በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝ የውኃ ምንጭ

የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝ የውኃ ምንጭ

የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝ የውኃ ምንጭ

“እኔ ከምሰጠው ውሃ የሚጠጣ ግን ከቶ አይጠማም፤ እኔ የምሰጠው ውሃ በውስጡ የሚፈልቅ የዘላለም ሕይወት ውሃ ምንጭ ይሆናል።”—ዮሐንስ 4:14

“በድንገት፣ ከጨረቃዋ ጀርባ . . . ሰማያዊና ነጭ ቀለም ያለው አንጸባራቂ ፈርጥ ብቅ አለ፤ ውኃ ሰማያዊ ቀለም ያለውና በዝግታ የሚንቀሳቀሱ ነጫጭ ሻሾች የሚታዩበት ይህ ሉል፣ ጥቁር ከሆነ ባሕር ውስጥ ቀስ በቀስ ብቅ የሚል ትንሽ ዕንቁ ይመስል ነበር።”—የጠፈር ተመራማሪ የሆኑት ኤድገር ሚቼል፣ ምድር ከሕዋ ላይ ስትታይ ምን እንደምትመስል የገለጹት በዚህ መንገድ ነበር።

እኚህ የጠፈር ተመራማሪ ስሜታቸውን እንዲህ ባሉ ማራኪ ቃላት ለመግለጽ እስኪነሳሱ ድረስ ምድራችን ይህን ያህል እንድታንጸባርቅ ያደረጋት ምንድን ነው? በላይዋ ላይ የሚገኘው ውኃ ነው! ሦስት አራተኛ የሚያህለውን የምድር ክፍል የሚሸፍነው ውኃ ፕላኔታችን ውበት እንድትላበስ ከማድረግ የበለጠ ጠቀሜታ አለው፤ ውኃ በምድር ላይ ያሉ ፍጥረታት በሕይወት እንዲቀጥሉ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል። እንዲያውም 65 በመቶ የሚሆነው የሰውነታችን ክፍል ውኃ ነው። በመሆኑም ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንዲህ ብሏል:- “[ውኃ] ዕፅዋትም ሆኑ እንስሳት በሚያካሂዱት በእያንዳንዱ ተፈጥሯዊ ሂደት ውስጥ ማለት ይቻላል የራሱ የሆነ ድርሻ ስላለው ለሕይወት እጅግ አስፈላጊ ነው።”

ውኃ ዑደት የሚያደርግበት የራሱ የሆነ መንገድ ስላለው ያልቃል ብለን መስጋት አይኖርብንም። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ብሏል:- “ጥቅም ላይ የሚውለው እያንዳንዱ የውኃ ጠብታ ማለት ይቻላል ወደ ውቅያኖስ ይገባል። ከዚያም በፀሐይ አማካኝነት ይተናል። በመጨረሻም በዝናብ መልክ ተመልሶ ወደ ምድር ይመጣል። በዚህ መንገድ በምድር ላይ ያለውን ውኃ መልሰን መላልሰን እንጠቀምበታለን። ውኃን የፈለግነውን ያህል ብንጠቀምበት ፈጽሞ አያልቅም።” መጽሐፍ ቅዱስ ይህን አስገራሚ ሂደት ከዛሬ 3,000 ዓመታት ገደማ በፊት እንዲህ ሲል ገልጾታል:- “ወንዞች ሁሉ ወደ ባሕር ይፈሳሉ፤ ባሕሩ ግን ፈጽሞ አይሞላም፤ ወንዞች ወደ መጡበት ስፍራ፣ ወደዚያ እንደ ገና ይመለሳሉ።” በእርግጥም የውኃ ዑደት ምንኛ አስደናቂ ነው!—መክብብ 1:7

ውኃ ለሕይወት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነና እንዴት ባለ አስደናቂ መንገድ ወደ እኛ እንደሚደርስ ተመልክተናል፤ በመሆኑም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ውኃ የሚናገር ሐሳብ ከ700 ጊዜ በላይ መገኘቱ ሊያስገርመን አይገባም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ የውኃን ዋና ዋና ጥቅሞች በተለይም ደግሞ በማንጻትና ሕይወት በማቆየት ረገድ የሚጫወተውን ትልቅ ሚና ከመንፈሳዊ ነገሮች ጋር በማያያዝ ይጠቀምበታል።—ኢሳይያስ 58:11፤ ዮሐንስ 4:14

መጽሐፍ ቅዱስ ያለው የማንጻት ኃይል

እስራኤላውያን አዘውትረው ገላቸውን ስለሚታጠቡና ዕቃዎቻቸውን ስለሚያጥቡ በአካላዊ ንጽሕናቸው ተለይተው ይታወቁ ነበር። አንድ ሰው ምግብ ለመመገብ ወደ ቤት ሲገባ እግሩን መታጠቡ የተለመደ ነበር። (ሉቃስ 7:44) እስራኤላውያን ውኃን የሚጠቀሙት ገላቸውንና ዕቃዎቻቸውን በንጽሕና ለመያዝ ብቻ ሳይሆን አምልኮ በሚያቀርቡበት ጊዜ የሚጠበቅባቸውን የንጽሕና ደረጃ ለማሟላት ጭምር ነበር። በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የሚያገለግሉት ካህናት አዘውትረው ገላቸውን መታጠብም ሆነ ልብሶቻቸውን ማጠብ ይጠበቅባቸው ነበር። (ዘፀአት 30:18-21) ከጊዜ በኋላ ደግሞ ሰሎሞን፣ ኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ውስጥ 44,000 ሊትር ውኃ የሚይዝ “በርሜል” አሠርቶ ነበር፤ ይህ ደግሞ በአምላክ ሕግ ውስጥ የሠፈረውን የንጽሕና ደረጃ ለማሟላት ያስችል ነበር። (2 ዜና መዋዕል 4:2, 6) ውኃ በዚህ መንገድ ጥቅም ላይ መዋሉ በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ ክርስቲያኖች ምን ትርጉም አለው?

ኢየሱስ የክርስቲያን ጉባኤን “በቃሉ አማካይነት በውሃ አጥቦ [እንዳነጻ]” ሐዋርያው ጳውሎስ ገልጿል። ውኃ አካላዊ ንጽሕናን ለመጠበቅ እንደሚያስችል ሁሉ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው እውነትም ሰዎችን በሥነ ምግባርም ሆነ በመንፈሳዊ ንጹሕ የማድረግ ኃይል አለው። የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት በዚህ መንገድ መንጻታቸው ‘ቅዱስና ነውር አልባ’ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል። (ኤፌሶን 5:25-27) በመሆኑም የአምላክን ሞገስ ለማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ በሥነ ምግባርም ይሁን በመንፈሳዊ “ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ” ሆነው ለመገኘት መጣር ይኖርባቸዋል። (2 ጴጥሮስ 3:11, 14) ታዲያ ይህን ጥረታቸውን ማሳካት እንዲችሉ የአምላክ ቃል የሚረዳቸው እንዴት ነው?

ይሖዋ አምላክን ማስደሰት የሚፈልጉ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረው በማጥናት መንፈሳዊውን ውኃ መጠጣት ይኖርባቸዋል። እነዚህ ሰዎች፣ ያገኙት እውቀት በአእምሯቸውና በልባቸው ላይ በጎ ተጽዕኖ ሲያሳድር የሚከተለውን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ ይነሳሳሉ:- “መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በአእምሮአችሁ መታደስ ተለወጡ።”—ሮሜ 12:2

እነዚህ ሰዎች የአምላክን ፈቃድ በትክክል ማወቃቸው በባሕርያቸውና በአስተሳሰባቸው ላይ ምን እንከን እንዳለ እንዲያስተውሉ ይረዳቸዋል። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወታቸው ውስጥ ተግባራዊ እያደረጉ ሲሄዱ የአምላክ ቃል ልክ እንደ ውኃ ከከባድ ኃጢአት እንኳ ሳይቀር ‘ያጥባቸዋል።’—1 ቆሮንቶስ 6:9-11

በስፔይን የሚኖረው አልፎንሶ ይህን ለውጥ በሕይወቱ ተመልክቷል። አልፎንሶ፣ “ከ18 ዓመቴ ጀምሮ በሕይወቴ ደስተኛ አልነበርኩም” በማለት ተናግሯል። አልፎንሶ የዕፅ ሱሰኛ የነበረ ከመሆኑም በላይ ልማደኛ ወንጀለኛ ነበር። እንዲህ ብሏል:- “ሕይወቴን የምመራበት መንገድም ሆነ ከሰዎች ጋር ያለኝ ግንኙነት ጥሩ ስላልነበር እንደረከስኩ ይሰማኝ ነበር።

“ትምህርት ቤት ሳለሁ ንጹሕ አለባበስ የነበራትና ቅንነት የሚነበብባት አንዲት ወጣት አስተዋልኩ፤ ይህ ደግሞ ከሌሎች የተለየች አድርጓት ነበር። የዚህች ወጣት አኗኗር ልክ እንደ እሷ ንጹሕ ሕይወት የመምራት ፍላጎት አሳደረብኝ። በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ እንድገኝ ያቀረበችልኝን ግብዣ ተቀበልኩ። ብዙም ሳይቆይ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የጀመርኩ ሲሆን ከአምላክ ጋርም ዝምድና መሠረትኩ። በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሕይወቴን አስተካክዬ ንጹሕ የሆነ አካሄድ በመከተል የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ። በሕይወቴ ውስጥ ያደረግኩትን አስገራሚ ለውጥ የተመለከቱ በአካባቢዬ የሚኖሩ በርካታ ወላጆች የዕፅ ሱሰኛ የሆኑ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ልጆቻቸውን እንድረዳላቸው ይጠይቁኝ ነበር።”

የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝ ውኃ

በአንድ ወቅት ኢየሱስ፣ ከያዕቆብ ጉድጓድ ውኃ ለመቅዳት ለመጣች ሳምራዊት ሴት ስለ “ሕይወት ውሃ” ነግሯት ነበር። ኢየሱስ እንዲህ ብሏታል:- “እኔ ከምሰጠው ውሃ የሚጠጣ ግን ከቶ አይጠማም፤ እኔ የምሰጠው ውሃ በውስጡ የሚፈልቅ የዘላለም ሕይወት ውሃ ምንጭ ይሆናል።” (ዮሐንስ 4:10, 14) ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ እንደሚጠቁመው ‘የሕይወት ውሃ’ የሰው ልጆች የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ አምላክ ያደረጋቸውን ዝግጅቶች ያመለክታል። እነዚህ ዝግጅቶች ደግሞ የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው ይገኛሉ። የዚህ ምሳሌያዊ ውኃ ዋነኛ ንጥረ ነገር የክርስቶስ ኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ነው። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአል።”—ዮሐንስ 3:16

ቀደም ሲል የተጠቀሰው አልፎንሶ ከአምላክ ያገኘው ‘የሕይወት ውሃ’ ምን ያህል ጥቅም እንዳለው ተገንዝቧል። በዕፅ ሱሰኝነታቸውና በወንጀል ድርጊታቸው የገፉበትን ሰዎች አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ታላቅ ወንድሜና የቀድሞ ጓደኞቼ ሁሉ ሞተዋል። ከአምላክ ቃል ያገኘሁት እውቀት ተመሳሳይ ዕጣ እንዳይደርስብኝ ረድቶኛል። ይሖዋ ባደረጋቸው መንፈሳዊ ዝግጅቶች በመጠቀሜ በሕይወት መቆየት ችያለሁ።” አልፎንሶ፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ በተማረው መሠረት አምላክ ቃል በገባው አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት የሚያገኝበትን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቃል።—2 ጴጥሮስ 3:13

ለሁሉም ሰው የቀረበ ግብዣ

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የመጨረሻ መጽሐፍ ‘ከአምላክና ከበጉ ዙፋን የሚወጣ እንደ መስተዋት የጠራ የሕይወት ውሃ ወንዝ’ የሚል አገላለጽ ይዟል። (ራእይ 22:1) ይህ ወንዝ፣ የሰው ልጆች ቀደም ሲል አዳምና ሔዋን ያጡትን ፍጹም ሕይወት መልሰው እንዲያገኙ የሚያስችሏቸውን አምላክ ያደረጋቸውን ዝግጅቶች ያመለክታል።

ይህ ጥቅስ ስለ ወንዙ ከተናገረ በኋላ “የተጠማም ሁሉ ይምጣ፤ የሚፈልግም ሁሉ የሕይወትን ውሃ በነጻ ይውሰድ” የሚል ግብዣ ያቀርባል። (ራእይ 22:17) በዛሬው ጊዜ ይህ ግብዣ በምድር ዙሪያ እየቀረበ ነው። ከ235 በላይ በሆኑ አገሮች ውስጥ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች፣ ሰዎች ሕይወት የሚያስገኘውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት እንዲያገኙ በመርዳት በየዓመቱ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ሰዓታትን ያሳልፋሉ።

አንተስ የሕይወት ውኃ ጠምቶሃል? ከሆነ፣ በምሳሌያዊ አነጋገር ይህን ንጹሕ ውኃ መጠጣት ማለትም ፈጣሪያችን ያደረጋቸውን ዝግጅቶች ማወቅና መጠቀም ትችላለህ። እንዲህ ማድረግህ ደግሞ “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት ያገኙ ዘንድ፣ ለሚመጣው ዘመን ጽኑ መሠረት የሚሆን ሀብት ለራሳቸው [ከሚያከማቹ]” ሰዎች መካከል ያስቆጥርሃል።—1 ጢሞቴዎስ 6:19

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ውኃ አካላዊ ንጽሕናን ለመጠበቅ እንደሚያስችል ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነትም ሰዎችን በሥነ ምግባርም ሆነ በመንፈሳዊ ንጹሕ የማድረግ ኃይል አለው

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ሰዎች ውኃ የሚያገኙት እንዴት ነበር?

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ሰዎች አስተማማኝ የሆነ የውኃ ምንጭ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ያደርጉ ነበር። አብርሃምና ይስሐቅ ለቤተሰቦቻቸውና ለመንጎቻቸው በቂ ውኃ ለማግኘት በቤርሳቤህ አቅራቢያ ጉድጓዶችን ቆፍረው ነበር።—ዘፍጥረት 21:30, 31፤ 26:18

ጥልቀት የሌላቸው ጉድጓዶች አብዛኛውን ጊዜ ለረጅም ወራት በሚዘልቀውና ሞቃታማ በሆነው የበጋ ወቅት ይደርቃሉ። አስተማማኝ የሆነ የውኃ አቅርቦት እንዲኖር ከተፈለገ አንድ ጉድጓድ በጥልቅ መቆፈር አለበት። (ምሳሌ 20:5) በለኪሶ የሚገኝ አንድ ጉድጓድ 44 ሜትር ጥልቀት አለው። በገባዖን የሚገኝ ሌላ ጉድጓድ ደግሞ 25 ሜትር ጥልቀትና 11 ሜትር ስፋት አለው። ይህን ጉድጓድ ለመቆፈር ወደ 30,000 ኩንታል የሚመዝኑ ድንጋዮችን ማውጣት አስፈልጎ ነበር። ከያዕቆብ የውኃ ጉድጓድ ውኃ ለመቅዳት የመጣችው ሳምራዊት ሴት ‘ጉድጓዱ ጥልቅ ነው’ በማለት ለኢየሱስ ነግራው ነበር። ምናልባትም በዚህ ጉድጓድ ውስጥ ያለው ውኃ የሚገኘው ከ23 ሜትር ጥልቀት በኋላ ሳይሆን አይቀርም።—ዮሐንስ 4:11

በጥንቱ ሩቅ ምሥራቅ፣ ሰዎች ጉድጓዶችን በመቆፈር ውኃ ያጠራቅሙ ነበር። ከጥቅምት እስከ ሚያዝያ የሚጥለው ዝናብ በእነዚህ ጉድጓዶች ውስጥ ይጠራቀም ነበር። በዝናብ ወቅት ከፍ ካሉ ቦታዎች የሚወርደው ውኃ ወደ ጉድጓዶቹ እንዲገባ ቦዮችን ያበጁ ነበር። እስራኤላውያንም ውኃ ለማጠራቀም ሰፋፊ ጉድጓዶችን ይቆፍሩ ነበር።—2 ዜና መዋዕል 26:10

ከጉድጓዶች ውስጥ ውኃ መቅዳት በጥንት ጊዜም ሆነ ዛሬ በጣም ከባድ ሥራ ነው። እንደ ርብቃና የዮቶር ልጆችን የመሳሰሉ ሴቶች ለቤተሰቦቻቸውና ለመንጎቻቸው በየዕለቱ ውኃ ከጉድጓድ በመቅዳት ይህን አስፈላጊ ሥራ ያከናውኑ ነበር።—ዘፍጥረት 24:15-20፤ ዘፀአት 2:16

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አልፎንሶ በአሁኑ ጊዜ፣ የአምላክን ቃል ለሰዎች ሲናገር