‘ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት’
“ካመሰገነ በኋላ [ቂጣውን] ቆርሶ ‘ይህ ለእናንተ የተሰጠ ሥጋዬ ማለት ነው። ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት’ አለ።”—1 ቆሮ. 11:24
1, 2. ሐዋርያቱ ወደ ኢየሩሳሌም ጉዞ የሚያደርጉበትን ጊዜ አስመልክቶ ምን አስበው ሊሆን ይችላል?
‘ሰማዩ ጥርት ያለ በመሆኑ አዲሷ ጨረቃ ትታያለች። ትናንት ማታ በኢየሩሳሌም የነበሩ ዘበኞችም ጨረቃዋን አይተዋት መሆን አለበት። የሳንሄድሪን ሸንጎ አባላት ይህን ሰምተው አዲስ ወር ማለትም ኒሳን መጀመሩን አውጀዋል። ይህንን ዜና ርቀው ለሚገኙ አካባቢዎች ለማብሰር እሳት በማቀጣጠል ምልክት ስለተሰጠ ወይም መልእክተኞች ስለተላኩ እዚህ ያሉ ሰዎች እንኳ ኒሳን መጀመሩን አውቀዋል። ኢየሱስ ከፋሲካ በፊት ኢየሩሳሌም መድረስ እንደሚፈልግ ጥርጥር የለውም።’
2 ከዮርዳኖስ ማዶ በሚገኘው በፔሪያ ከኢየሱስ ጋር የነበሩ አንዳንድ ሐዋርያት፣ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም የመጨረሻውን ጉዞ ሲያደርግ ከላይ ያለው ሐሳብ ወደ አእምሯቸው መጥቶ ሊሆን ይችላል። (ማቴ. 19:1፤ 20:17, 29፤ ማር. 10:1, 32, 46) የአይሁዳውያኑ ወር ኒሳን የሚጀምርበት ቀን ከታወቀ ከ13 ቀናት በኋላ ፀሐይ ስትጠልቅ ይኸውም ኒሳን 14 ፋሲካ ይከበራል።
3. ክርስቲያኖች ፋሲካ የሚከበርበትን ቀን ማወቅ የሚፈልጉት ለምንድን ነው?
3 የጌታ ራት የሚከበረው ከፋሲካ ጋር በተመሳሳይ ወቅት ነው፤ በዓሉ በ2014 የሚከበረው ሚያዝያ 14 ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ነው። ይህ ዕለት ለእውነተኛ ክርስቲያኖችም ሆነ ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች ልዩ ቀን ነው። ለምን? በ1 ቆሮንቶስ 11:23-25 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጠናል፦ “ኢየሱስ አልፎ በተሰጠበት ሌሊት አንድ ቂጣ አንስቶ ካመሰገነ በኋላ ቆርሶ ‘ይህ ለእናንተ የተሰጠ ሥጋዬ ማለት ነው። ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት’ አለ። ከጽዋው ጋር በተያያዘም እንዲሁ አደረገ።”
4. (ሀ) ከመታሰቢያው በዓል ጋር በተያያዘ የትኞቹ ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ? (ለ) የመታሰቢያው በዓል የሚውለው መቼ እንደሆነ በየዓመቱ የሚወሰነው እንዴት ነው? ( “የ2014 የመታሰቢያ በዓል” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
4 ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ በየዓመቱ እንዲያከብሩት ያዘዘው በዓል ሲከበር መገኘትህ እንደማይቀር ጥርጥር የለውም። ይሁንና አስቀድመህ እነዚህን ጥያቄዎች ልታስብባቸው ትችላለህ፦ ‘ለዚያ ምሽት መዘጋጀት ያለብኝ እንዴት ነው? በዓሉን ለማክበር ምን ነገሮች ያስፈልጋሉ? በዓሉ በሚከበርበት ወቅት ምን ይከናወናል? እንዲሁም ይህ በዓል እና በዓሉ ላይ የሚቀርቡት ነገሮች ለእኔ ምን ትርጉም አላቸው?’
ቂጣውና ወይኑ
5. ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር ለመጨረሻ ጊዜ ፋሲካን ለማክበር ምን ዝግጅት እንዲደረግ አዝዞ ነበር?
5 ኢየሱስ፣ ፋሲካን የሚበሉበትን ክፍል እንዲያዘጋጁ ሐዋርያቱን ሲልካቸው የተለያዩ ጌጦችን በመጠቀም ቤቱን እንዲያስውቡት እየነገራቸው አልነበረም፤ ከዚህ ይልቅ ምቹ፣ ንጹሕ እና ለተጠሩት ሰዎች የሚበቃ ቤት እንዲያዘጋጁ ፈልጎ ነበር። (ማርቆስ 14:12-16ን አንብብ።) ሐዋርያቱ፣ ያልቦካ ቂጣንና ቀይ ወይን ጠጅን ጨምሮ ለበዓሉ የሚያስፈልጉ የተለያዩ ነገሮችን ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል። ኢየሱስ፣ ፋሲካን በልተው ከጨረሱ በኋላ ትኩረቱን በቂጣውና በወይኑ ላይ አደረገ።
6. (ሀ) ኢየሱስ፣ ፋሲካ ከተበላ በኋላ ቂጣውን አስመልክቶ ምን አለ? (ለ) በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚቀርበው ቂጣ ምን ዓይነት ነው?
6 በወቅቱ በቦታው የነበረው ሐዋርያው ማቴዎስ ከጊዜ በኋላ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ኢየሱስ ቂጣ አንስቶ ከባረከ በኋላ ቆረሰው፤ ከዚያም ለደቀ መዛሙርቱ በመስጠት ‘እንኩ፣ ብሉ . . .’ አለ።” (ማቴ. 26:26) ኢየሱስ የተጠቀመበት “ቂጣ” ለፋሲካ የቀረበው ያልቦካ ቂጣ ነበር። (ዘፀ. 12:8፤ ዘዳ. 16:3) ቂጣው የተዘጋጀው ከስንዴ ዱቄትና ከውኃ ብቻ ሲሆን እርሾም ሆነ እንደ ጨው ያሉ ማጣፈጫዎች አልገቡበትም። ከዚህም ሌላ ሊጡ እርሾ ስላልገባበት ቂጣው አልነፋም። ምንም ያልገባበት፣ ደረቅና በቀላሉ ሊቆርራረስ የሚችል ነበር። በዛሬው ጊዜ የመታሰቢያ በዓሉ እየቀረበ ሲመጣ የጉባኤ ሽማግሌዎች ቂጣውን በዚህ መልክ የሚያዘጋጅ አንድ ሰው ይመድባሉ፤ ሊጡ የሚቦካው የስንዴ ዱቄትና ውኃ በመጠቀም ሲሆን ቂጣው ዘይት በስሱ በተቀባ መጋገሪያ ላይ ይጋገራል። (የስንዴ ዱቄት ማግኘት የማይቻል ከሆነ የሩዝ፣ የገብስ፣ የበቆሎ ወይም ተመሳሳይ የሆነ የሌላ እህል ዱቄት መጠቀም ይቻላል።) ማትዛ የተባለው የአይሁዳውያን ቂጣም ለዚህ ዓላማ ሊውል ይችላል፤ ሆኖም ይህ ቂጣ ብቅል፣ እንቁላል ወይም ሽንኩርት ያልገባበት መሆን አለበት።
7. ኢየሱስ የተጠቀመበት ወይን ጠጅ ምን ዓይነት ነበር? በዛሬው ጊዜ በመታሰቢያው በዓል ላይ የምንጠቀመው ምን ዓይነት ወይን ጠጅ ነው?
7 ማቴዎስ አክሎ እንዲህ ብሏል፦ “[ኢየሱስ] ጽዋ አንስቶ ካመሰገነ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ በመስጠት እንዲህ አለ፦ ‘ሁላችሁም ከዚህ ጠጡ።’” (ማቴ. 26:27, 28) ኢየሱስ ያነሳው ጽዋ፣ ቀይ ወይን ጠጅ የያዘ ነበር። (የወይን ፍሬ የሚሰበሰብበት ወቅት ካለፈ ረጅም ጊዜ ስለሆነ መጠጡ የወይን ጭማቂ ሊሆን አይችልም።) እስራኤላውያን በግብፅ የመጀመሪያውን ፋሲካ ሲያከብሩ ወይን ጠጅ እንዲጠቀሙ ባይታዘዙም ኢየሱስ በዓሉን ሲያከብር ይህን መጠጥ መጠቀም ትክክል እንዳልሆነ አልተሰማውም። እንዲያውም የጌታ ራትን ባቋቋመበት ወቅት ተጠቅሞበታል። በመሆኑም ክርስቲያኖች የመታሰቢያ በዓሉን ሲያከብሩ ወይን ጠጅ ይጠቀማሉ። የክርስቶስ ደም ያለውን ዋጋ ከፍ ለማድረግ ምንም ነገር መጨመር እንደማያስፈልግ ሁሉ፣ ለዚህ ዓላማ የሚውለው ወይን ጠጅም ብራንዲ ወይም ሌሎች ማጣፈጫዎች ሊጨመሩበት አይገባም። የመታሰቢያው በዓል ሲከበር ጥቅም ላይ የሚውለው ወይን ጠጅ ቀይና ምንም ነገር ያልተቀላቀለበት ሊሆን ይገባል፤ ቤት ውስጥ የተዘጋጀ ወይን ጠጅ ወይም ምንም ያልተጨመረባቸውን ወይን ጠጆች (ለምሳሌ እንደ ቡዦሌ፣ በርገንዲ ወይም ኪያንቲ ያሉትን) መጠቀም ይቻላል።
ቂጣውና ወይኑ ያላቸው ትርጉም
8. ክርስቲያኖች ቂጣውና ወይኑ ላላቸው ትርጉም ትኩረት የሚሰጡት ለምንድን ነው?
8 ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ሐዋርያት ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ክርስቲያኖችም የጌታ ራትን ማክበር እንደሚጠበቅባቸው በግልጽ ተናግሯል። በቆሮንቶስ ለሚገኙ የእምነት ባልንጀሮቹ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እኔ ከጌታ የተቀበልኩትና ለእናንተም ያስተላለፍኩት ይህ ነው፤ ጌታ ኢየሱስ . . . አንድ ቂጣ አንስቶ ካመሰገነ በኋላ ቆርሶ ‘ይህ ለእናንተ የተሰጠ ሥጋዬ ማለት ነው። ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት’ አለ።” (1 ቆሮ. 11:23, 24) በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ክርስቲያኖችም ከዚህ ጋር በሚስማማ መልኩ ይህን ልዩ በዓል በየዓመቱ የሚያከብሩ ከመሆኑም ሌላ ቂጣውና ወይኑ ላላቸው ትርጉም ትኩረት ይሰጣሉ።
9. አንዳንዶች፣ ኢየሱስ ስለተጠቀመበት ቂጣ ምን ዓይነት የተሳሳተ አመለካከት አላቸው?
9 ክርስቲያን ነን የሚሉ አንዳንድ ሰዎች ‘ኢየሱስ “ይህ ሥጋዬ ነው” ስላለ ቂጣው ተአምራዊ በሆነ መንገድ ቃል በቃል ወደ ኢየሱስ ሥጋ ተለውጧል’ ብለው ያስባሉ። ይሁን እንጂ ይህ ሐሳብ ከእውነታው የራቀ ነው። * ኢየሱስ ይህን በተናገረበት ወቅት የኢየሱስ ሥጋም ሆነ እንዲበሉት የሰጣቸው ያልቦካው ቂጣ በታማኝ ሐዋርያቱ ፊት ነበሩ። ከዚህ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስ በሌሎች ጊዜያት ያደርግ እንደነበረው ሁሉ ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ እየተናገረ ነበር።—ዮሐ. 2:19-21፤ 4:13, 14፤ 10:7፤ 15:1
10. በጌታ ራት ላይ የሚቀርበው ቂጣ ምን ይወክላል?
10 ሐዋርያቱ እንዲበሉት የተሰጣቸው ቂጣ የኢየሱስን አካል የሚወክል ነው። ይሁንና ይህ አካል የትኛው ነው? በአንድ ወቅት የአምላክ አገልጋዮች ቂጣው የሚወክለው “የክርስቶስን አካል” ይኸውም የቅቡዓንን ጉባኤ እንደሆነ ያስቡ ነበር፤ እንዲህ ያሰቡት ኢየሱስ ቂጣውን የቆራረሰው ቢሆንም ከአጥንቶቹ መካከል ግን አንዱም ስላልተሰበረ ነው። (ኤፌ. 4:12፤ ሮም 12:4, 5፤ 1 ቆሮ. 10:16, 17፤ 12:27) ከጊዜ በኋላ ግን ቅዱሳን መጻሕፍትን ሲመረምሩ ቂጣው፣ ለኢየሱስ የተዘጋጀለትን ሰብዓዊ አካል እንደሚያመለክት ተገነዘቡ። ኢየሱስ ተሰቅሎ እስከ መሞት ድረስ ‘በሥጋው መከራ ተቀብሏል።’ ከዚህ አንጻር በጌታ ራት ላይ የሚቀርበው ቂጣ ኢየሱስ ‘ኃጢአታችንን የተሸከመበትን’ ሰብዓዊ አካል ይወክላል።—1 ጴጥ. 2:21-24፤ 4:1፤ ዮሐ. 19:33-36፤ ዕብ. 10:5-7
11, 12. (ሀ) ኢየሱስ ወይኑን አስመልክቶ ምን ብሏል? (ለ) በጌታ ራት ላይ የሚቀርበው ወይን ጠጅ ምን ይወክላል?
11 ይህ ሐሳብ ኢየሱስ በወቅቱ ስለ ወይኑ የተናገረውን ነገር እንድንረዳ ያስችለናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ከጽዋው ጋር በተያያዘም እንዲሁ አደረገ፤ ራት ከበላ በኋላ ‘ይህ ጽዋ በደሜ አማካኝነት የሚመሠረተው አዲሱ ቃል ኪዳን ማለት ነው። . . .’ አለ።” (1 ቆሮ. 11:25) በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ከአዲሱ መደበኛ ትርጉም ጋር በሚመሳሰል መንገድ ይህን ጥቅስ ቃል በቃል “ይህ ጽዋ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው” በማለት ተርጉመውታል። ታዲያ ኢየሱስ በእጁ የያዘው ጽዋ የሚያመለክተው አዲሱን ቃል ኪዳን ነው? አይደለም። “ጽዋው” የሚያመለክተው በውስጡ ያለውን ነገር ይኸውም ወይኑን ነበር። ወይኑ ደግሞ የሚፈስሰውን ደሙን እንደሚያመለክት ወይም እንደሚወክል ኢየሱስ ገልጿል።
12 በማርቆስ ወንጌል ላይ እንደተገለጸው ኢየሱስ “ይህ ለብዙዎች የሚፈስ ‘የቃል ኪዳን ደሜ’ ማለት ነው” በማለት ተናግሯል። (ማር. 14:24) አዎን፣ የኢየሱስ ደም የሚፈስሰው ‘ብዙዎች የኃጢአት ይቅርታ’ እንዲያገኙ ነው። (ማቴ. 26:28) በመሆኑም ቀዩ ወይን ጠጅ የኢየሱስን ደም የሚወክል መሆኑ ተገቢ ነው። በዚህ ደም አማካኝነት ቤዛው ስለተከፈለልን ነፃ መውጣት እንችላለን፤ በሌላ አባባል ‘ለበደላችን ይቅርታ እናገኛለን።’—ኤፌሶን 1:7ን አንብብ።
የክርስቶስን ሞት ማክበር
13. ዓመታዊው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል የሚከበረው እንዴት እንደሆነ ግለጽ።
13 በመታሰቢያው በዓል ላይ የምትገኘው ለመጀመሪያ ጊዜ ከሆነ በዚያ ምን እንደሚፈጸም ልትጠብቅ ትችላለህ? በስብሰባው ላይ የተገኙ ሁሉ ተመችቷቸው በዓሉን እንዲያከብሩ ቦታው ማራኪና ንጹሕ እንደሚሆን መጠበቁ ተገቢ ነው። ቦታውን ለማስዋብ የተወሰኑ አበቦች ሊኖሩ ቢችሉም የተብለጨለጨ ወይም ከልክ በላይ ያሸበረቀ እንዲሆን አይደረግም። ብቃት ያለው አንድ ሽማግሌ፣ ግልጽ በሆነና ክብር በተላበሰ መልኩ ስለ በዓሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ንግግር ይሰጣል። ተናጋሪው፣ የተሰበሰቡት ሁሉ ክርስቶስ ያደረገላቸውን ነገር እንዲያደንቁ በሚያደርግ መልኩ ንግግሩን ያቀርባል። እንዲሁም ኢየሱስ ሕይወት እንድናገኝ ሲል ለእኛ በመሞት ቤዛውን እንደከፈለልን ይገልጻል። (ሮም 5:8-10ን አንብብ።) ተናጋሪው፣ ክርስቲያኖች ስለሚያገኟቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹ ሁለት የተለያዩ ተስፋዎች ያብራራል።
14. በመታሰቢያው በዓል ወቅት በሚቀርበው ንግግር ላይ ስለ የትኞቹ ተስፋዎች ይብራራል?
14 አንደኛው፣ የኢየሱስ ሐዋርያት ያላቸው ዓይነት ተስፋ ይኸውም በሰማይ ከክርስቶስ ጋር የመግዛት ተስፋ ሲሆን ይህን የሚያገኙት የክርስቶስ ተከታዮች በአንጻራዊ ሁኔታ ቁጥራቸው ጥቂት ነው። (ሉቃስ 12:32፤ 22:19, 20፤ ራእይ 14:1) ሌላኛው ደግሞ በዛሬው ጊዜ ያሉ አምላክን በታማኝነት የሚያገለግሉ አብዛኞቹ ታማኝ ክርስቲያኖች የሚያገኙት ተስፋ ነው። እነዚህ ሰዎች እንደገና ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ተዘርግቶላቸዋል። ይህ ተስፋ እውን በሚሆንበት ጊዜ ክርስቲያኖች ከረጅም ጊዜ አንስቶ ሲጸልዩለት የኖሩት ነገር ይፈጸማል፤ የአምላክ ፈቃድ በሰማይ እንደሆነ ሁሉ በምድርም ይሆናል። (ማቴ. 6:10) እንዲሁም በዚያ ወቅት ሰዎች ማብቂያ ለሌለው ጊዜ አስደሳች ሕይወት እንደሚመሩ ቅዱሳን መጻሕፍት ይገልጻሉ።—ኢሳ. 11:6-9፤ 35:5, 6፤ 65:21-23
15, 16. የጌታ ራት በሚከበርበት ወቅት ቂጣው ምን ይደረጋል?
15 ንግግሩ ሊያበቃ ሲቃረብ ተናጋሪው፣ ኢየሱስ ለሐዋርያቱ በሰጠው መመሪያ መሠረት በዓሉን የምናከብርበት ሰዓት እንደደረሰ ይገልጻል። እርሾ ያልገባበት ቂጣና ቀዩ ወይን ጠጅ፣ ከተናጋሪው አጠገብ ባለ ጠረጴዛ ላይ ሊቀመጡ ይችላሉ። ተናጋሪው፣ ኢየሱስ በዓሉን ባቋቋመበት ወቅት ስለተናገረውና ስላደረገው ነገር በሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ላይ ትኩረት እንድናደርግ ይጋብዛል። ለምሳሌ ያህል፣ የማቴዎስ ዘገባ እንዲህ ይላል፦ “ኢየሱስ ቂጣ አንስቶ ከባረከ በኋላ ቆረሰው፤ ከዚያም ለደቀ መዛሙርቱ በመስጠት ‘እንኩ፣ ብሉ። ይህ ሥጋዬ ማለት ነው’ አለ።” (ማቴ. 26:26) ኢየሱስ፣ እርሾ ያልገባበትን ቂጣ በግራና በቀኙ ላሉት ሐዋርያት ለማከፋፈል ሲል ቆራርሶታል። በተመሳሳይም ሚያዝያ 14 በሚከበረው በዓል ላይ እርሾ ያልገባበት የተቆራረሰ ቂጣ ሳህን ላይ ተቀምጦ ታያለህ።
16 ቂጣው በሚዞርበት ወቅት ጊዜ እንዳይባክን በቂ ሳህኖች እንዲኖሩ ይደረጋል። ቂጣው ሲዞር የተለየ የአምልኮ ሥርዓት አይከናወንም። በመጀመሪያ አጭር ጸሎት ይቀርባል፤ ከዚያም፣ ሁኔታው እንደየአካባቢው ሊለያይ ቢችልም ቂጣ የያዙት ሳህኖች ሥርዓታማ በሆነ መንገድ እንዲዞሩ ይደረጋል። በ2013 ይህ በዓል በተከበረበት ወቅት በአብዛኞቹ ጉባኤዎች ውስጥ ከቂጣው የተካፈሉት ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ነበር። በዚህ ዓመትም በመታሰቢያው በዓል ላይ ከቂጣው የሚካፈሉት ሰዎች ቁጥር ጥቂት ሊሆን ምናልባትም የሚካፈል ሰው ላይኖር ይችላል።
17. በመታሰቢያው በዓል ወቅት ኢየሱስ ወይን ጠጁን አስመልክቶ የሰጠው መመሪያ ተግባራዊ የሚሆነው እንዴት ነው?
17 ከዚያም ተናጋሪው፣ ማቴዎስ በመቀጠል በተናገረው በሚከተለው ሐሳብ ላይ ትኩረት ያደርጋል፦ “[ኢየሱስ] ጽዋ አንስቶ ካመሰገነ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ በመስጠት እንዲህ አለ፦ ‘ሁላችሁም ከዚህ ጠጡ፤ ይህ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ “የቃል ኪዳን ደሜ” ማለት ነው።’” (ማቴ. 26:27, 28) ከዚህ መመሪያ ጋር በሚስማማ መልኩ ሌላ ጸሎት ከቀረበ በኋላ ቀይ ወይን ጠጅ የያዙት ‘ጽዋዎች’ በሁሉም ፊት እንዲዞሩ ይደረጋል።
18. ከቂጣውና ከወይኑ የሚካፈሉት ጥቂቶች ቢሆኑም ሁላችንም በበዓሉ ላይ መገኘታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
18 በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚገኙት አብዛኞቹ ሰዎች ከቂጣውና ከወይን ጠጁ አይካፈሉም፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ መካፈል የሚችሉት በሰማይ ባለው መንግሥቱ ከእሱ ጋር የሚገዙት ብቻ እንደሆኑ ጠቁሟል። (ሉቃስ 22:28-30ን አንብብ፤ 2 ጢሞ. 4:18) በበዓሉ ላይ የሚገኙት ሌሎች ሰዎች ግን ከቂጣውና ከወይን ጠጁ ባይካፈሉም ፕሮግራሙን በአክብሮት ይከታተላሉ። ያም ቢሆን በጌታ ራት ላይ መገኘታቸው አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማቸዋል፤ ምክንያቱም እንዲህ ማድረጋቸው የኢየሱስን መሥዋዕት ከፍ አድርገው እንደሚመለከቱት ያሳያል። በመታሰቢያው በዓል ላይ ተገኝተው የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት በሚያስገኛቸው በረከቶች ላይ ያሰላስላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በቅርቡ ከሚመጣው ‘ታላቅ መከራ’ በሕይወት ከሚያልፉት “እጅግ ብዙ ሕዝብ” መካከል የመቆጠር መብት አላቸው። እነዚህ የይሖዋ አምላኪዎች ‘ልብሳቸውን በበጉ ደም አጥበው ነጭ አድርገውታል።’—ራእይ 7:9, 14-17
19. ለጌታ ራት ለመዘጋጀትና ከበዓሉ ጥቅም ለማግኘት ምን ማድረግ ትችላለህ?
19 በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ልዩ በዓል ለማክበር ዝግጅት ያደርጋሉ። በዓሉ ከመከበሩ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች በበዓሉ ላይ እንዲገኙ መጋበዝ እንጀምራለን። ከዚህም በተጨማሪ በዓሉ ከመድረሱ በፊት ባሉት ቀናት አብዛኞቻችን ኢየሱስ በ33 ዓ.ም. ከተከበረው በዓል በፊት ባሉት ቀናት ስላደረጋቸው ነገሮችና በዕለቱ ስለተከናወኑት ነገሮች የሚገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን እናነብባለን። በበዓሉ ላይ ለመገኘት ፕሮግራማችንን እናስተካክላለን። ወደ በዓሉ የሚመጡ እንግዶችን መቀበልና ሙሉውን ፕሮግራም መከታተል እንድንችል ከመክፈቻው መዝሙርና ጸሎት በፊት ቀደም ብለን መድረሳችን የተገባ ነው። የጉባኤው አባላትም ሆኑ እንግዶች፣ በስብሰባው ላይ የተገኙ ሁሉ ንግግሩ ሲቀርብ መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ገልጠው መከታተላቸው በጣም ይጠቅማቸዋል። ከሁሉ በላይ ደግሞ በመታሰቢያው በዓል ላይ መገኘታችን ለኢየሱስ መሥዋዕት ልባዊ አድናቆት እንዳለን የሚያሳይ ከመሆኑም ሌላ “ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት” በማለት ኢየሱስ የሰጠውን መመሪያ እንደምንታዘዝ ያሳያል።—1 ቆሮ. 11:24
^ አን.9 ሃይንሪሽ ማየር የተባሉት ጀርመናዊ ምሁር እንዲህ ብለዋል፦ “በወቅቱ የኢየሱስ ሥጋ ገና አልተቆረሰም (ኢየሱስ ገና አልሞተም)፤ ደሙም ቢሆን ገና አልፈሰሰም፤ . . . በበዓሉ ላይ የተገኙት እንግዶች [ሐዋርያቱ] ይህን ስላዩ ቃል በቃል የጌታን ሥጋና ደም እየበሉና እየጠጡ እንደሆነ አድርገው ሊያስቡ አይችሉም፤ [በመሆኑም] ኢየሱስ፣ በቀላል ቋንቋ የተናገረውን ይህን ሐሳብ [ተከታዮቹ] በተሳሳተ መንገድ ሊረዱት ይችላሉ ብሎ እንዳላሰበ ግልጽ ነው።”