እምነት በማሳየት ረገድ ሙሴን ምሰሉ
“ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን ሴት ልጅ፣ ልጅ ተብሎ ለመጠራት በእምነት እምቢ አለ።”—ዕብ. 11:24
1, 2. (ሀ) ሙሴ 40 ዓመት ሲሆነው ምን ውሳኔ አደረገ? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።) (ለ) ሙሴ ከአምላክ ሕዝቦች ጋር መንገላታትን የመረጠው ለምንድን ነው?
ሙሴ በግብፅ ሊያገኝ የሚችላቸውን ነገሮች ጠንቅቆ ያውቃል። ሀብታሞች የሚኖሩባቸውን የተንጣለሉ ቪላ ቤቶች የማየት አጋጣሚ ነበረው። እሱም ራሱ የንጉሣውያን ቤተሰብ አባል ነበር። በዚያ ላይ “የግብፃውያንን ጥበብ ሁሉ” ተምሯል፤ ይህም ሥነ ጥበብን፣ ሥነ ፈለክን፣ ሒሳብንና ሌሎች ሳይንሶችን ሳይጨምር አይቀርም። (ሥራ 7:22) አንድ ግብፃዊ ከመመኘት ውጭ ሊያገኘው የማይችለውን ሀብት፣ ሥልጣንና ሌሎች መብቶች ማግኘት ለእሱ ቀላል ነበር!
2 ይሁን እንጂ ሙሴ 40 ዓመት ሲሆነው አሳዳጊዎቹ የሆኑትን የግብፃውያን ንጉሣዊ ቤተሰብ ግራ ሊያጋባ የሚችል አንድ ውሳኔ አደረገ። ሙሴ የነበረውን ልዩ አጋጣሚ ተወ፤ ይህን ያደረገው አንድ መካከለኛ ኑሮ ያለው ግብፃዊ የነበረውን ዓይነት ሕይወት ለመኖር እንኳ አልነበረም፤ ከዚህ ይልቅ ባሪያ ከሆኑ ሕዝቦች ጋር መኖርን መረጠ! ለምን? እምነት ስለነበረው ነው። (ዕብራውያን 11:24-26ን አንብብ።) ሙሴ በዓይኑ ከሚያየው ባሻገር ያለውን ነገር በእምነት መመልከት ችሎ ነበር። መንፈሳዊ ሰው ስለነበረ ‘በማይታየው’ ማለትም በይሖዋ ላይ እምነት ነበረው፤ እንዲሁም እሱ የገባቸው ተስፋዎች እንደሚፈጸሙ እርግጠኛ ነበር።—ዕብ. 11:27
3. በዚህ የጥናት ርዕስ ላይ ለየትኞቹ ሦስት ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን?
3 እኛም በዓይናችን ከምናየው ባሻገር ያለውን ነገር መመልከት ይኖርብናል። “እምነት ያላቸው ዓይነት ሰዎች” መሆን ይገባናል። (ዕብ. 10:38, 39) በመሆኑም እምነታችንን ለማጠናከር እንዲረዳን በዕብራውያን 11:24-26 ላይ ሙሴን በተመለከተ የተጠቀሱትን ሐሳቦች እንመረምራለን። የጥቅሱን ሐሳብ ስንመረምር ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን፦ ሙሴ የነበረው እምነት በሥጋዊ ምኞቶች እንዳይሸነፍ የረዳው እንዴት ነው? ነቀፋ ቢደርስበትም እምነት ማዳበሩ የአገልግሎት መብቱን ከፍ አድርጎ እንዲመለከት የረዳው እንዴት ነው? ሙሴ “የሚከፈለውን ወሮታ በትኩረት” የተመለከተውስ ለምንድን ነው?
በሥጋዊ ምኞቶች አልተሸነፈም
4. ሙሴ ‘በኃጢአት ስለሚገኝ ደስታ’ ምን ነገር ማስተዋል ችሎ ነበር?
4 ሙሴ ‘በኃጢአት የሚገኘው ደስታ ጊዜያዊ’ መሆኑን በእምነት ዓይኑ ማስተዋል ችሎ ነበር። በዘመኑ የነበሩ አንዳንዶች እንደዚህ አይሰማቸው ይሆናል፤ ምክንያቱም ግብፅ በጣዖት አምልኮና በመናፍስታዊ ድርጊት የተሞላች ብትሆንም የዓለም ኃያል መንግሥት ነበረች፤ በሌላ በኩል ደግሞ የይሖዋ ሕዝቦች በባርነት እየማቀቁ ነበር! ያም ቢሆን ሙሴ፣ አምላክ ሁኔታውን መለወጥ እንደሚችል ያውቅ ነበር። የራሳቸውን ምኞት ለመፈጸም የሚሯሯጡ ሰዎች የተሳካላቸው ቢመስሉም ሙሴ ክፉዎች መጥፋታቸው እንደማይቀር እምነት ነበረው። በመሆኑም ‘በኃጢአት የሚገኝ ጊዜያዊ ደስታ’ አላጓጓውም።
5. ‘በኃጢአት በሚገኝ ጊዜያዊ ደስታ’ እንዳንሸነፍ ምን ሊረዳን ይችላል?
5 ‘በኃጢአት በሚገኝ ጊዜያዊ ደስታ’ እንዳትሸነፍ ምን ሊረዳህ ይችላል? በኃጢአት የሚገኝ ደስታ ቅጽበታዊ መሆኑን አትርሳ። “ዓለምም ሆነ ምኞቱ በማለፍ ላይ” እንደሆኑ በእምነት ዓይንህ ይታይህ። (1 ዮሐ. 2:15-17) ንስሐ ያልገቡ ኃጢአተኞች የወደፊት ዕጣቸው ምን እንደሆነ አሰላስል። “በሚያዳልጥ ስፍራ” የቆሙ ያህል ነው፤ ‘ፈጽመው ይወድማሉ!’ (መዝ. 73:18, 19) ኃጢአት ለመፈጸም ስትፈተን ‘ወደፊት ምን እንዲያጋጥመኝ ነው የምፈልገው?’ በማለት ራስህን ጠይቅ።
6. (ሀ) ሙሴ “የፈርዖን ሴት ልጅ፣ ልጅ ተብሎ ለመጠራት” ያልፈለገው ለምንድን ነው? (ለ) ሙሴ ያደረገው ውሳኔ ትክክል ነበር የምትለው ለምንድን ነው?
6 ሙሴ የነበረው እምነት በሥራ መስክ ምርጫው ላይ ለውጥ አምጥቷል። “ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን ሴት ልጅ፣ ልጅ ተብሎ ለመጠራት በእምነት እምቢ አለ።” (ዕብ. 11:24) ሙሴ፣ በግብፅ ቤተ መንግሥት ውስጥ ሆኖ አምላክን ማገልገል እንደሚችልና በዚያ በሚያገኘው ሀብትና ሥልጣን እስራኤላውያን ወንድሞቹን መርዳት እንደሚችል አድርጎ አላሰበም። ከዚህ ይልቅ ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር ስላለው በፍጹም ልቡ፣ ነፍሱና ኃይሉ እሱን ለማገልገል ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ ነበር። (ዘዳ. 6:5) ሙሴ ያደረገው ይህ ውሳኔ ከብዙ ሐዘን ጠብቆታል። ምክንያቱም ትቶት የወጣው አብዛኛው የግብፃውያን ሀብት ብዙም ሳይቆይ በእስራኤላውያን ተወስዷል! (ዘፀ. 12:35, 36) ፈርዖንም ቢሆን ውርደት የተከናነበ ከመሆኑም ሌላ በመጨረሻ ሕይወቱን አጥቷል። (መዝ. 136:15) በሌላ በኩል ግን ሙሴ ሕይወቱን ማትረፍ የቻለ ሲሆን አምላክ መላውን ብሔር ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመምራት ተጠቅሞበታል። በመሆኑም ትርጉም ያለው ሕይወት መምራት ችሏል።
7. (ሀ) በማቴዎስ 6:19-21 መሠረት ጊዜያዊ ጥቅም ከሚያስገኝልን ነገር አሻግረን መመልከት ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) በቁሳዊና በመንፈሳዊ ሀብት መካከል ያለውን ልዩነት የሚያሳይ አንድ ተሞክሮ ተናገር።
7 ወጣት የይሖዋ አገልጋይ ነህ? ከሆነ እምነት ማዳበርህ የሥራ መስክ በመምረጥ ረገድ ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው? ስለ ወደፊቱ ጊዜ እቅድ ማውጣትህ አስተዋይ መሆንህን ያሳያል። ይሁን እንጂ ትኩረትህ ያረፈው ጊዜያዊ ጥቅም የሚያስገኝ ሀብት በማከማቸት ላይ ነው? ወይስ አምላክ በገባው ቃል ላይ ያለህ እምነት ዘላለማዊ ጥቅም የሚያስገኝ ሀብት እንድታከማች ይረዳሃል? (ማቴዎስ 6:19-21ን አንብብ።) በባሌ ዳንስ ተሰጥኦ ያላት ሶፊ የተባለች ተወዛዋዥ በአንድ ወቅት ይህ ምርጫ ተደቅኖባት ነበር። በመላው ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኙ የባሌ ዳንስ ተቋማት ውስጥ ነፃ የትምህርት ዕድልና በሙያዋ ትልቅ ደረጃ ላይ ለመድረስ የሚያስችላት አጋጣሚ አግኝታ ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “ተወዳጅ መሆን የሚያጓጓ ነው። እንዲያውም ከእኩዮቼ የተሻልኩ እንደሆንኩ ተሰምቶኝ ነበር። ግን ደስታ አልነበረኝም።” ከዚያም ሶፊ የወጣቶች ጥያቄ—ሕይወቴን እንዴት ብጠቀምበት ይሻላል? * የተባለውን ቪዲዮ ተመለከተች። “ዓለም ስኬትና ታዋቂነት የሰጠኝ ለይሖዋ የማቀርበውን የሙሉ ልብ አምልኮ መሥዋዕት አድርጌ እንደሆነ ተገነዘብኩ” ብላለች። “በመሆኑም ወደ ይሖዋ አጥብቄ ጸለይኩ። ከዚያም የተወዛዋዥነት ሙያዬን ተውኩ።” ሶፊ ይህን ውሳኔ በማድረጓ ምን ይሰማታል? እንዲህ ብላለች፦ “የቀድሞ ሕይወቴ ምንም አያጓጓኝም። አሁን መቶ በመቶ ደስተኛ ነኝ። ከባለቤቴ ጋር አቅኚ ሆነን እያገለገልን ነው። ታዋቂ አይደለንም፤ በቁሳዊም ቢሆን ያለን ነገር በጣም ጥቂት ነው። ይሁን እንጂ ይሖዋን ይዘናል፤ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችና መንፈሳዊ ግቦች አሉን። በመሆኑም ምንም የሚቆጨኝ ነገር የለም።”
8. አንድ ወጣት ሕይወቱን ስለሚጠቀምበት መንገድ ውሳኔ ሲያደርግ የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ሊረዳው ይችላል?
8 ይሖዋ፣ ለአንተ ከሁሉ የተሻለውን ነገር ያውቃል። ሙሴ እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? አምላክህን እግዚአብሔርን እንድትፈራው፣ በመንገዶቹ ሁሉ እንድትሄድ፣ እንድትወደው፣ በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ እንድታገለግለው፣ መልካም እንዲሆንልህና ዛሬ እኔ የምሰጥህን ትእዛዞችና ሥርዐቶች እንድትጠብቅ አይደለምን?” (ዘዳ. 10:12, 13) ይሖዋን እንድትወደውና ‘በፍጹም ልብህና በፍጹም ነፍስህ’ እሱን እንድታገለግለው የሚያስችልህን የሥራ መስክ ገና ወጣት ሳለህ ምረጥ። እንዲህ ዓይነቱ ውሳኔ ‘መልካም እንደሚሆንልህ’ ወይም ጥሩ ውጤት እንደሚያስገኝልህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።
የአገልግሎት መብቱን ከፍ አድርጎ ተመልክቷል
9. ሙሴ የተሰጠውን ተልዕኮ መወጣት ከባድ እንዲሆንበት የሚያደርገው ምን ሊሆን ይችላል? አብራራ።
9 ሙሴ “ቅቡዕ ሆኖ የሚደርስበት ነቀፋ በግብፅ ከሚገኝ ውድ ሀብት የላቀ እንደሆነ” ተገንዝቦ ነበር። (ዕብ. 11:26) ሙሴ “ቅቡዕ” የተባለው እስራኤላውያንን ከግብፅ እንዲያወጣ ይሖዋ ስለመረጠው ነው። ሙሴ፣ ይህን ተልዕኮ መወጣት ቀላል እንዳልሆነ አልፎ ተርፎም “ነቀፋ” እንደሚያስከትልበት ያውቅ ነበር። ኃላፊነቱን ከመቀበሉ በፊት አንድ እስራኤላዊ “አንተን በእኛ ላይ ገዥና ዳኛ ማን አደረገህ?” በማለት በንቀት ተናግሮት ነበር። (ዘፀ. 2:13, 14) ከጊዜ በኋላ ደግሞ ሙሴ ራሱ “ፈርዖን እንዴት ይሰማኛል?” በማለት ይሖዋን ጠይቆት ነበር። (ዘፀ. 6:12) ሙሴ፣ የሚደርስበትን ነቀፋ ለመቋቋም የሚያስችለውን ዝግጅት ለማድረግ ስለፈለገ የተሰማውን ፍርሃትና ጭንቀት ለይሖዋ ገልጾለት ነበር። ታዲያ ሙሴ ከባድ የሆነውን ተልዕኮ እንዲወጣ ይሖዋ የረዳው እንዴት ነው?
10. ሙሴ ተልዕኮውን እንዲወጣ ይሖዋ ያስታጠቀው እንዴት ነው?
10 በመጀመሪያ፣ ይሖዋ “እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ” በማለት ለሙሴ አረጋገጠለት። (ዘፀ. 3:12) በሁለተኛ ደረጃ ይሖዋ፣ የስሙ ትርጉም ካሉት ገጽታዎች አንዱ የሆነውን ይኸውም “መሆን የምፈልገውን እሆናለሁ” * የሚለውን መግለጫ በመንገር የመተማመን መንፈስ እንዲያድርበት አደረገ። (ዘፀ. 3:14 NW) በሦስተኛ ደረጃ፣ ሙሴ በአምላክ የተላከ መሆኑን የሚያረጋግጥ ተአምር ለመሥራት የሚያስችል ኃይል ሰጠው። (ዘፀ. 4:2-5) በአራተኛ ደረጃ ደግሞ ተልዕኮውን በመወጣት ረገድ እንዲያግዘው አሮንን አጋርና ቃል አቀባይ አድርጎ ሰጠው። (ዘፀ. 4:14-16) ሙሴ፣ አምላክ ለአገልጋዮቹ ምንም ዓይነት ተልዕኮ ሲሰጥ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት እንደሚያስታጥቃቸው እርግጠኛ ነበር፤ በመሆኑም በሕይወቱ መገባደጃ ላይ የእሱ ተተኪ ለሆነው ለኢያሱ በልበ ሙሉነት እንዲህ ብሎታል፦ “እግዚአብሔር ራሱ በፊትህ ይሄዳል፤ ከአንተም ጋር ይሆናል፤ ፈጽሞ አይለይህም፤ አይተውህምም፤ አትፍራ፤ ተስፋም አትቍረጥ።”—ዘዳ. 31:8
11. ሙሴ የአገልግሎት መብቱን ከፍ አድርጎ የተመለከተው ለምንድን ነው?
11 ሙሴ ከይሖዋ ያገኘው እርዳታ ተፈታታኝ የነበረውን ተልዕኮውን “በግብፅ ከሚገኝ ውድ ሀብት የላቀ እንደሆነ” አድርጎ እንዲመለከት አስችሎታል፤ ላገኘው መብት ከፍተኛ ቦታ እንደሚሰጥ በዚህ መንገድ አሳይቷል። ደግሞስ ፈርዖንን ማገልገል ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ከማገልገል ጋር እንዴት ሊወዳደር ይችላል? የግብፅ መስፍን መሆን የይሖዋ “ቅቡዕ” ከመሆን ጋር ሲነጻጸር ምን ቦታ አለው? ሙሴ የአገልግሎት መብቱን ከፍ አድርጎ በመመልከቱ ተባርኳል። ከይሖዋ ጋር ልዩ የሆነ ዝምድና የነበረው ሲሆን እስራኤላውያንን ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲመራ “አስፈሪ ተግባር” እንዲፈጽም ይሖዋ አስችሎታል።—ዘዳ. 34:10-12
12. ከፍ አድርገን ልንመለከታቸው የሚገቡ ይሖዋ የሰጠን መብቶች የትኞቹ ናቸው?
12 እኛም ተልዕኮ ተሰጥቶናል። ይሖዋ ለሐዋርያው ጳውሎስና ለሌሎች እንዳደረገው ሁሉ እኛንም በልጁ በኩል ለአገልግሎት ሾሞናል። (1 ጢሞቴዎስ 1:12-14ን አንብብ።) ሁላችንም ምሥራቹን የማወጅ መብት አግኝተናል። (ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20) አንዳንዶች በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ይካፈላሉ። የጎለመሱ ወንድሞች ደግሞ የጉባኤ አገልጋዮችና ሽማግሌዎች በመሆን በጉባኤ ውስጥ ሌሎችን ያገለግላሉ። ይሁን እንጂ፣ አማኝ ያልሆኑ ዘመዶችህና ሌሎች ሰዎች እንዲህ ያሉ መብቶች ያን ያህል ቦታ የሚሰጣቸው እንዳልሆኑ ሊናገሩ አልፎ ተርፎም የራስህን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግህ ሊነቅፉህ ይችላሉ። (ማቴ. 10:34-37) እነሱ ተስፋ እንዲያስቆርጡህ የምትፈቅድ ከሆነ መሥዋዕት መክፈልህ ተገቢ ስለ መሆኑ ወይም ኃላፊነቱን መወጣት ስለ መቻልህ መጠራጠር ልትጀምር ትችላለህ። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ካጋጠመህ እምነት እንድትጸና ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው?
13. ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነቶቻችንን መወጣት እንድንችል ይሖዋ የሚያስታጥቀን እንዴት ነው?
13 ይሖዋ እንዲረዳህ በእምነት ጠይቀው። የሚሰማህን ፍርሃትና ጭንቀት ንገረው። ደግሞም ተልዕኮውን የሰጠህ ይሖዋ ራሱ ነው፤ በመሆኑም እንዲሳካልህ ይረዳሃል። እንዴት? ሙሴን በረዳበት መንገድ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ይሖዋ “አበረታሃለሁ፤ እረዳሃለሁ፤ በጽድቄም ቀኝ እጄ ደግፌ እይዝሃለሁ” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶሃል። (ኢሳ. 41:10) በሁለተኛ ደረጃ፣ “የተናገርሁትን አደርጋለሁ፤ ያቀድሁትን እፈጽማለሁ” በማለት እሱ የሰጣቸው ተስፋዎች እምነት የሚጣልባቸው እንደሆኑ ገልጾልሃል። (ኢሳ. 46:11) በሦስተኛ ደረጃ፣ አገልግሎትህን መፈጸም እንድትችል ‘ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነ ኃይል’ ይሰጥሃል። (2 ቆሮ. 4:7) በአራተኛ ደረጃ ደግሞ አሳቢ የሆነው አባታችን ‘እርስ በርስ የሚጽናኑና የሚተናነጹ’ እውነተኛ አምላኪዎችን ያቀፈ ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር ሰጥቶሃል፤ ይህም በተሰጠህ ኃላፊነት እንድትጸና ያስችልሃል። (1 ተሰ. 5:11) ይሖዋ፣ ኃላፊነትህን እንድትወጣ ስላስታጠቀህ በእሱ ላይ ያለህ እምነት እያደገ ይሄዳል፤ ይህም እሱን ከማገልገል ጋር በተያያዘ ያገኘሃቸውን መብቶች ከየትኛውም ምድራዊ ሀብት ይበልጥ ከፍ አድርገህ እንድትመለከት ይረዳሃል።
‘የሚከፈለውን ወሮታ በትኩረት ተመልክቷል’
14. ሙሴ ሽልማቱን እንደሚያገኝ እርግጠኛ የነበረው ለምንድን ነው?
14 ሙሴ ‘የሚከፈለውን ወሮታ በትኩረት ተመልክቷል።’ (ዕብ. 11:26) ስለ ወደፊቱ ጊዜ ያለው እውቀት በአመለካከቱ ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል፤ እርግጥ ነው፣ በወቅቱ የነበረው እውቀት ውስን ነበር። እንደ ቅድመ አያቱ አብርሃም ሁሉ ሙሴም ይሖዋ የሞቱትን እንደሚያስነሳ ሙሉ እምነት ነበረው። (ሉቃስ 20:37, 38፤ ዕብ. 11:17-19) ሙሴ ወደፊት ስለሚያገኛቸው በረከቶች ተስፋ ማድረጉ በስደት ያሳለፋቸው 40 ዓመታትና በምድረ በዳ የቆየባቸው 40 ዓመታት በከንቱ እንዳለፉ አድርጎ እንዳያስብ ረድቶታል። ይሖዋ ቃል የገባቸው ተስፋዎች እንዴት እንደሚፈጸሙ በዝርዝር ባያውቅም የማይታየውን ሽልማቱን በእምነት ዓይን መመልከት ችሏል።
15, 16. (ሀ) በምናገኘው ወሮታ ላይ ትኩረት ማድረጋችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በመንግሥቱ አገዛዝ ሥር በጉጉት የምትጠብቃቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?
15 አንተስ ‘የሚከፈልህን ወሮታ በትኩረት ትመለከታለህ?’ እኛም ልክ እንደ ሙሴ አምላክ ቃል ስለገባቸው ተስፋዎች የተሟላ እውቀት የለንም። ለምሳሌ ያህል፣ ታላቁ መከራ የሚጀምርበት “የተወሰነው ጊዜ መቼ እንደሆነ” አናውቅም። (ማር. 13:32, 33) ያም ቢሆን፣ ወደፊት ስለምትመጣው ገነት ከሙሴ የተሻለ እውቀት አለን። ዝርዝር ጉዳዮችን ባናውቅም እንኳ ‘በትኩረት ልንመለከታቸው’ የምንችላቸው በአምላክ መንግሥት ሥር የሚፈጸሙ ብዙ ተስፋዎች አሉ። አዲሱ ዓለም በዓይነ ሕሊናችን ፍንትው ብሎ የሚታየን ከሆነ ለአምላክ መንግሥት ቅድሚያ ለመስጠት እንነሳሳለን። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? እስቲ ይህንን አስብ፦ ስለ አንድ ቤት በቂ እውቀት ሳይኖርህ ቤቱን ለመግዛት ትወስናለህ? እንዲህ እንደማታደርግ የታወቀ ነው! በተመሳሳይም ግልጽ ሆኖ የማይታየንን ነገር ተስፋ በማድረግ ሕይወታችንን ማባከን አንፈልግም። በአምላክ አገዛዝ ሥር የሚኖረው ሕይወት ጥርት ባለ መንገድ በእምነት ዓይናችን ሊታየን ይገባል።
16 በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ስለሚኖረው ሕይወት ጥርት ያለ እይታ እንዲኖርህ ከፈለግክ ራስህን በገነት ውስጥ እንዳለህ አድርገህ በማሰብ በዚያ የሚኖርህን ሕይወት ‘በትኩረት ተመልከት።’ ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናህ ሳል። ለምሳሌ ያህል፣ በቅደመ ክርስትና ዘመን ስለኖሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪኮች ስታጠና፣ ከሞት ሲነሱ ምን ጥያቄ ልትጠይቃቸው እንደምትችል አስብ። በመጨረሻው ዘመን ስላሳለፍከው ሕይወት ምን ጥያቄ ሊያቀርቡልህ እንደሚችሉ ገምት። በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ከኖሩ ቅድመ አያቶችህ ጋር ስትገናኝ እንዲሁም አምላክ ስላደረገላቸው ነገር ስታስተምራቸው ምን ያህል ልትደሰት እንደምትችል ይታይህ። መፈራራት በሌለበት ሁኔታ የተለያዩ የዱር እንስሳትን ቀርበህ በመመልከት ስለ እነሱ መማርህ የሚፈጥረውን የደስታ ስሜት ለማሰብ ሞክር። ወደ ፍጽምና እየተጠጋህ ስትመጣ ከይሖዋ ጋር ያለህ ዝምድና ምን ያህል የቀረበ እንደሚሆን አስብ።
17. የማይታየው ወሮታችን በዓይነ ሕሊናችን ግልጽ ሆኖ እንዲታየን ማድረጋችን የሚረዳን እንዴት ነው?
17 የማይታየው ወሮታችን በዓይነ ሕሊናችን ግልጽ ሆኖ እንዲታየን ማድረጋችን በያዝነው ጎዳና እንድንጸና፣ ደስተኞች እንድንሆንና አስተማማኝ የሆነውን የወደፊት ሕይወት ግምት ውስጥ ያስገባ ውሳኔ እንድናደርግ ይረዳናል። ጳውሎስ ለቅቡዓን ክርስቲያኖች “የማናየውን ነገር ተስፋ የምናደርግ ከሆነ . . . ጸንተን እንጠባበቀዋለን” በማለት ጽፏል። (ሮም 8:25) በመሠረታዊ ሥርዓት ደረጃ ይህ ሐሳብ የዘላለም ሕይወት ተስፋ ላላቸው ለሁሉም ክርስቲያኖች ይሠራል። ሽልማታችንን ገና ያላገኘን ቢሆንም እምነታችን ጠንካራ ከሆነ ‘የሚከፈለንን ወሮታ’ በትዕግሥት እንጠባበቃለን። ልክ እንደ ሙሴ፣ በይሖዋ አገልግሎት የምናሳልፋቸው ዓመታት እንደባከኑ አድርገን አንቆጥራቸውም። ከዚህ ይልቅ፣ ‘የሚታዩት ነገሮች ጊዜያዊ፣ የማይታዩት ነገሮች ግን ዘላለማዊ’ እንደሆኑ እርግጠኞች ነን።—2 ቆሮንቶስ 4:16-18ን አንብብ።
18, 19. (ሀ) እምነታችንን ጠብቀን ለመኖር ተጋድሎ ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?
18 እምነት ‘የማይታዩት እውነተኛ ነገሮች መኖራቸውን የሚያሳየው ተጨባጭ ማስረጃ’ በግልጽ እንዲታየን ያስችለናል። (ዕብ. 11:1) ሥጋዊ ሰው፣ ይሖዋን ማገልገል ምን ያህል ውድ ዋጋ እንዳለው አይታየውም። ውድ የሆኑት መንፈሳዊ ሀብቶች ለዚህ ሰው “ሞኝነት” ናቸው። (1 ቆሮ. 2:14) እኛ ግን ዓለም ማየት የማይችላቸውን ነገሮች ይኸውም በገነት ውስጥ የሚኖረውን ሕይወትና የሙታን ትንሣኤን ለማየት ተስፋ እናደርጋለን። ጳውሎስን “ለፍላፊ” በማለት ይጠሩት እንደነበሩት በዘመኑ የነበሩ ፈላስፎች ሁሉ በዛሬው ጊዜም ብዙ ሰዎች የምንሰብከው ተስፋ ፈጽሞ የማይፈጸም እንደሆነ አድርገው ይቆጥሩታል።—ሥራ 17:18
19 የምንኖረው እምነት የለሽ በሆነ ዓለም ውስጥ ስለሆነ እምነታችንን ጠብቀን ለመኖር ተጋድሎ ማድረግ አለብን። በመሆኑም “እምነትህ እንዳይጠፋ” ለይሖዋ ምልጃ አቅርብ። (ሉቃስ 22:32) ኃጢአት መሥራት የሚያስከትለው መዘዝ፣ ይሖዋን ማገልገል ያለው የላቀ ዋጋ እንዲሁም ወደፊት የምታገኘው የዘላለም ሕይወት ተስፋ ምንጊዜም ግልጽ ሆኖ ይታይህ። ሙሴ እምነት ማዳበሩ ከእነዚህም የበለጠ ነገር እንዲታየው አስችሎታል። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እምነቱ “የማይታየውን” አምላክ እንዲያይ የረዳው እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን።—ዕብ. 11:27