ይሖዋ ትዳራችሁን እንዲያጠናክረውና እንዲጠብቀው ፍቀዱ
“[ይሖዋ] ከተማን ካልጠበቀ፣ ጠባቂ በከንቱ ይተጋል።”
1, 2. (ሀ) ከእስራኤላውያን መካከል 24,000 የሚሆኑት አስደናቂ በረከቶችን ያጡት ለምንድን ነው? (ለ) ይህ ጥንታዊ ታሪክ ለእኛ ትርጉም አለው የምንለው ለምንድን ነው?
የእስራኤል ብሔር ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባቱ ከጥቂት ጊዜ በፊት በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ወንዶች “ከሞዓብ ሴቶች ጋር [አመነዘሩ]።” በዚህም ምክንያት 24,000 የሚሆኑትን ይሖዋ ቀሰፋቸው። እስቲ አስበው፤ እስራኤላውያን ለረጅም ጊዜ ሲጠብቁት የነበረውን ውርሻ ለማግኘት በጣም ተቃርበው የነበረ ቢሆንም በፈተና በመውደቃቸው ይህን አስደናቂ በረከት ሳያገኙ ቀሩ።—ዘኁ. 25:1-5, 9
2 ይህ አሳዛኝ ታሪክ የተመዘገበው “የሥርዓቶቹ ፍጻሜ የደረሰብንን እኛን ለማስጠንቀቅ ነው።” (1 ቆሮ. 10:6-11) “በመጨረሻዎቹ ቀኖች” መደምደሚያ ላይ የምንኖረው የአምላክ አገልጋዮች ጽድቅ በሰፈነበት አዲስ ዓለም ደፍ ላይ እንገኛለን። (2 ጢሞ. 3:1፤ 2 ጴጥ. 3:13) የሚያሳዝነው ግን፣ አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች በሥነ ምግባር ረገድ አቋማቸውን አላልተዋል። በፆታ ብልግና ወጥመድ በመውደቃቸው ይህ አካሄድ የሚያስከትለውን መራራ ውጤት አጭደዋል። እንዲህ ያሉ ሰዎች ዘላለማዊ በረከት የማግኘት አጋጣሚያቸውን ሊያጡ ይችላሉ።
3. ባለትዳሮች የይሖዋ አመራርና ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ምስል ተመልከት።)
3 በዛሬው ጊዜ የሥነ ምግባር ብልግና እንደ መቅሰፍት እየተስፋፋ በመሆኑ ባልና ሚስት፣ ትዳራቸውን ለመጠበቅ የሚያደርጉት ጥረት ከንቱ እንዳይሆን የይሖዋ አመራርና ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል። (መዝሙር 127:1ን አንብብ።) ባለትዳሮች ልባቸውን በመጠበቅ፣ ወደ አምላክ በመቅረብ፣ አዲሱን ስብዕና በመልበስ፣ ትርጉም ያለው የሐሳብ ልውውጥ በማድረግ እንዲሁም ለትዳር ጓደኛቸው የሚገባውን በማድረግ ትዳራቸውን ማጠናከር የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ከዚህ በመቀጠል እንመረምራለን።
ልባችሁን ጠብቁ
4. አንዳንድ ክርስቲያኖችን ወደ ኃጢአት ጎዳና የመራቸው ምንድን ነው?
4 አንድ ክርስቲያን በሥነ ምግባር ብልግና ሊፈተን የሚችለው እንዴት ነው? ወደ ጥፋት የሚመራውን የብልግና ጎዳና ለመከተል ብዙውን ጊዜ ምክንያት የሚሆነው የምናየው ነገር ነው። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “የፆታ ስሜቱ እስኪቀሰቀስ ድረስ አንዲትን ሴት በምኞት የሚመለከት ሁሉ በዚያን ጊዜ በልቡ ከእሷ ጋር አመንዝሯል።” (ማቴ. 5:27, 28፤ 2 ጴጥ. 2:14) ኃጢአት የፈጸሙ በርካታ ክርስቲያኖች ይህን ያደረጉት ፖርኖግራፊ በመመልከት፣ የብልግና ይዘት ያላቸው ጽሑፎችን በማንበብ ወይም አስጸያፊ የኢንተርኔት ገጾችን በመቃኘት ሥነ ምግባራዊ አቋማቸውን አላልተው ስለነበር ነው። ሌሎች ደግሞ የፆታ ስሜት በሚያነሳሱ ፊልሞች፣ ቲያትሮች ወይም የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ይዝናኑ ነበር። ወደ ምሽት ክለቦችና እርቃን ጭፈራ ቤቶች ወይም አስነዋሪ ድርጊት ወደሚፈጸምባቸው መታሻ ቤቶች የሄዱም አሉ።
5. ልባችንን መጠበቅ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
5 አንዳንዶች ደግሞ በፈተና የሚወድቁት፣ ተገቢ ካልሆነ አቅጣጫ ትኩረት ለማግኘት ስለሚሞክሩ ነው። የምንኖረው ራስን መግዛት በጠፋበትና የሥነ ምግባር ብልግና በተስፋፋበት ዓለም ውስጥ በመሆኑ ተንኰለኛ የሆነው ልባችን የትዳር ጓደኛችን ላልሆነ ሰው የፍቅር ስሜት እንዲያድርብን በማድረግ በቀላሉ ሊያታልለን ይችላል። (ኤርምያስ 17:9, 10ን አንብብ።) ኢየሱስ “ከልብ ክፉ ሐሳብ፣ ግድያ፣ ምንዝር፣ ዝሙት፣ . . . ይወጣሉ” ብሏል።—ማቴ. 15:19
6, 7. (ሀ) ተንኰለኛ የሆነ ልብ አንድን ሰው ምን ዓይነት የኃጢአት ጎዳና እንዲከተል ሊያደርገው ይችላል? (ለ) በብልግና አዘቅት እንዳንወድቅ ራሳችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?
6 እርስ በርስ የሚፈላለጉ ሁለት ሰዎች ተንኰለኛ በሆነው ልባቸው ውስጥ ተገቢ ያልሆነ ምኞት ሥር እንዲሰድድ ከፈቀዱ፣ ከትዳር ጓደኛቸው ጋር ብቻ መወያየት ያለባቸውን ነገር ማውራት ሊጀምሩ ይችላሉ። ብዙም ሳይቆይ አብረው ጊዜ ለማሳለፍ የተለያዩ ዘዴዎችን መፍጠር ይጀምራሉ፤ እንዲሁ ሲታይ የሚገናኙት በአጋጣሚ ይመስል ይሆናል፤ ግንኙነታቸውም ሌላ ነገር ያለው ላይመስል ይችላል። በዚህ መልኩ አዘውትረው ጊዜ ሲያሳልፉ አንዳቸው ለሌላው ያላቸው ስሜት እየጠነከረ ስለሚሄድ የሥነ ምግባር አቋማቸው እየላላ ይመጣል። የሚያደርጉት ነገር ስህተት እንደሆነ ያውቃሉ፤ ሆኖም በዚህ የኃጢአት ጎዳና መጓዛቸውን በቀጠሉ መጠን ይህን አካሄድ ማቆም ይበልጥ ይከብዳቸዋል።—ምሳሌ 7:21, 22
7 እነዚህ ሰዎች ከመጥፎ ፍላጎትና ተገቢ ያልሆነ አነጋገር አልፈው ከትዳር ጓደኛቸው ጋር ብቻ ሊያደርጓቸው የሚገቡ ነገሮችን መፈጸም ለምሳሌ እጅ ለእጅ መያያዝ፣ መሳሳም፣ መደባበስ፣ የፆታ ስሜት በሚቀሰቅስ መንገድ መተሻሸት እንዲሁም ሌሎች የፍቅር መግለጫዎችን መለዋወጥ ሊጀምሩ ይችላሉ፤ ይህም ሥነ ምግባራዊ መከላከያቸው ቀስ በቀስ እንዲሸረሸር ያደርጋል። በመጨረሻም ‘በራሳቸው ምኞት ይማረካሉ እንዲሁም ይታለላሉ’፤ በሌላ አባባል ምኞታቸው ወጥመድ ይሆንባቸዋል። “ምኞት ከፀነሰች በኋላ ኃጢአትን ትወልዳለች” ማለትም የፆታ ብልግና ይፈጽማሉ። (ያዕ. 1:14, 15) ይህ ምንኛ የሚያሳዝን ይሆናል! እነዚህ ግለሰቦች ይሖዋ፣ ቅዱስ ለሆነው የጋብቻ ዝግጅት ያላቸውን አክብሮት እንዲያጠናክርላቸው ቢፈቅዱ ኖሮ እንዲህ ባለው የብልግና አዘቅት ከመውደቅ ይድኑ ነበር። ይሁንና አንድ ሰው ለጋብቻ ዝግጅት አክብሮት ማዳበር የሚችለው እንዴት ነው?
ምንጊዜም ወደ አምላክ ቅረቡ
8.ከይሖዋ ጋር ያለን ወዳጅነት ሥነ ምግባራዊ አቋማችንን ለመጠበቅ የሚረዳን እንዴት ነው?
8 መዝሙር 97:10ን አንብብ። ከይሖዋ ጋር ያለን ወዳጅነት ሥነ ምግባራዊ አቋማችንን ለመጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል። ግሩም ስለሆኑት የአምላክ ባሕርያት ስናውቅና ‘የተወደድን ልጆች በመሆን አምላክን ለመኮረጅ’ እንዲሁም ‘በፍቅር መመላለሳችንን ለመቀጠል’ ጥረት ስናደርግ ‘ከዝሙትና ከማንኛውም ዓይነት ርኩሰት’ ለመራቅ ያለን ቁርጠኝነት ይጠናከራል። (ኤፌ. 5:1-4) ባለትዳሮች፣ አምላክ “ሴሰኞችንና አመንዝሮችን [እንደሚፈርድባቸው]” ስለሚያውቁ ጋብቻቸው ክቡርና ከርኩሰት የጸዳ እንዲሆን ለማድረግ ጠንክረው ይሠራሉ።
9. (ሀ) ዮሴፍ የፆታ ብልግና እንዲፈጽም የቀረበለትን ፈተና ማሸነፍ የቻለው እንዴት ነው? (ለ) ከዮሴፍ ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?
9 ከአምላክ ታማኝ አገልጋዮች አንዳንዶቹ፣ የይሖዋ ምሥክር ካልሆኑ የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ከሥራ ሰዓት ውጪ ጊዜ በማሳለፍ የሥነ ምግባር አቋማቸውን አላልተዋል። በሥራ ሰዓትም ቢሆን ፈታኝ ሁኔታ ሊያጋጥም ይችላል። ዮሴፍ በተባለው መልከ መልካም ወጣት ላይ የአሠሪው ባለቤት ዓይኗን የጣለችበት በሥራ ቦታው ነው። ይህች ሴት በየዕለቱ እሱን ለማጥመድ ትጥር ነበር። አንድ ቀን “ልብሱን ጨምድዳ ይዛ ‘በል አብረኸኝ ተኛ’ አለችው።” ዮሴፍ ግን ጥሏት ሸሸ። ዮሴፍ እንዲህ ያለ ፈታኝ ሁኔታ ሲያጋጥመው ሥነ ምግባራዊ አቋሙን እንዳያላላ የረዳው ምንድን ነው? ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናውንና ታማኝነቱን መጠበቅ የቻለው ከአምላክ ጋር ያለውን ዝምድና ላለማበላሸት ቁርጥ አቋም ስለነበረው ነው። እንዲህ ያለ ጠንካራ አቋም በመውሰዱ ሥራውን ያጣ ከመሆኑም ሌላ ያለ በደሉ ወደ ወኅኒ ወርዷል፤ ሆኖም ይሖዋ ባርኮታል። (ዘፍ. 39:1-12፤ 41:38-43) እንግዲያው ክርስቲያኖች በሥራ ቦታም ይሁን በሌሎች አጋጣሚዎች የትዳር ጓደኛቸው ካልሆነ ሰው ጋር ፈታኝ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ላለመገኘት መጠንቀቅ አለባቸው።
አዲሱን ስብዕና ልበሱ
10. አዲሱ ስብዕና ከሥነ ምግባራዊ አደጋ የሚጠብቀን እንዴት ነው?
10 አዲሱ ስብዕና ‘እንደ አምላክ ፈቃድ የተፈጠረና ከእውነተኛ ጽድቅና ታማኝነት ጋር የሚስማማ’ በመሆኑ ለባለትዳሮች አስፈላጊ ከሆኑት ሥነ ምግባራዊ መከላከያዎች አንዱ ነው። (ኤፌ. 4:24) ይህን አዲስ ስብዕና የሚለብሱ ክርስቲያኖች እንደ “ዝሙት፣ ርኩሰት፣ የፆታ ምኞት፣ መጥፎ ፍላጎትና . . . መጎምጀት” ያሉ በአካል ክፍሎቻቸው ውስጥ የሚገኙ ዝንባሌዎችን ‘መግደል’ ይኖርባቸዋል። (ቆላስይስ 3:5, 6ን አንብብ።) “ግደሉ” የሚለው ቃል ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት እንድንፈጽም የሚገፋፋንን ሥጋዊ ምኞት ለማሸነፍ ጠንካራ እርምጃ መውሰድ እንዳለብን የሚያጎላ ነው። የትዳር ጓደኛችን ላልሆነ ሰው የፆታ ስሜት እንዲያድርብን ሊያደርግ ከሚችል ማንኛውም ነገር መራቅ ይኖርብናል። (ኢዮብ 31:1) አኗኗራችንን ከአምላክ ፈቃድ ጋር ስናስማማ “ክፉ የሆነውን ነገር [መጸየፍ]” እንዲሁም ‘ጥሩ የሆነውን ነገር አጥብቀን መያዝ’ እንማራለን።—ሮም 12:2, 9
11. አዲሱን ስብዕና መልበስ ትዳርን የሚያጠናክረው እንዴት ነው?
11 አዲሱ ስብዕና “ከፈጣሪው አምሳል” ይኸውም ከይሖዋ ጋር የሚስማማ ነው። (ቆላ. 3:10) ባለትዳሮች “ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄን፣ ደግነትን፣ ትሕትናን፣ ገርነትንና ትዕግሥትን” በመልበስ ሥነ ምግባራዊ መከላከያቸውን ሲያጠናክሩ ይባረካሉ። (ቆላ. 3:12) ከዚህም ሌላ ‘የክርስቶስ ሰላም በልባቸው እንዲነግሥ’ ሲፈቅዱ ይበልጥ ተስማምተው መኖር ይችላሉ። (ቆላ. 3:15) ባልና ሚስት ‘እርስ በርሳቸው ከልብ ሲዋደዱ’ ትዳራቸው ምንኛ አስደሳች ይሆናል! እንዲሁም ‘አንዳቸው ሌላውን ለማክበር ቀዳሚ’ ሲሆኑ የበለጠ እርካታ ያገኛሉ።
12. ትዳርን አስደሳች ለማድረግ የትኞቹ ባሕርያት አስፈላጊ እንደሆኑ ይሰማሃል?
12 ሲድ የተባለ አንድ ክርስቲያን ትዳራቸው ደስታ የሰፈነበት እንዲሆን አስተዋጽኦ ያደረጉት ባሕርያት የትኞቹ እንደሆኑ ሲጠየቅ እንዲህ ብሏል፦ “በዋነኝነት ፍቅርን ለማዳበር ሁልጊዜ ጥረት እናደርጋለን። ገርነትም በጣም አስፈላጊ ባሕርይ እንደሆነ ይሰማናል።” ባለቤቱ ሶንያም በዚህ የምትስማማ ሲሆን አክላ እንዲህ ብላለች፦ “ደግነት በጣም ጠቃሚ ባሕርይ እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም። ትሕትና ለማሳየትም ጥረት እናደርጋለን፤ እርግጥ ይህን ማድረግ ቀላል የማይሆንባቸው ጊዜያት አሉ።”
ትርጉም ያለው የሐሳብ ልውውጥ አድርጉ
13. ትዳርን ለማጠናከር ከሚረዱት ቁልፎች አንዱ ምንድን ነው? ለምንስ?
13 ደግነት የሚንጸባረቅበት ንግግር ትዳርን ለማጠናከር ከሚረዱት ቁልፎች አንዱ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። ባልና ሚስት የማያውቁትን ሰው ሌላው ቀርቶ የቤት እንስሶቻቸውን በአክብሮት እያናገሩ የትዳር ጓደኛቸውን ግን አክብሮት በጎደለው መንገድ የሚያዋሩ ቢሆን እንዴት የሚያሳዝን ነው! “የመረረ ጥላቻ፣ ቁጣ፣ ንዴት፣ ጩኸትና ስድብ” የትዳር ጥንካሬ እየተዳከመ እንዲሄድ ያደርጋሉ። (ኤፌ. 4:31) ባልና ሚስት፣ የትዳር ጓደኛቸውን ሁልጊዜ በመንቀፍ ወይም በአሽሙር በመናገር የጋብቻቸውን መሠረት ከማናጋት ይልቅ ደግነትና ርኅራኄ የሚንጸባረቅባቸው ቃላት በመጠቀም ትዳራቸውን ማጠናከር ይችላሉ።
14. የትኞቹን ባሕርያት ከማንጸባረቅ መቆጠብ የጥበብ እርምጃ ነው?
14 መጽሐፍ ቅዱስ “ለዝምታ ጊዜ አለው” ይላል። (መክ. 3:7) ይህ ሲባል ግን የትዳር ጓደኛችንን በማኩረፍ የዝምታ ግድግዳ እንገነባለን ማለት አይደለም፤ እንዲህ ያለው ዝምታ አስፈላጊ የሆነውን የሐሳብ ልውውጥ እንዳናደርግ እንቅፋት ይሆንብናል። በጀርመን የምትገኝ አንዲት ባለትዳር “እንዲህ ባሉ ሁኔታዎች ውስጥ ዝም ማለት የትዳር ጓደኛችሁን ሊጎዳው ይችላል” ብላለች። በሌላ በኩል ደግሞ “ውጥረት የሚፈጥር ሁኔታ ሲኖር መረጋጋት ሁልጊዜ ቀላል ባይሆንም በቁጣ መገንፈልም ተገቢ አይደለም” በማለት አክላ ተናግራለች። “በዚህ ጊዜ የትዳር ጓደኛችሁን የሚጎዳ ነገር ሳታስቡት ልትናገሩ ወይም ልታደርጉ ትችላላችሁ፤ ይህ ደግሞ ሁኔታውን ከማባባስ ውጪ የሚፈይደው ነገር የለም።” ደግሞም መጯጯህና መኳረፍ ችግሮችን ለመፍታት አይረዱም። ከዚህ ይልቅ ባለትዳሮች አለመግባባቶችን ሳይውሉ ሳያድሩ በመፍታትና ማቆሚያ የሌለው ንትርክ ውስጥ ከመግባት በመቆጠብ ትዳራቸውን ማጠናከር ይችላሉ።
15. ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ትዳርን የሚያጠናክረው እንዴት ነው?
15 ባለትዳሮች፣ አንዳቸው ለሌላው ስሜታቸውንና አመለካከታቸውን ለማጋራት የሚጥሩ ከሆነ የትዳራቸው ጥምረት ይጠናከራል። የምንናገርበትን መንገድ ከምንናገረው ነገር ባልተናነሰ ልናስብበት ይገባል። እንግዲያው በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥም እንኳ የድምፃችሁ ቃናም ይሁን የምትጠቀሙባቸው ቃላት ደግነት የሚንጸባረቅባቸው ይሁኑ። እንዲህ ስታደርጉ የትዳር ጓደኛችሁ እናንተን ማዳመጥ ቀላል ይሆንለታል። (ቆላስይስ 4:6ን አንብብ።) ባልና ሚስት ‘የሚያንጽና ሊጠቅም የሚችል መልካም ቃል’ ብቻ ተጠቅመው ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ የሚያደርጉ ከሆነ ትዳራቸውን ማጠናከር ይችላሉ።
ለትዳር ጓደኛችሁ የሚገባውን አድርጉ
16, 17. ባልና ሚስት ለትዳር ጓደኛቸው ስሜታዊና ፆታዊ ፍላጎት ትኩረት መስጠት የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?
16 ባለትዳሮች ከራሳቸው ይልቅ የትዳር ጓደኛቸውን ፍላጎት ሲያስቀድሙም የትዳራቸው ጥምረት ይጠናከራል። (ፊልጵ. 2:3, 4) ባሎችም ሆኑ ሚስቶች ለትዳር ጓደኛቸው ስሜታዊና ፆታዊ ፍላጎት ትኩረት መስጠት ይኖርባቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 7:3, 4ን አንብብ።
17 የሚያሳዝነው ግን፣ አንዳንድ ባለትዳሮች ፍቅራቸውን ከመግለጽ ወይም የፆታ ግንኙነት ከመፈጸም ይቆጠባሉ፤ አንዳንድ ወንዶች ደግሞ ለሚስቶቻቸው አሳቢነት ማሳየት የድክመት ምልክት እንደሆነ ይሰማቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “እናንተም ባሎች፣ አብረዋችሁ የሚኖሩትን የሚስቶቻችሁን ሁኔታ ለመረዳት መጣር ይገባችኋል” ይላል። (1 ጴጥ. 3:7 ፊሊፕስ) አንድ ባል፣ ለትዳር ጓደኛው የሚገባትን ማድረግ ሲባል የፆታ ግንኙነት ከመፈጸም ያለፈ ነገርን እንደሚጨምር መገንዘብ ያስፈልገዋል። አንዲት ሚስት በፆታ ግንኙነት ደስታ ልታገኝ የምትችለው ባሏ የፆታ ግንኙነት ሲፈጽሙ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ጊዜያትም ፍቅርና እንክብካቤ የሚያሳያት ከሆነ ነው። ሁለቱም ፍቅርና አሳቢነት የሚያሳዩ ከሆነ አንዳቸው የሌላውን ስሜታዊና ፆታዊ ፍላጎት ማርካት ይችላሉ።
18. ባልና ሚስት የትዳራቸውን ጥምረት ማጠናከር የሚችሉት እንዴት ነው?
18 ለትዳር ጓደኛ ታማኝ ላለመሆን ሰበብ የሚሆን ነገር ባይኖርም ባልና ሚስት አንዳቸው ለሌላው አሳቢነት የማያሳዩ ከሆነ ይህ አንደኛው ወገን ፍቅር ለማግኘት ወደ ሌላ ሰው እንዲሄድ ወይም ምንዝር ለመፈጸም እንዲፈተን ሊያደርገው ይችላል። (ምሳሌ 5:18፤ መክ. 9:9) በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ “በጋራ ስምምነት ለተወሰነ ጊዜ ካልሆነ በስተቀር አንዳችሁ ለሌላው የሚገባውን አትከልክሉ” ይላል። ለምን? እንዲህ የተባለው “ራሳችሁን መግዛት አቅቷችሁ ሰይጣን እንዳይፈታተናችሁ” ነው። (1 ቆሮ. 7:5) ባልም ሆነ ሚስት ‘ራሳቸውን መግዛት አቅቷቸው’ በሰይጣን ፈተና ቢወድቁና ምንዝር ቢፈጽሙ ምንኛ የሚያሳዝን ይሆናል! በሌላ በኩል ግን ሁለቱም ወገኖች “[የራሳቸውን] ጥቅም ሳይሆን የሌላውን ሰው ጥቅም” የሚፈልጉና ለትዳር ጓደኛቸው የሚገባውን ማድረግን እንደ ግዴታ ሳይሆን እንደ ፍቅር መግለጫ የሚመለከቱት ከሆነ በፍቅር የሚፈጽሙት የፆታ ግንኙነት የትዳራቸውን ጥምረት ያጠናክረዋል።
ምንጊዜም ትዳራችሁን ጠብቁ
19. ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ሊሆን ይገባል? ለምንስ?
19 የምንገኘው ጽድቅ በሰፈነበት አዲስ ዓለም ደፍ ላይ ነው። በመሆኑም በሞዓብ ሜዳ እንደነበሩት 24,000 እስራኤላውያን እኛም ለሥጋዊ ምኞታችን ብንሸነፍ መዘዙ የከፋ ይሆናል። የአምላክ ቃል ይህንን አሳፋሪና አሳዛኝ ታሪክ ካወሳ በኋላ “የቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ” ይላል። (1 ቆሮ. 10:12) እንግዲያው ለሰማያዊው አባታችንም ሆነ ለትዳር ጓደኛችን ምንጊዜም ታማኝ በመሆን ትዳራችንን ማጠናከራችን በጣም አስፈላጊ ነው። (ማቴ. 19:5, 6) ከምንጊዜውም ይበልጥ አሁን፣ ‘ቆሻሻና እድፍ ሳይኖርብን በሰላም ለመገኘት የተቻለንን ጥረት ማድረግ’ ያስፈልገናል።—2 ጴጥ. 3:13, 14