ይሖዋ የሚለው ስም በአዲስ ኪዳን ውስጥ መኖር አለበት?
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የአምላክ ስም መኖሩ ያን ያህል አስፈላጊ ነው? አምላክ፣ ስሙ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲኖር እንደሚፈልግ ጥርጥር የለውም። ቴትራግራማተን ተብለው በሚጠሩት አራት የዕብራይስጥ ፊደላት የሚወከለው የአምላክ ስም በተለምዶ ብሉይ ኪዳን ተብሎ በሚጠራው የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት በኩረ ጽሑፍ ውስጥ 7,000 ጊዜ ያህል ተጠቅሶ ይገኛል። *
የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን፣ የአምላክ የግል ስም በብሉይ ኪዳን ወይም በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ እንደሚገኝ ያምናሉ። ይሁንና ብዙዎቹ በተለምዶ አዲስ ኪዳን ተብሎ በሚጠራው የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ጥንታዊ ቅጂዎች ውስጥ እንደሌለ ይሰማቸዋል።
አንድ የአዲስ ኪዳን ጸሐፊ ቴትራግራማተን የሚገኝባቸውን ጥቅሶች ከብሉይ ኪዳን ላይ ወስዶ ሲጽፍ ምን ያደርጋል? በርካታ ተርጓሚዎች እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው የአምላክን የግል ስም ከመጻፍ ይልቅ “ጌታ” የሚለውን ቃል ይጠቀማሉ። የአዲስ ዓለም የቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም ግን ይህን አካሄድ አይከተልም። በመሆኑም በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ወይም በአዲስ ኪዳን ውስጥ ይሖዋ የሚለው ስም 237 ጊዜ ተጠቅሶ ይገኛል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች የአምላክን ስም በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከማስገባት ጋር በተያያዘ ምን ችግሮች ያጋጥሟቸዋል? በእነዚህ የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል ውስጥ የአምላክ ስም ሊኖር ይገባል ለማለት የሚያስችሉ ምን ምክንያቶች አሉ? የአምላክ ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መስፈሩስ ለአንተ ምን ትርጉም አለው?
በትርጉም ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮች
በእጃችን የሚገኙት የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት የመጀመሪያዎቹ ቅጂዎች አይደሉም። ማቴዎስ፣ ዮሐንስ፣ ጳውሎስና ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የጻፏቸው ጥንታዊ ቅጂዎች ለረጅም ጊዜ አገልግሎት ላይ በመዋላቸው ምክንያት አርጅተው እንደጠፉ ጥርጥር የለውም። በመሆኑም እነዚህን መጻሕፍት መገልበጥና ግልባጮቹ በሚያረጁበት ጊዜ ደግሞ ሌሎች ግልባጮችን ማዘጋጀት ያስፈልግ ነበር። በዛሬው ጊዜ ከሚገኙት በሺህ የሚቆጠሩ የአዲስ ኪዳን ቅጂዎች መካከል አብዛኞቹ የተጻፉት ቢያንስ የመጀመሪያዎቹ ቅጂዎች ከተጻፉ ከሁለት መቶ ዓመት በኋላ ነው። በዚያ ዘመን ቅዱሳን መጻሕፍትን ይገለብጡ የነበሩ ሰዎች ቴትራግራማተንን “ጌታ” የሚል ትርጉም ያለው ኩርዮስ ወይም ኪርዮስ በሚለው የግሪክኛ ቃል ተክተው አሊያም የአምላክን ስም በዚህ ቃል ከተኩት ቀደም ብለው ከተዘጋጁ ቅጂዎች ላይ ገልብጠው ሊሆን ይችላል። *
ይህን የሚያውቅ አንድ ተርጓሚ ቴትራግራማተን በጥንቶቹ የግሪክኛ ቅጂዎች ውስጥ ይገኝ እንደነበር የሚጠቁም አሳማኝ ማስረጃ መኖር አለመኖሩን ማረጋገጥ አለበት። ታዲያ እንዲህ ያለ ማስረጃ ማግኘት ይቻል ይሆን? እስቲ የሚከተሉትን ነጥቦች ተመልከት:-
-
ኢየሱስ ከብሉይ ኪዳን ሲጠቅስ ወይም ከዚያ ላይ ሲያነብ መለኮታዊውን ስም ተጠቅሟል። (ዘዳግም 6:13, 16፤ 8:3፤ መዝሙር 110:1፤ ኢሳይያስ 61:1, 2፤ ማቴዎስ 4:4, 7, 10፤ 22:44፤ ሉቃስ 4:16-21) ቴትራግራማተን በዛሬው ጊዜ ባሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ እንደሚገኘው ሁሉ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በኖሩበት ዘመንም በተለምዶ ብሉይ ኪዳን በሚባለው የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ይገኝ ነበር። ይሁን እንጂ ለብዙ ዘመናት፣ ምሑራን በግሪክኛው የሰብዓ ሊቃናት የብሉይ ኪዳንና የአዲስ ኪዳን ትርጉሞች ውስጥ ቴትራግራማተን እንደማይገኝ ያስቡ ነበር። ሆኖም በ20ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ በኢየሱስ ዘመን የነበሩ እጅግ ጥንታዊ የሆኑ የግሪክኛ ሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ቁርጥራጮች ተገኙ። በእነዚህ ቁርጥራጮች ላይ የአምላክን ስም የሚወክሉት የዕብራይስጥ ፊደላት መገኘታቸው የምሑራንን ትኩረት ስቧል።
-
ዮሐንስ 17:6, 11, 12, 26 የ1954 ትርጉም) ኢየሱስ ‘እኔ በአባቴ ስም መጥቼአለሁ’ በማለት በግልጽ ተናግሯል። በተጨማሪም ሁሉንም ነገሮች የሚሠራው ‘በአባቱ ስም’ እንደሆነ በአጽንኦት ገልጿል። እንዲያውም ኢየሱስ የሚለው ስም “ይሖዋ አዳኝ ነው” የሚል ትርጉም አለው።—ዮሐንስ 5:43፤ 10:25
ኢየሱስ በአምላክ ስም የተጠቀመ ሲሆን ይህንንም ስም ለሰዎች አሳውቋል። ( -
የመለኮታዊው ስም ምህጻረ ቃል በግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ይገኛል። በራእይ 19:1, 3, 4, 6 ላይ በሚገኘው “ሃሌ ሉያ!” የሚለው ሐረግ ውስጥ የመለኮታዊው ስም ምህጻረ ቃል ይገኛል። ይህ ሐረግ ቃል በቃል ሲተረጎም “እናንት ሕዝቦች ያህን አወድሱት!” ማለት ሲሆን ያህ ደግሞ ይሖዋ የሚለው ስም ምህጻረ ቃል ነው።
-
የጥንቶቹ የአይሁዳውያን ጽሑፎች፣ ክርስትናን የተቀበሉ አይሁዳውያን በጽሑፎቻቸው ውስጥ መለኮታዊውን ስም ይጠቀሙበት እንደነበር ያሳያሉ። የአይሁዳውያንን የቃል ሕጎች አሰባስቦ የያዘውና በ300 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ የተጠናቀቀው ዘ ቶሴፍታ የተባለው መጽሐፍ በሰንበት ስለተቃጠሉት የክርስቲያን ጽሑፎች እንደሚከተለው ብሏል:- “የወንጌላውያንና የሚኒም [አይሁዳውያን ክርስቲያኖች እንደሆኑ ይታመናል] መጻሕፍትን ከእሳት መታደግ አልተቻለም። መጻሕፍቱን በውስጣቸው ከሰፈረው መለኮታዊ ስም ጋር . . . አቃጥለዋቸው ነበር።” ይህ ጽሑፍ በሁለተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ መጀመሪያ ላይ ይኖር ስለነበረ ዮሲ ስለሚባል ረቢ ይጠቅሳል። ይህ የገሊላ ሰው ከሰንበት ውጪ ባሉ ቀናት መደረግ ስላለበት ነገር ሲናገር “አንድ ሰው መለኮታዊውን ስም ብቻ [ከክርስቲያን ጽሑፎች] ላይ ቀድዶ በማውጣት ከደበቀው በኋላ የቀረውን ያቃጥለዋል” ብሏል። በመሆኑም በሁለተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ይኖሩ የነበሩት አይሁዳውያን፣ ክርስቲያኖች በጽሑፎቻቸው ላይ የይሖዋን ስም መጠቀማቸውን ያምኑ እንደነበር የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ አለ።
በዚህ ረገድ ተርጓሚዎች ምን አድርገዋል?
በግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የአምላክን ስም ወደ ቀድሞ ቦታው እንዲመለስ ያደረገው መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲስ ዓለም ትርጉም ብቻ ነው? በፍጹም። ሌሎች በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎችም ቀደም ሲል በተገለጹት ምክንያቶች የተነሳ መለኮታዊው ስም በአዲስ ኪዳን ውስጥ መግባት እንዳለበት ያምናሉ።
ለምሳሌ ያህል፣ በአፍሪካ፣ በአሜሪካ፣ በእስያና በፓስፊክ ደሴቶች ውስጥ በሚነገሩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ በርካታ የአዲስ ኪዳን ትርጉሞች መለኮታዊውን ስም ብዙ ጊዜ ተጠቅመዋል። (በገጽ 21 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።) ከእነዚህ ትርጉሞች መካከል አንዳንዶቹ የተዘጋጁት በቅርብ ዓመታት ነው። ለምሳሌ ያህል፣ የሮቱማን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም (1999) በአዲስ ኪዳን ውስጥ በሚገኙ 48 ጥቅሶች ላይ ጂሆቫ የሚለውን ስም 51 ጊዜ በይሁዳ 14 ላይ ጂሆቫ የሚለውን ስም የተጠቀሙ ሲሆን 100 በሚያህሉ የግርጌ ማስታወሻዎችም ላይ የመለኮታዊው ስም አጠራር ይህ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።
ተጠቅሟል። በኢንዶኔዢያ በተዘጋጀው የባታክ-ቶባ ትርጉም (1989) ደግሞ ዬሆዋ የሚለው ስም በአዲስ ኪዳን ውስጥ 110 ጊዜ ይገኛል። መለኮታዊው ስም በፈረንሳይኛ፣ በጀርመንኛና በስፓንኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይም ይገኛል። ለአብነት ያህል፣ ፓብሎ ቤሶን በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ አዲስ ኪዳንን ወደ ስፓንኛ ተርጉመዋል።በአዲስ ኪዳን ውስጥ የአምላክን ስም ከተጠቀሙ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ አንዳንዶቹ ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል:-
-
በኸርማን ሃይንፌተር የተዘጋጀው ኤ ሊተራል ትራንስሌሽን ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት . . . ፍሮም ዘ ቴክስት ኦቭ ዘ ቫቲካን ማኑስክሪፕት (1863)
-
በቤንጃሚን ዊልሰን የተዘጋጀው ዚ ኢምፋቲክ ዳያግሎት (1864)
-
በጆርጅ ባርከር ስቲቨንስ የተዘጋጀው ዚ ኢፒስትልስ ኦቭ ፖል ኢን ሞደርን ኢንግሊሽ (1898)
-
በዊልያም ራዘርፎርድ የተዘጋጀው ሴይንት ፖልስ ኢፒስትል ቱ ዘ ሮማንስ (1900)
-
በጆርጅ ለፈቭር የተዘጋጀው ዘ ክሪስቺያንስ ባይብል—ኒው ቴስታመንት (1928)
-
የለንደን ጳጳስ በነበሩት በዊልያም ዋንድ የተዘጋጀው ዘ ኒው ቴስታመንት ሌተርስ (1946)
በቅርቡ የወጣውና በብዙዎች ዘንድ የሚታወቀው ኒው ሊቪንግ ትራንስሌሽን (የ2004 እትም) በመቅድሙ ላይ “የመለኮታዊው ስም አተረጓጎም” በሚለው ርዕስ ሥር የሚከተለውን ሐሳብ አስፍሯል:- “በርካታ የእንግሊዝኛ ትርጉሞች እንደሚያደርጉት ቴትራግራማተን (የሐወሐ) በሚገኝባቸው ቦታዎች ላይ ሁሉ ‘ጌታ’ (the LORD) የሚለው ቃል ተጠቅመናል። ይህ ደግሞ ‘ጌታ’ (Lord) ተብሎ ከተተረጎመው አዶናይ ከተባለው ስም ለመለየት ያስችላል።” አክሎም አዲስ ኪዳንን አስመልክቶ ሐሳብ ሲሰጥ እንዲህ ብሏል:- “ኩርዮስ የሚለው የግሪክኛ ቃል በሁሉም ቦታዎች ላይ ‘ጌታ’ (Lord) ተብሎ የተተረጎመ ቢሆንም በአዲስ ኪዳን ላይ ከብሉይ ኪዳን የተወሰዱ ጥቅሶች ሲኖሩ ‘ጌታ’ (LORD) በሚለው ቃል ተጠቅመናል።” (በሰያፍ የጻፍናቸው እኛ ነን።) በመሆኑም ይህን መጽሐፍ ቅዱስ የተረጎሙ ሰዎች በአዲስ ኪዳን ውስጥ ቴትራግራማተንን (የሐወሐ) የሚወክል ቃል መኖር አለበት በሚለው ሐሳብ እንደሚስማሙ ተናግረዋል።
ዚ አንከር ባይብል ዲክሽነሪ “በአዲስ ኪዳን ውስጥ የሚገኘው ቴትራግራማተን” በሚል ርዕስ ያሰፈረው የሚከተለው ሐሳብ ትኩረት የሚስብ ነው:- “ጥንታዊ በሆኑት የአዲስ ኪዳን ቅጂዎች ላይ የሚገኙት ከብሉይ ኪዳን በተወሰዱ በአንዳንድ ወይም በሁሉም ጥቅሶች ላይ ያህዌህ የሚለውን መለኮታዊ ስም የሚወክለው ቴትራግራማተን ይገኝ እንደነበር አንዳንድ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ።” ከዚህም በተጨማሪ ጆርጅ ሃዋርድ የተባሉ ምሑር እንዲህ ብለዋል:- “ቴትራግራም፣ የጥንት ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን መጻሕፍት መሠረት በሆነው በግሪክኛ መጽሐፍ ቅዱስ [የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም] ቅጂዎች ላይ አሁንም የሚገኝ በመሆኑ የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ከቅዱሳን መጻሕፍት ሲጠቅሱ ቴትራግራምን ይጠቀሙ ነበር ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው።”
ሁለት አሳማኝ ምክንያቶች
ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው በአዲስ ኪዳን ውስጥ የአምላክን ስም የተጠቀመው የአዲስ ዓለም ትርጉም ብቻ አይደለም። አንድ ዳኛ የዓይን ምሥክሮች የሌሉበት የፍርድ ጉዳይን ሲያይ እንደሚያደርገው ሁሉ የአዲስ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ኮሚቴ አባላትም ጠቃሚ ማስረጃዎችን በሙሉ በጥንቃቄ መርምረዋል። ከዚያም ባሉት ተጨባጭ ማስረጃዎች ላይ ተመርኩዘው የይሖዋን ስም በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ለማካተት ወሰኑ። እንዲህ ለማድረግ ያነሳሳቸውን ሁለት አሳማኝ ምክንያቶች ተመልከት።
(1) ተርጓሚዎቹ የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት፣ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ቀጣይ ክፍል እንደመሆናቸው መጠን የይሖዋ ስም በውስጣቸው አለመኖሩ መጽሐፍ ቅዱስን ወጥነት የጎደለው እንደሚያስመስለው ተሰምቷቸዋል።
ተርጓሚዎቹ የደረሱበት መደምደሚያ ምክንያታዊ ነው የምንለው ለምንድን ነው? በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ አጋማሽ ገደማ ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ በኢየሩሳሌም ለሚገኙ ሽማግሌዎች እንዲህ ብሎ ነበር:- “እግዚአብሔር ለስሙ የሚሆንን ወገን ከአሕዛብ ይወስድ ዘንድ አስቀድሞ እንዴት እንደ ጐበኘ ስምዖን ተርኮአል።” (የሐዋርያት ሥራ 15:14 የ1954 ትርጉም) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ሰዎች የአምላክን ስም የማያውቁ ወይም በስሙ የማይጠቀሙ ቢሆኑ ኖሮ ያዕቆብ እንዲህ ማለቱ ምክንያታዊ ይመስልሃል?
(2) ከጊዜ በኋላ የተገኙት የሰብዓ ሊቃናት ቅጂዎች ኪሪዮስ (ጌታ) ከሚለው ቃል ይልቅ የአምላክን መለኮታዊ ስም ተጠቅመዋል። በመሆኑም ተርጓሚዎች፣ በኢየሱስ ዘመን የነበሩ የግሪክኛም ሆኑ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት መለኮታዊው ስም ይጠቀሙ ነበር የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል።
መለኮታዊውን ስም ከግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የማውጣት ልማድ የተስፋፋው ከኢየሱስ ዘመን በኋላ ሳይሆን አይቀርም። አንተስ ምን ትላለህ? ኢየሱስም ሆነ ሐዋርያቱ አምላክን የማያስከብረውን ይህን ልማድ የደገፉ ይመስልሃል?—ማቴዎስ 15:6-9
“የይሖዋን ስም” መጥራት
የጥንት ክርስቲያኖች በተለይ የአምላክን ስም የያዙ ጥቅሶችን ከብሉይ ኪዳን ላይ ሲጠቅሱ የይሖዋን ስም ይጠቀሙ እንደነበር ቅዱሳን መጻሕፍት በግልጽ ያሳያሉ። በመሆኑም የአዲስ ዓለም ትርጉም ይሖዋ የሚለውን መለኮታዊ ስም በግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ያስገባበት ጠንካራ ምክንያቶች አሉ።
ይህ ለአንተ ምን ትርጉም አለው? ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ይኖሩ ለነበሩት ክርስቲያኖች፣ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ላይ በመጠቀስ “የጌታን [“የይሖዋን፣” NW] ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” ብሏቸዋል። ከዚያም የሚከተሉትን ጥያቄዎች አቅርቧል:- “ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ስለ እርሱስ ሳይሰሙ እንዴት ያምኑበታል?” (ሮሜ 10:13, 14፤ ኢዩኤል 2:32) የአምላክን ስም በተገቢው ቦታ ላይ የሚጠቀሙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን ማንበብህ ይበልጥ ወደ አምላክ እንድትቀርብ ይረዱሃል። (ያዕቆብ 4:8) ይሖዋ የተባለውን የአምላክን ስም ማወቅና መጥራት መቻል በእርግጥም እጅግ ታላቅ መብት ነው!