሆነ የተብራራበት ጊዜ ነበር። እንዲህ ያለው ማብራሪያ ትክክለኛና ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ ያለው መሆኑ የተረጋገጠ ቢሆንም በዚህ ጥቅስ ላይ ሊተላለፍ የተፈለገው ዋና ነጥብ ይህ አይመስልም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ሁለት ምክንያቶችን እንመልከት።
አንደኛ፣ ጥቅሱ “ቤትህን ሥራ” ሲል ቀደም ሲል የተመሠረተ ቤተሰብን ማበረታታትን ወይም ማጠናከርን ለማመልከት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ጥቅሱ የሚናገረው ቃል በቃል ቤት ስለ መሥራት ነው። “ሥራ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል በምሳሌያዊ አነጋገር ቤተሰብ መሥራትን ወይም መመሥረትን ማለትም ጎጆ መውጣትንና ልጆች ማፍራትን ሊያመለክትም ይችላል።
ሁለተኛ፣ ጥቅሱ ነገሮችን በተገቢው ቅደም ተከተል ማከናወንን የሚያጎላ በሌላ አባባል “መጀመሪያ ይህንን አድርግ፤ ከዚያም እንዲህ ታደርጋለህ” የሚል ይመስላል። ታዲያ ይህ ምሳሌ፣ አንድ ሰው በሰብዓዊ ነገሮች ረገድ ያለበትን ኃላፊነት መወጣቱ ከመንፈሳዊ ነገሮች መቅደም እንዳለበት መግለጹ ሊሆን ይችላል? እንዳልሆነ ግልጽ ነው!
በጥንት ዘመን አንድ ሰው የራሱን ‘ቤት ለመሥራት’ ማለትም ሚስት አግብቶ ቤተሰብ ለመመሥረት ከፈለገ ‘ሚስቴን እንዲሁም ልጆች ከወለድን እነሱን ለመንከባከብና ለማስተዳደር ዝግጁ ነኝ?’ ብሎ ራሱን መጠየቅ ያስፈልገው ነበር። ቤተሰብ ከመመሥረቱ በፊት እርሻውን ወይም ሰብሉን በመንከባከብ በውጭ መሥራት ነበረበት። በመሆኑም የ1980 ትርጉም ይህንን ጥቅስ እንዲህ በማለት በግልጽ አስቀምጦታል፦ “በመጀመሪያ በርስትህ ላይ ለኑሮህ የሚያስፈልግህን ሁሉ አደራጅ፤ ከዚያ በኋላ ቤት መሥራትና ትዳር ማቋቋም ትችላለህ።” ታዲያ ይህ መሠረታዊ ሥርዓት በዛሬው ጊዜም ይሠራል?
አዎን። ለማግባት የሚፈልግ ሰው ጋብቻው የሚያስከትልበትን ኃላፊነት ለመሸከም በሚገባ መዘጋጀት አለበት። አካላዊ ሁኔታው የሚፈቅድለት ከሆነ መሥራት ይኖርበታል። እርግጥ ነው፣ አንድ ወንድ ቤተሰቡን ለመንከባከብ ጠንክሮ መሥራት አለበት ሲባል ቁሳዊ ነገሮችን በማሟላት ብቻ ይወሰናል ማለት አይደለም። የቤተሰቡን አካላዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶች የማያሟላ ሰው እምነት የለሽ ከሆነ ሰው የከፋ እንደሆነ የአምላክ ቃል ይገልጻል! (1 ጢሞ. 5:8) በመሆኑም አንድ ወጣት ለማግባትና ቤተሰብ ለመመሥረት በሚዘጋጅበት ወቅት ራሱን እንዲህ እያለ መጠየቅ ይኖርበታል፦ ‘በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ለቤተሰቤ የሚያስፈልገውን መሠረታዊ ነገር ለማሟላት ዝግጁ ነኝ? በመንፈሳዊ ነገሮች ረገድ ቤተሰቤን ለመምራትስ ዝግጁ ነኝ? ከሚስቴና ከልጆቼ ጋር በቋሚነት መጽሐፍ ቅዱስን የማጥናት ኃላፊነቴን ለመወጣት ተዘጋጅቻለሁ?’ የአምላክ ቃል ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸውን እነዚህን ኃላፊነቶች የመወጣትን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ይገልጻል።—ዘዳ. 6:6-8፤ ኤፌ. 6:4
በመሆኑም ለማግባት የሚፈልግ አንድ ወጣት በምሳሌ 24:27 ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት በጥንቃቄ ሊያስብበት ይገባል። በተመሳሳይም አንዲት ወጣት ለማግባት ስታስብ ሚስትና እናት መሆን የሚያስከትሏቸውን ኃላፊነቶች ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን ራሷን መጠየቅ ይኖርባታል። ለማግባት የሚያስቡ ሰዎች ወይም በቅርቡ የተጋቡ ባልና ሚስትም ልጆች ስለመውለድ ሲያስቡ ተመሳሳይ ጥያቄዎችን ራሳቸውን ሊጠይቁ ይችላሉ። (ሉቃስ 14:28) የአምላክ ሕዝቦች በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን እንዲህ ያለውን መመሪያ መከተላቸው ብዙ ችግሮችን ማስወገድ እንዲችሉ የሚረዳቸው ከመሆኑም ሌላ አስደሳች የቤተሰብ ሕይወት ለመምራት ያስችላቸዋል።
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
አንድ ወጣት ትዳርን በተመለከተ የትኞቹን ጥያቄዎች ራሱን መጠየቅ ይኖርበታል?