የምትወደው ሰው ሲሞት
የምትወደው ሰው ሲሞት
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 17, 2007 ከምሽቱ አንድ ሰዓት አካባቢ አንድ የመንገደኞች አውሮፕላን በብራዚል፣ ማዕከላዊ ሳኦ ፓውሎ የሚገኘውን አየር ማረፊያ መንደርደሪያ አስፋልት ስቶ ወጣ። አውሮፕላኑ ዋናውን መንገድ ጥሶ በመሄድ በአየር ማረፊያ ውስጥ ከሚገኘው መጋዘን ጋር ተጋጨ። በዚህ አደጋ 200 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
በብራዚል ታሪክ ውስጥ ከተከሰቱት የአውሮፕላን አደጋዎች ሁሉ አስከፊ ነው በተባለለት በዚህ አደጋ የሚወዱትን ሰው በሞት ያጡ ሰዎች፣ ሁኔታውን ፈጽሞ አይረሱትም። የሚወዱትን ሰው በአደጋው ካጡት ሰዎች መካከል ክላውዴቲ ትገኝበታለች። ስለ አደጋው የሰማችው ቴሌቪዥን እየተመለከተች ሳለ ነበር። በጥቅምት ወር ለማግባት ዝግጅት እያደረገ የነበረው የ26 ዓመቱ ልጇ ሬናቶ አውሮፕላኑ ውስጥ ነበር። በጣም የተደናገጠችው ክላውዴቲ ልጇን በሞባይል ለማግኘት ጥረት ብታደርግም ምንም ምላሽ አላገኘችም። ክላውዴቲ ተዝለፍልፋ መሬት ላይ በመውደቅ ምርር ብላ አለቀሰች።
በጥር 1986 አንትጂ አሳዛኝ በሆነ የመኪና አደጋ እጮኛዋን በሞት አጣች። ሁኔታውን ስትሰማ ከመጠን በላይ የደነገጠች ሲሆን በወቅቱ ምን ተሰምቷት እንደነበር ስትገልጽ እንዲህ ብላለች:- “በመጀመሪያ ነገሩን ማመን ከብዶኝ ነበር። መጥፎ ሕልም እያየሁ እንደሆነና ከእንቅልፌ ስባንን የማየው ሁሉ ውሸት እንደሆነ እረዳለሁ የሚል ስሜት ተሰምቶኝ ነበር። በጣም የተርበተበትኩ ከመሆኔም በላይ ሆዴን የረገጡኝ ያህል ከፍተኛ ሕመም ተሰማኝ።” አንትጂ ለቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት በመንፈስ ጭንቀት ተሠቃይታለች። አደጋው ከደረሰ ከ20 ዓመት በላይ ያለፈ ቢሆንም ያን ጊዜ የተከሰተውን ሁኔታ መለስ ብላ ስታስብ ውስጧ ይረበሻል።
እንደነዚህ ባሉ አሳዛኝ አደጋዎች ምክንያት የምንወደውን ሰው በድንገት በሞት ስናጣ ነገሩን አምኖ ለመቀበል የሚከብደን ከመሆኑም በላይ የሚሰማንን የድንጋጤና የተስፋ መቁረጥ ስሜት በቃላት መግለጽ አዳጋች ነው። የምንወደው ሰው ለረጅም ጊዜ በቆየበት ሕመም ሳቢያ እንደሚሞት ብናውቅም እንኳ ይህ ሰው ሲሞት የሚሰማን ሐዘን ቀላል አይደለም። ማንኛችንም ብንሆን የምንወደውን ሰው ሞት ሙሉ በሙሉ አምነን መቀበል አንችልም። የናንሲ እናት ለረጅም ጊዜ በሕመም ከተሠቃዩ በኋላ በ2002 አረፉ። ይሁንና ናንሲ እናቷ በሞቱበት ዕለት ከመደንገጧ የተነሳ ሆስፒታሉ ወለል ላይ ኩርምት ብላ ቁጭ አለች። ከዚያን ቀን ጀምሮ ሕይወት ትርጉም የለሽ ሆነባት። ይህ ከሆነ አምስት ዓመታት ያለፉ ቢሆንም ስለ እናቷ ስታስብ አሁንም ድረስ ታለቅሳለች።
ዶክተር ሃሊ ፕሪጀርሰን፣ “ሰዎች ሁኔታውን አምነው ቢቀበሉም ከሐዘናቸው ሙሉ በሙሉ መጽናናት ያስቸግራቸዋል” ብለዋል። አንተም በተመሳሳይ ለረጅም ጊዜ በቆየ ሕመም ሳቢያ አሊያም በድንገት የምትወደውን ሰው በሞት አጥተህ ከሆነ እንደሚከተለው ብለህ ትጠይቅ ይሆናል:- ‘ይህን ያህል ማዘኔ የጤና ነው? የምወደውን ሰው በሞት ማጣቴ ያስከተለብኝን ሐዘን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው? በሞት ያጣሁትን ሰው ዳግመኛ አገኘው ይሆን?’ የሚቀጥለው ርዕስ ለእነዚህና ልታነሳቸው ለምትችላቸው ሌሎች ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
EVERTON DE FREITAS/AFP/Getty Images