“የማይታየው” አምላክ ይታይሃል?
“የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ በጽናት ቀጥሏል።”—ዕብ. 11:27
1, 2. (ሀ) ሙሴ የነበረበት ሁኔታ አደገኛ ይመስል የነበረው ለምን እንደሆነ አብራራ። (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።) (ለ) ሙሴ የንጉሡን ቁጣ ያልፈራው ለምንድን ነው?
ፈርዖን አስፈሪ ንጉሥ ከመሆኑም ሌላ ለግብፃውያን እንደ አምላክ ነበር። አንድ መጽሐፍ እንደተናገረው ፈርዖን በግብፃውያን ዘንድ “በምድር ላይ ካሉ ፍጥረታት ሁሉ በጥበብና በኃይል የሚተካከለው እንደሌለ” ይታሰብ ነበር። ፈርዖን በሕዝቡ ዘንድ ፍርሃት ለማሳደር ሲል ለመንደፍ የተዘጋጀ የእባብ ምስል ያለበት ዘውድ ያደርጋል፤ ይህም የንጉሡ ጠላቶች በፍጥነት እንደሚደመሰሱ የሚያሳይ ምልክት ነበር። በመሆኑም ይሖዋ “ሕዝቤን፣ የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ ምድር እንድታወጣቸው ወደ ፈርዖን እልክሃለሁ” በማለት ተልዕኮ ሲሰጠው ሙሴ ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል መገመት ትችላለህ።—ዘፀ. 3:10
2 ሙሴ ወደ ግብፅ በመሄድ የአምላክን መልእክት አወጀ፤ ይህም ፈርዖንን አስቆጣው። የግብፅ ምድር በዘጠኝ መቅሰፍቶች ከተመታ በኋላ ፈርዖን ሙሴን እንዲህ ሲል አስጠነቀቀው፦ “ሁለተኛ እኔ ዘንድ እንዳትደርስ! ፊቴን ባየህበት በዚያ ቀን ፈጽመህ እንደምትሞት ዕወቅ።” (ዘፀ. 10:28) ሙሴ ከፈርዖን ፊት ከመውጣቱ በፊት የንጉሡ የበኩር ልጅ እንደሚሞት ተናገረ። (ዘፀ. 11:4-8) በመጨረሻም ሙሴ፣ ፍየል ወይም ጠቦት በግ በማረድ ደሙን በበራቸው መቃንና ጉበን ላይ እንዲቀቡ ለእስራኤላውያን ቤተሰብ መመሪያ ሰጠ፤ ጠቦት በግ ደግሞ ራ በተባለው የግብፃውያን አምላክ ዘንድ እንደ ቅዱስ ነገር ተድርጎ ይታይ ነበር። (ዘፀ. 12:5-7) በዚህ ጊዜ ፈርዖን ምን ዓይነት ምላሽ ሊሰጥ እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ያም ሆነ ይህ ሙሴ አልፈራም። ለምን? “የንጉሡን ቁጣ” ከመፍራት ይልቅ በእምነት ይሖዋን የታዘዘው ‘የማይታየውን አምላክ እንደሚያየው አድርጎ በጽናት ስለቀጠለ’ ነው።—ዕብራውያን 11:27, 28ን አንብብ።
3. ሙሴ ‘በማይታየው’ አምላክ ላይ ከነበረው እምነት ጋር በተያያዘ ምን እንመረምራለን?
3 ‘አምላክን የምታየው’ ያህል ሆኖ እንዲሰማህ የሚያደርግ ጠንካራ እምነት አለህ? (ማቴ. 5:8) “የማይታየውን” አምላክ ለማየት የሚያስችል የጠራ መንፈሳዊ እይታ እንዲኖረን እስቲ የሙሴን ታሪክ እንመልከት። ሙሴ በይሖዋ ላይ የነበረው እምነት ከሰው ፍርሃት የጠበቀው እንዴት ነው? አምላክ ቃል በገባቸው ነገሮች ላይ እምነት እንዳለው ያሳየው በምን መንገድ ነው? ሙሴ “የማይታየውን” አምላክ ማየት መቻሉ እሱና ሕዝቡ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ በገቡበት ወቅት ብርታት የሰጠው እንዴት ነው?
“የንጉሡን ቁጣ” አልፈራም
4. ነገሩን በሰብዓዊ ዓይን የሚመለከት ሰው፣ ሙሴን ከፈርዖን ጋር ሲያነጻጽረው ምን ብሎ ሊያስብ ይችላል?
4 በሰብዓዊ ዓይን ስንመለከተው ሙሴ ከፈርዖን ጋር ጨርሶ ሊወዳደር የሚችል ሰው አልነበረም። የሙሴ ሕልውና፣ ደኅንነቱ እንዲሁም የወደፊት ሕይወቱ በፈርዖን እጅ ውስጥ ያለ ይመስል ነበር። ሙሴ ራሱ “ወደ ፈርዖን የምሄድና የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ የማወጣ እኔ ማን ነኝ?” በማለት ይሖዋን ጠይቆት ነበር። (ዘፀ. 3:11) ከ40 ዓመታት ገደማ በፊት ሙሴ ሕይወቱን ለማትረፍ ከግብፅ ሸሽቶ ወጥቶ ነበር። በመሆኑም ‘ወደ ግብፅ ተመልሼ በመሄድ ንጉሡን የሚያስቆጣ ነገር ማድረጌ ጥበብ ነው?’ በማለት አስቦ ሊሆን ይችላል።
5, 6. ሙሴ ከፈርዖን ይልቅ ይሖዋን እንዲፈራ የረዳው ምንድን ነው?
5 ሙሴ ወደ ግብፅ ከመመለሱ በፊት አምላክ አንድ ጠቃሚ የሆነ እውነታ አስተምሮት ነበር፤ ይህ እውነታ “እግዚአብሔርን መፍራት ጥበብ ነው” የሚለው ሲሆን ሙሴም ከጊዜ በኋላ ይህን ሐሳብ በኢዮብ መጽሐፍ ውስጥ መዝግቦታል። (ኢዮብ 28:28) ሙሴ እንዲህ ዓይነት ፍርሃት በማዳበር ነገሮችን በጥበብ እንዲይዝ ለመርዳት ሲል ይሖዋ በሰዎችና ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ መካከል ያለውን ጉልህ ልዩነት ግልጽ አደረገለት። ይሖዋ ሙሴን እንዲህ በማለት ጠየቀው፦ “ለሰው አንደበቱን የሰጠው ማነው? ሰውን ደንቆሮ ወይም ዲዳ የሚያደርገው ማነው? ዓይን የሚሰጥ ወይም ዕውር የሚያደርገውስ ማነው? እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን?”—ዘፀ. 4:11
6 አምላክ ሙሴን ሊያስተምረው የፈለገው ምንድን ነው? ሙሴ መፍራት አያስፈልገውም። የላከው ይሖዋ ነው፤ ስለዚህ ለፈርዖን የአምላክን መልእክት እንዲያደርስ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ሊሰጠው ይችላል። በተጨማሪም ፈርዖን ከይሖዋ ጋር ጨርሶ ሊወዳደር አይችልም። ደግሞም የአምላክ አገልጋዮች በግብፃውያን ገዢዎች እጅ ለአደጋ ሲጋለጡ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ አልነበረም። ሙሴ ከዚያ በፊት በነበሩት ፈርዖኖች አገዛዝ ወቅት ይሖዋ አብርሃምን፣ ዮሴፍንና እሱን ራሱን እንዴት ከአደጋ እንደጠበቃቸው አሰላስሎ ሊሆን ይችላል። (ዘፍ. 12:17-19፤ 41:14, 39-41፤ ዘፀ. 1:22–2:10) ሙሴ ‘በማይታየው’ አምላክ በይሖዋ ላይ እምነት በማሳደር በድፍረት ፈርዖን ፊት የቀረበ ሲሆን አምላክ ያዘዘውን መልእክት አንድም ሳያስቀር ተናግሯል።
7. አንዲት እህት በይሖዋ ላይ ያላት እምነት ጥበቃ የሆነላት እንዴት ነው?
7 ኤላ የተባለች እህትም ልክ እንደ ሙሴ በይሖዋ ላይ እምነት ማሳደሯ በሰው ፍርሃት እንዳትሸነፍ ረድቷታል። በ1949 የኬጂቢ አባላት ኤላን አሰሯት፤ ከዚያም አፍጥጠው በሚመለከቷት ወጣት የፖሊስ መኮንኖች ፊት ልብሷን በሙሉ እንድታወልቅ አስገደዷት። እንዲህ ብላለች፦ “እንደተዋረድኩ ተሰማኝ። ሆኖም ወደ ይሖዋ ከጸለይኩ በኋላ ውስጣዊ ሰላምና መረጋጋት አገኘሁ።” ቀጥሎም ለሦስት ቀን ያህል አንድ ጠባብ ክፍል ውስጥ ብቻዋን አሰሯት። ኤላ ሁኔታውን እንዲህ ስትል ተርካለች፦ “የፖሊስ መኮንኖቹ እንዲህ እያሉ ፎከሩ፦ ‘ይሖዋ የሚባል ስም በኢስቶኒያ ውስጥ ፈጽሞ እንዳይታወስ እናደርጋለን! እናንተ ካምፕ ትገባላችሁ፤ ሌሎቹ ደግሞ ወደ ሳይቤሪያ ይጋዛሉ።’ ከዚያም እያፌዙ ‘እስቲ ይሖዋ ሲረዳችሁ እናያለን!’ አሉን።” ኤላ በሰው ፍርሃት ትሸነፍ ይሆን? ወይስ በይሖዋ ትታመናለች? ለምርመራ በቀረበችበት ወቅት ለሚያሾፉባት የፖሊስ መኮንኖች በድፍረት እንዲህ ብላለች፦ “ይህን ጉዳይ ብዙ አስቤበታለሁ። የአምላክን ሞገስ አጥቼ ነፃ ሆኜ ከመኖር ከአምላክ ጋር ያለኝን ዝምድና እንደያዝኩ በእስር ቤት መቆየት እመርጣለሁ።” ይሖዋ ለኤላ፣ በፊቷ የቆሙትን ሰዎች ያህል እውን ነበር። እምነቷ ንጹሕ አቋሟን መጠበቅ እንድትችል ረድቷታል።
8, 9. (ሀ) ለሰው ፍርሃት ማርከሻው ምንድን ነው? (ለ) በሰው ፍርሃት የመሸነፍ ፈተና ካጋጠመህ ትኩረትህን በማን ላይ ማድረግ ይኖርብሃል?
8 በይሖዋ ላይ እምነት ማዳበርህ ፍርሃትን ለማሸነፍ ይረዳሃል። ከፍተኛ ባለሥልጣናት የአምልኮ ነፃነትህን በሚያግዱበት ወቅት ሕልውናህ፣ ደኅንነትህ እንዲሁም የወደፊት ሕይወትህ በእነሱ እጅ እንደወደቀ ይሰማህ ይሆናል። ‘ይሖዋን ማገልገሌን በመቀጠል ባለሥልጣናቱን ማስቆጣቴ ጥበብ ነው?’ የሚል ሐሳብ ሊመጣብህ ይችላል። ለሰው ፍርሃት ማርከሻው በአምላክ ላይ እምነት ማሳደር እንደሆነ አስታውስ። (ምሳሌ 29:25ን አንብብ።) ይሖዋ “ሟች የሆኑትን ሰዎች፣ እንደ ሣር የሚጠወልጉትን የሰው ልጆች ለምን ትፈራለህ?” በማለት ጠይቋል።—ኢሳ. 51:12, 13
9 ሁሉን ቻይ በሆነው አባትህ ላይ ትኩረት አድርግ። ጨካኝ በሆኑ ገዢዎች ሥር መከራ የሚደርስባቸውን አገልጋዮቹን ይመለከታቸዋል፤ የሚደርስባቸውን ሥቃይ ይረዳል፤ እንዲሁም ለእነሱ ሲል እርምጃ ይወስዳል። (ዘፀ. 3:7-10) በከፍተኛ ባለሥልጣናት ፊት ስለ እምነትህ መናገር በሚኖርብህ ጊዜም ‘እንዴት ብዬ እናገራለሁ? ምንስ ብዬ እመልሳለሁ? ብለህ አትጨነቅ፤ ምክንያቱም የምትናገረው ነገር በዚያኑ ሰዓት ይሰጥሃል።’ (ማቴ. 10:18-20) ሰብዓዊ ገዢዎችና የመንግሥት ባለሥልጣናት ከይሖዋ ጋር ጨርሶ ሊወዳደሩ አይችሉም። እምነትህን ከአሁኑ ካጠናከርህ አንተን ለመርዳት የሚጓጓው ይሖዋ እውን ይሆንልሃል።
አምላክ በገባው ቃል ላይ እምነት እንዳለው አሳይቷል
10. (ሀ) ይሖዋ በ1513 ዓ.ዓ. ኒሳን ወር ላይ ለእስራኤላውያን ምን መመሪያ ሰጣቸው? (ለ) ሙሴ የአምላክን መመሪያዎች የታዘዘው ለምንድን ነው?
10 በ1513 ዓ.ዓ. በኒሳን ወር ላይ ሙሴና አሮን ለእስራኤላውያን እንግዳ የሆነ መመሪያ እንዲሰጡ ይሖዋ አዘዛቸው፤ መመሪያው እስራኤላውያን እንከን የሌለበት በግ ወይም ፍየል በማረድ ደሙን በበራቸው መቃንና ጉበን ላይ እንዲቀቡ የሚያዝዝ ነበር። (ዘፀ. 12:3-7) ታዲያ ሙሴ ምን አደረገ? ሐዋርያው ጳውሎስ ከጊዜ በኋላ ስለ ሙሴ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “አጥፊው የበኩር ልጆቻቸውን እንዳይገድል ሙሴ ፋሲካን ያከበረውና መቃኖቹ ላይ ደም የረጨው በእምነት ነው።” (ዕብ. 11:28) ሙሴ፣ ይሖዋ እምነት የሚጣልበት አምላክ እንደሆነ ያውቅ ነበር፤ በመሆኑም ይሖዋ፣ የግብፃውያንን የበኩር ልጆች ለመግደል የገባውን ቃል እንደሚፈጽም እምነት ነበረው።
11. ሙሴ ሌሎችን ያስጠነቀቀው ለምንድን ነው?
11 የሙሴ ልጆች በወቅቱ በምድያም የነበሩ ይመስላል፤ ይህ ቦታ የሚገኘው ደግሞ ‘ከአጥፊው’ ርቆ ነው። * (ዘፀ. 18:1-6) ያም ሆኖ ሙሴ ታዛዥ በመሆን፣ እስራኤላውያን ቤተሰቦች የበኩር ልጆቻቸውን ከጥፋት ማትረፍ እንዲችሉ አስጠንቅቋል። የሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ ነበር፤ ሙሴም ለወገኖቹ ፍቅር ነበረው። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ሙሴ በፍጥነት “የእስራኤልን ሕዝብ አለቆች በሙሉ አስጠርቶ . . . ‘የፋሲካን በግ እረዱ’” አላቸው።—ዘፀ. 12:21
12. ይሖዋ፣ የትኛውን አስፈላጊ መልእክት እንድናውጅ አዝዞናል?
12 የይሖዋ ሕዝቦች በመላእክት በመታገዝ የሚከተለውን አስፈላጊ የሆነ መልእክት ለሰዎች እያወጁ ነው፦ “አምላክን ፍሩ፣ ክብርም ስጡት፤ ምክንያቱም እሱ ፍርድ የሚሰጥበት ሰዓት ደርሷል፤ በመሆኑም ሰማይን፣ ምድርን፣ ባሕርንና የውኃ ምንጮችን የሠራውን አምልኩ።” (ራእይ 14:7) ይህን መልእክት የምናውጅበት ጊዜ አሁን ነው። ሰዎች ታላቂቱ ባቢሎን ‘ከሚደርስባት መቅሰፍት ተካፋይ እንዳይሆኑ’ ከእሷ መውጣት እንዳለባቸው ማስጠንቀቅ ይኖርብናል። (ራእይ 18:4) ‘ሌሎች በጎችም’ ከቅቡዓን ክርስቲያኖች ጋር በመተባበር ከአምላክ የራቁ ሰዎችን ከእሱ ጋር ‘እንዲታረቁ’ እየለመኑ ነው።—ዮሐ. 10:16፤ 2 ቆሮ. 5:20
13. ምሥራቹን የመስበክ ፍላጎታችን እያደገ እንዲሄድ ምን ይረዳናል?
13 “ፍርድ የሚሰጥበት ሰዓት” እንደደረሰ እርግጠኞች ነን። ይሖዋ የስብከቱና ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ አጣዳፊ መሆኑን መናገሩ የተጋነነ እንዳልሆነም እምነት አለን። ሐዋርያው ዮሐንስ “አራቱን የምድር ነፋሳት አጥብቀው” የያዙ “አራት መላእክት በአራቱ የምድር ማዕዘናት ቆመው” በራእይ ተመልክቶ ነበር። (ራእይ 7:1) እነዚህ መላእክት በዚህ ዓለም ላይ ታላቅ መከራን የሚያመጡትን የጥፋት ነፋሳት ለመልቀቅ በተጠንቀቅ ላይ እንደሆኑ በእምነት ዓይንህ ይታይሃል? እነዚህ መላእክት በእምነት ዓይንህ የሚታዩህ ከሆነ ምሥራቹን በሙሉ ልብ መስበክ ትችላለህ።
14. ‘ኃጢአተኛው ሰው ከክፉ ሥራው እንዲመለስ ለማስጠንቀቅ’ የሚያነሳሳን ምንድን ነው?
14 እውነተኛ ክርስቲያኖች አሁንም ቢሆን ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት የመመሥረት መብት አግኝተዋል፤ እንዲሁም የዘላለም ሕይወት ተስፋ አላቸው። ያም ቢሆን ‘ኃጢአተኛው ሰው ነፍሱን ያድን ዘንድ ከክፉ ሥራው እንዲመለስ የማስጠንቀቅ’ ኃላፊነት እንዳለብን እናውቃለን። (ሕዝቅኤል 3:17-19ን አንብብ።) እርግጥ ነው፣ የምንሰብከው የደም ዕዳ እንዳይኖርብን ብለን ብቻ አይደለም። ለይሖዋና ለሰዎች ፍቅር አለን። ኢየሱስ፣ ፍቅርና ምሕረት ማሳየት ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ስለ ደጉ ሳምራዊ በተናገረው ምሳሌ ላይ ገልጿል። ‘ለሰዎች የምመሠክረው ልክ እንደ ሳምራዊው ሰው “በአዘኔታ” ስሜት ተነሳስቼ ነው?’ እያልን ራሳችንን እንጠይቅ። ደግሞም በምሳሌው ላይ እንደተጠቀሱት ካህኑና ሌዋዊው ሰበብ አስባብ በመፍጠር ሰዎችን ‘ገለል ብለን ማለፍ’ በፍጹም አንፈልግም። (ሉቃስ 10:25-37) አምላክ ቃል በገባቸው ነገሮች ላይ ያለን እምነት እንዲሁም ለሰዎች ያለን ፍቅር ጊዜው ከማለቁ በፊት በስብከቱ ሥራ የተሟላ ተሳትፎ እንድናደርግ ያነሳሱናል።
“ቀይ ባሕርን በእምነት ተሻገሩ”
15. እስራኤላውያን ወጥመድ ውስጥ እንደገቡ የተሰማቸው ለምንድን ነው?
15 ሙሴ ‘በማይታየው’ አምላክ በይሖዋ ላይ እምነት ማሳደሩ ከግብፅ የወጡት እስራኤላውያን አደጋ በተጋረጠባቸው ወቅት ረድቶታል። መጽሐፍ ቅዱስ ሁኔታውን እንዲህ በማለት ዘግቧል፦ “እስራኤላውያን ቀና ብለው ተመለከቱ፤ እነሆ፣ ግብፃውያን ይከታተሏቸው ነበር፤ እነርሱም በታላቅ ፍርሃት ወደ እግዚአብሔር ጮኹ።” (ዘፀ. 14:10-12) እንዲህ ያለ አጣብቂኝ ውስጥ እንደሚገቡ ቀደም ሲል አያውቁም ነበር? ያውቁ ነበር። ምክንያቱም ይሖዋ አስቀድሞ እንዲህ ሲል ተናግሮ ነበር፦ “የፈርዖንን ልብ ስለማደነድነው ያሳድዳቸዋል፤ ነገር ግን በፈርዖንና በሰራዊቱ ሁሉ ለራሴ ክብርን አገኛለሁ፤ ግብፃውያንም እኔ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] መሆኔን ያውቃሉ።” (ዘፀ. 14:4) ይሁን እንጂ እስራኤላውያን የታያቸው በሥጋዊ ዓይን የሚታዩት ነገሮች ብቻ ናቸው፤ ይኸውም ከፊት ለፊታቸው ያለው ለማቋረጥ የማይሞከረው ቀይ ባሕር፣ ከኋላቸው እየገሠገሡ ያሉት የፈርዖን ፈጣን የጦር ሠረገላዎች እንዲሁም እየመራቸው ያለው የ80 ዓመት አዛውንትና እረኛ የሆነው ሙሴ ናቸው! በመሆኑም ወጥመድ ውስጥ እንደገቡ ተሰማቸው።
16. እስራኤላውያን ቀይ ባሕር በደረሱበት ወቅት ሙሴ እምነቱ እንዳይፈራ የረዳው እንዴት ነው?
16 ያም ቢሆን ሙሴ በፍርሃት አልተሸበረም። ለምን? ምክንያቱም ከባሕሩ ወይም ከሚከተላቸው ሠራዊት እጅግ የበለጠ ኃይል ያለውን አካል በእምነት ዓይኑ ተመልክቶ ነበር። ‘ይሖዋ የሚያደርግላቸው መታደግ ታይቶት’ ነበር፤ እንዲሁም ይሖዋ ለእስራኤላውያን እንደሚዋጋላቸው ያውቃል። (ዘፀአት 14:13, 14ን አንብብ።) የሙሴ እምነት ለሕዝቡ የብርታት ምንጭ ሆኗል። መጽሐፍ ቅዱስ “በደረቅ ምድር እንደሚሄዱ ሆነው ቀይ ባሕርን በእምነት ተሻገሩ፤ ይሁንና ግብፃውያን እንዲህ ለማድረግ በደፈሩ ጊዜ ሰጠሙ” በማለት ይናገራል። (ዕብ. 11:29) ከዚያ በኋላ ሕዝቡ “እግዚአብሔርን ፈሩ፤ በእግዚአብሔርና፣ በባሪያው በሙሴም አመኑ።”—ዘፀ. 14:31
17. ወደፊት እምነታችንን የሚፈትን ምን ሁኔታ ያጋጥመናል?
17 በቅርቡ የእኛም ሕይወት አደጋ ላይ እንደወደቀ የሚሰማን ጊዜ ይመጣል። አርማጌዶን ከመጀመሩ በፊት የዓለም መንግሥታት በኃይልም ሆነ በቁጥር ከእኛ እጅግ የሚበልጡ የሃይማኖት ድርጅቶችን ሙሉ በሙሉ ያጠፋሉ። (ራእይ 17:16) በዚያን ጊዜ ምን ያህል ለጥቃት የተጋለጥን እንደምንሆን ይሖዋ ሁኔታችንን በትንቢት ሲገልጽ ‘ቅጥር የሌላቸው መንደሮች’ እንዲሁም ‘ያለ ቅጥር፣ ያለ በርና ያለ ብረት መወርወሪያ የሚኖረው ሕዝብ’ ብሏል። (ሕዝ. 38:10-12, 14-16) ነገሩን በሰብዓዊ ዓይን ከተመለከትነው ከጥቃቱ ልንተርፍ የምንችልበት ምንም መንገድ የሌለ ሊመስል ይችላል። ታዲያ በዚያን ጊዜ በፍርሃት ትሸበር ይሆን?
18. በታላቁ መከራ ወቅት መፍራት የማይኖርብን ለምን እንደሆነ አብራራ።
18 በፍርሃት መሸበር የለብንም። ለምን? ምክንያቱም ይሖዋ፣ በሕዝቡ ላይ እንዲህ ዓይነት ጥቃት እንደሚደርስ አስቀድሞ ተናግሯል። ይህ ብቻ ሳይሆን የመጨረሻ ውጤቱም ምን እንደሚሆን ገልጿል። “‘ጎግ የእስራኤልን ምድር ሲወጋ፣ ብርቱ ቍጣዬ ይነሣሣል፤’ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ‘በዚያን ጊዜ በቅናቴና በሚያስፈራው ቍጣዬ . . . [እናገራለሁ]።’” (ሕዝ. 38:18-23) ይሖዋ፣ በሕዝቦቹ ላይ ጉዳት ለማድረስ የሚቃጡትን በሙሉ ያጠፋቸዋል። “ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን” በሚያመጣው ውጤት ላይ እምነት ማሳደራችን ‘ይሖዋ የሚያደርግልን መታደግ’ እንዲታየን እንዲሁም ንጹሕ አቋማችንን እንድንጠብቅ ይረዳናል።—ኢዩ. 2:31, 32
19. (ሀ) በይሖዋና በሙሴ መካከል የነበረው ወዳጅነት ምን ያህል የጠበቀ ነበር? (ለ) በመንገድህ ሁሉ ይሖዋን የምታውቅ ከሆነ ምን በረከት ታገኛለህ?
19 ‘የማይታየውን እንደምታየው አድርገህ በጽናት በመቀጠል’ ለዚያ አስፈሪ ጊዜ ራስህን ከአሁኑ አዘጋጅ! አዘውትረህ በማጥናትና በመጸለይ ከይሖዋ አምላክ ጋር ያለህን ወዳጅነት አጠናክር። ሙሴ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ስለነበረው እንዲሁም ይሖዋ ታላላቅ ነገሮችን እንዲፈጽም ስለተጠቀመበት ይሖዋን “ፊት ለፊት” እንዳወቀው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዘዳ. 34:10) በእርግጥም ሙሴ የተለየ ነቢይ ነበር። አንተም እምነት ካለህ ይሖዋን በዓይንህ የምታየው ያህል ልታውቀው ትችላለህ። የአምላክ ቃል እንደሚያበረታታው “በመንገድህ ሁሉ” እሱን የምታውቅ ከሆነ “ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል።”—ምሳሌ 3:6
^ አን.11 ይሖዋ በግብፃውያን ላይ የፍርድ እርምጃ ለማስፈጸም የላከው መላእክትን እንደሆነ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል።—መዝ. 78:49-51