ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?
የገንዘብ አያያዝ
ባል፦ “ባለቤቴ ሎረ * የማያስፈልጉ ነገሮችን፣ ማለቴ እኔ ያስፈልጉናል ብዬ የማላምንባቸውን ነገሮች በመግዛት ገንዘብ እንደምታባክን ይሰማኛል። ገንዘብ ማጠራቀም አይሆንላትም! በዚህም ምክንያት ያልተጠበቀ ወጪ በሚያጋጥመን ጊዜ በጣም እንቸገራለን። ብዙ ጊዜ እንደምናገረው ሚስቴ ገንዘብ ይዛ ከወጣች የምትመለሰው ባዶ እጇን ነው።”
ሚስት፦ “ገንዘብ አላጠራቅም ይሆናል። ይሁን እንጂ ባለቤቴ ምግብና የቤት ቁሳቁሶችን ለመግዛት እንዲሁም የቤት ወጪዎችን ለመሸፈን ምን ያህል ገንዘብ እንደሚያስፈልግ አያውቅም፤ ምክንያቱም አብዛኛውን ጊዜ ቤት ውስጥ የምውለው እኔ ነኝ። እኔ ምን ነገር እንደሚያስፈልገን ስለማውቅ በኋላ ላይ ከባለቤቴ ጋር ገንዘብን በተመለከተ ንትርክ ውስጥ እንደሚከተን ባውቅም ዕቃውን እገዛዋለሁ።”
ባለትዳሮች ተረጋግተው መነጋገር እንዲከብዳቸው ከሚያደርጉት ርዕሰ ጉዳዮች መካከል አንዱ ገንዘብ ነው። አብዛኛውን ጊዜ በትዳር ውስጥ ለሚፈጠሩ አለመግባባቶች ዋነኛው መንስኤ ገንዘብ መሆኑ ምንም አያስገርምም።
ለገንዘብ ሚዛናዊ አመለካከት የሌላቸው ባለትዳሮች ውጥረትና የስሜት ቀውስ ሊያጋጥማቸው፣ እርስ በርስ መስማማት ሊያቅታቸው አልፎ ተርፎም መንፈሳዊነታቸው ሊጎዳ ይችላል። (1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) ገንዘባቸውን በአግባቡ የማይጠቀሙ ወላጆች ብዙ ሰዓት ለመሥራት ይገደዱ ይሆናል፤ ይህ ደግሞ ልጆቻቸው ከወላጆቻቸው እንዲሁም ባልና ሚስቱ አንዳቸው ከሌላው ማግኘት የሚገባቸውን ስሜታዊም ሆነ መንፈሳዊ ድጋፍ እንዲያጡ ያደርጋቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ እንዲህ ያሉ ወላጆች ልጆቻቸው ለገንዘብ ምክንያታዊ የሆነ አመለካከት እንዳይኖራቸው ያደርጓቸዋል።
መጽሐፍ ቅዱስ “ገንዘብ ጥላ ከለላ [ነው]” በማለት ይናገራል። (መክብብ 7:12) ይሁንና ገንዘብ ለትዳርህም ሆነ ለቤተሰብህ ጥላ ከለላ መሆኑ የተመካው ገንዘብን እንዴት መያዝ እንዳለብህ በማወቅህ ላይ ብቻ ሳይሆን ከትዳር ጓደኛህ ጋር በገንዘብ ጉዳዮች ረገድ እንዴት መነጋገር እንዳለብህ በመገንዘብህ ጭምር ነው። * እንዲያውም ገንዘብ ነክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚደረጉት ውይይቶች ባለትዳሮች እርስ በርስ እንዲጨቃጨቁ ሳይሆን ግንኙነታቸውን ይበልጥ እንዲያጠናክሩ የሚረዱ አጋጣሚዎች ሊሆኑ ይችላሉ።
ታዲያ ገንዘብ በትዳር ውስጥ በርካታ ችግሮች እንዲነሱ ምክንያት የሚሆነው ለምንድን ነው? ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ችግሮች በሚነሱበት ወቅት ከመነታረክ ይልቅ ችግሩን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት ምን ጠቃሚ እርምጃዎችን መውሰድ ትችላላችሁ?
ተፈታታኝ የሚያደርጉት ነገሮች
አብዛኛውን ጊዜ ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ለሚነሱት ችግሮች መንስኤው ገንዘቡ ሳይሆን ባልና ሚስቱ በገንዘብ አያያዝ ረገድ እርስ በርስ አለመተማመናቸው አሊያም ወደፊት ምን ያጋጥመን ይሆን የሚለው ፍርሃት ነው። ለምሳሌ አንድ ባል፣ ሚስቱ ያወጣችውን ወጪ አንድ በአንድ ማወቅ የሚፈልግ ከሆነ ባለቤቱ የቤተሰቡን ገንዘብ በተገቢው መንገድ የመያዝ ችሎታ የላትም ብሎ እንደሚያምን መናገሩ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም አንዲት ሚስት ባለቤቷ በቂ ገንዘብ እንደማያጠራቅም በመግለጽ የምታማርር ከሆነ ወደፊት አንድ ነገር ቢከሰት ቤተሰቡ የገንዘብ ችግር እንደሚገጥመው ፍርሃት እንዳላት መግለጿ ሊሆን ይችላል።
ባለትዳሮች ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ችግር በሚነሳበት ጊዜ ሰላማዊ ውይይት እንዳያደርጉ እንቅፋት የሚሆንባቸው ሌላው ተፈታታኝ ነገር ያደጉበት መንገድ ነው። በትዳር ዓለም ለስምንት ዓመታት የኖረው ማቲው እንዲህ ብሏል፦ “ባለቤቴ ያደገችው ገንዘብን በሥርዓት በሚይዝ ቤተሰብ ውስጥ ነው። እሷ
የእኔ ዓይነት ስጋት የለባትም። አባቴ የአልኮል ሱሰኛ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ያለማቋረጥ ያጨስ ነበር፤ ከዚህም በላይ ለረጅም ጊዜ ሥራ አጥ ሆኖ ቆይቶ ነበር። ለብዙ ጊዜ የሚያስፈልገንን ነገር ሳናገኝ ኖረናል፤ በዚህም ምክንያት ዕዳ ውስጥ መግባት በጣም ያስፈራኛል። እንዲህ ዓይነቱ ፍርሃት፣ አንዳንድ ጊዜ ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ከባለቤቴ ጋር ስነጋገር ምክንያታዊ ያልሆኑ ሐሳቦችን እንድሰነዝር ያደርገኛል።” በመካከላችሁ ለተፈጠረው ውጥረት መንስኤው ምንም ይሁን ምን ገንዘብ ትዳራችሁን የሚደግፍ እንጂ የሚያፈርስ እንዳይሆን ምን ማድረግ ትችላላችሁ?ለአንተ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር ምንድን ነው?—ገንዘብ ወይስ ትዳርህ?
ስኬታማ እንድትሆኑ የሚረዷችሁ አራት ቁልፎች
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ስለ ገንዘብ አያያዝ ለማስተማር ታቅዶ የተዘጋጀ መጽሐፍ አይደለም። ይሁንና ባለትዳሮች ከገንዘብ ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች መፍታት እንዲችሉ የሚረዳ ጥበብ ያዘለ ምክር ይሰጣል። ታዲያ ይህን ምክር ለምን አትመረምሩም? እስቲ ከዚህ በታች የቀረቡትን የመፍትሔ ሐሳቦች በተግባር ለማዋል ጥረት አድርጉ።
1. ስለ ገንዘብ ስትወያዩ በእርጋታ መነጋገርን ተማሩ።
“ጥበብ ግን ምክርን በሚቀበሉ ዘንድ ትገኛለች።” (ምሳሌ 13:10) በአስተዳደጋችሁ ምክንያት ከገንዘብ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በተመለከተ ሌሎች ሰዎችን በተለይም የትዳር ጓደኛችሁን ማማከር ያሳፍራችሁ ይሆናል። ያም ሆኖ አስፈላጊ ስለሆነው ስለዚህ ርዕሰ ጉዳይ አንስታችሁ መወያየት የምትችሉት እንዴት እንደሆነ መማራችሁ የጥበብ አካሄድ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ቤተሰቦችህ ለገንዘብ ባለህ አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ያሳደሩብህ እንዴት እንደሆነ ለባለቤትህ ለምን አትነግራትም? በተጨማሪም የትዳር ጓደኛህ ያደገችበት መንገድ ለገንዘብ ባላት አመለካከት ላይ ምን ተጽዕኖ እንዳሳደረባት ለመረዳት ሞክር።
በገንዘብ ዙሪያ ለመወያየት ችግሮች እስኪነሱ ድረስ መጠበቅ አያስፈልጋችሁም። መጽሐፍ ቅዱስን ከጻፉት ሰዎች መካከል አንዱ “ሁለት ሰዎች አብረው ለመሄድ ካልተቀጣጠሩ በቀር በአንድነት ለመሄድ ይችላሉን?” በማለት ጠይቆ ነበር። (አሞጽ 3:3 የታረመው የ1980 ትርጉም) ይህ መሠረታዊ ሥርዓት በተግባር ሊውል የሚችለው እንዴት ነው? ከገንዘብ ጋር ስለተያያዙ ጉዳዮች ለመወያየት የተወሰነ ሰዓት የምትመድቡ ከሆነ የትዳር ጓደኛችሁን በተሳሳተ መንገድ ተረድታችሁ ወደ ንትርክ እንዳትገቡ ይረዳችኋል።
እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ ስለ ቤተሰብ ወጪ ለመወያየት ቋሚ ጊዜ መድቡ። ወሩ በገባ በመጀመሪያው ቀን ወይም በሳምንቱ ውስጥ የተወሰነ ቀን ላይ መወያየት ትችላላችሁ። ውይይታችሁን አጭር አድርጉት፤ ምናልባትም ከ15 ደቂቃ ባይበልጥ ጥሩ ሊሆን ይችላል። ሁለታችሁም ዘና የምትሉበትን ጊዜ ምረጡ። በተጨማሪም ከቤተሰባችሁ ጋር ማዕድ ላይ ስትቀመጡ ወይም ከልጆቻችሁ ጋር ስትዝናኑ አሊያም እነዚህን በመሳሰሉ ሌሎች ወቅቶች ላይ ስለ ገንዘብ አንስታችሁ ላለመወያየት ወስኑ።
2. ገቢያችሁን በተመለከተ ትክክለኛው አመለካከት ይኑራችሁ።
“አንዳችሁ ሌላውን ለማክበር ቀዳሚ ሁኑ።” (ሮም 12:10) ደሞዝ የምታገኘው አንተ ብቻ ከሆንክ ገንዘቡ የአንተ ብቻ ሳይሆን የመላው ቤተሰብ ጭምር እንደሆነ አድርገህ በመመልከት ባለቤትህን እንደምታከብራት ማሳየት ትችላለህ።—1 ጢሞቴዎስ 5:8
አንተም ሆንክ ባለቤትህ ደሞዝ የምታገኙ ከሆነ ገቢያችሁ ስንት እንደሆነና ከበድ ያሉ ወጪዎችን ጨምሮ ምን ያህል ገንዘብ ማውጣት እንደምትችሉ በመነጋገር እርስ በርስ እንደምትከባበሩ ማሳየት ትችላላችሁ። እነዚህን ነገሮች ከትዳር ጓደኛችሁ የምትደብቁ ከሆነ በመካከላችሁ መተማመን ይጠፋል ብሎም ግንኙነታችሁ ይበላሻል። ልታወጧት ስላሰባችኋት ስለ እያንዳንዷ ሳንቲም የትዳር ጓደኛችሁን ማማከር አያስፈልጋችሁም። ይሁንና ከበድ ያለ ወጪ ለማድረግ በምታስቡበት ጊዜ እርስ በርስ መወያየታችሁ የትዳር ጓደኛችሁን አመለካከት እንደምታከብሩ ያሳያል።
እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ አንዳችሁ ሌላውን ሳታማክሩ ምን ያህል ገንዘብ ማውጣት እንደምትችሉ ተነጋግራችሁ ወስኑ፤ ለምሳሌ 20 ብር ወይም 200 ብር አሊያም ሌላ የተወሰነ ገንዘብ ልትመድቡ ትችላላችሁ። ከተስማማችሁት ገንዘብ በላይ ወጪ ማድረግ ስትፈልጉ ምንጊዜም የትዳር ጓደኛችሁን አማክሩ።
3. እቅዳችሁን በጽሑፍ አስፍሩ።
“የትጉህ ሰው ዕቅድ ወደ ትርፍ ያመራል።” (ምሳሌ 21:5) በትጋት የሠራኸው ሥራ ከንቱ እንዳይቀር ለማድረግ ለወደፊቱ ጊዜ እቅድ ማውጣት የምትችልበት አንዱ መንገድ ለቤተሰብህ በጀት ማውጣት ነው። በትዳር ዓለም ለአምስት ዓመታት የቆየችው ኒነ እንዲህ ብላለች፦ “ገቢያችሁንና ወጪያችሁን የመዘገባችሁበትን ወረቀት መመልከታችሁ ሁኔታችሁን በግልጽ ለማወቅ ስለሚያስችላችሁ በጣም ትገረሙ ይሆናል። ወረቀቱ ላይ የሰፈረው አኃዝ ከሚነግራችሁ ሐቅ መሸሽ አትችሉም።”
በጀት የምታወጡበት መንገድ ውስብስብ መሆን አያስፈልገውም። ለ26 ዓመታት በትዳር ዓለም የቆየውና የሁለት ወንድ ልጆች አባት የሆነው ዳረን እንዲህ ብሏል፦ “መጀመሪያ ላይ የተለያዩ ፖስታዎችን እንጠቀም ነበር። በሳምንት ውስጥ የሚያስፈልገንን ገንዘብ በተለያዩ ፖስታዎች ውስጥ እናስቀምጣለን። ለምሳሌ ያህል፣ የምግብና የመዝናኛ ሌላው ቀርቶ የፀጉር መስተካከያ ገንዘብ የምናስቀምጥበት
ፖስታ ነበረን። በአንደኛው ፖስታ ውስጥ ያለው ገንዘብ ካለቀ ከሌላኛው ፖስታ እንበደራለን፤ ይሁን እንጂ ሁልጊዜም በተቻለን ፍጥነት ገንዘቡን እንመልሳለን።” በተለይ ክፍያ የምትፈጽሙት በጥሬ ገንዘብ ካልሆነ በጀት ማውጣታችሁና ወጪያችሁን በጥንቃቄ መመዝገባችሁ በጣም አስፈላጊ ነው።እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ ቋሚ ወጪዎቻችሁን በሙሉ በጽሑፍ አስፍሩ። ከገቢያችሁ ውስጥ ምን ያህሉን ማጠራቀም እንዳለባችሁ ወስኑ። ቀጥሎም ለምግብ፣ ለመብራት እንዲሁም ለስልክ የምታወጡትን ጨምሮ በየጊዜው ሊለዋወጡ የሚችሉ ወጪዎችን ግምት በዝርዝር አስፍሩ። ከዚያም ለተወሰኑ ወራት ያህል ያወጣችሁትን ወጪ በሙሉ መዝግባችሁ ያዙ። አስፈላጊ ሆኖ ካገኛችሁት በአኗኗራችሁ ላይ ለውጥ አድርጉ፤ ይህ ደግሞ ዕዳ ውስጥ እንዳትዘፈቁ ይረዳችኋል።
4. ማን ምን ማድረግ እንዳለበት ተነጋገሩ።
“ለሥራቸው መልካም ውጤት ስለሚያገኙ፣ ከአንድ፣ ሁለት መሆን ይሻላል።” (መክብብ 4:9, 10) በአንዳንድ ቤተሰቦች ውስጥ ገንዘብ የሚይዘው ባል ነው። በሌሎች ቤተሰቦች ውስጥ ደግሞ ሚስት ይህን ኃላፊነት በብቃት ትወጣለች። (ምሳሌ 31:10-28) ያም ሆኖ ብዙ ባልና ሚስቶች ኃላፊነቱን መከፋፈል ይመርጣሉ። ለ21 ዓመታት በትዳር ዓለም የቆየው ማርዮ እንዲህ ብሏል፦ “ባለቤቴ አንዳንድ ወርሃዊ ወጪዎችንና ትንንሽ ወጪዎችን ተከታትላ ትከፍላለች፤ እኔ ደግሞ ግብር፣ ብድርና ኪራይ እከፍላለሁ። እነዚህን ወጪዎች ስናደርግ የምንነጋገር ሲሆን ሥራውን ተደጋግፈን እንሠራለን።” የምትጠቀሙበት ዘዴ ምንም ይሁን ምን ቁልፍ የሆነው ነገር ተባብራችሁ መሥራታችሁ ነው።
እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ እያንዳንዳችሁ ያላችሁን ጠንካራና ደካማ ጎን ከለያችሁ በኋላ ማን የትኛውን ኃላፊነት ቢሸከም የተሻለ እንደሚሆን ተነጋገሩ። ከጥቂት ወራት በኋላ ሥራችሁን ገምግሙ። ማስተካከያ ለማድረግ ፈቃደኞች ሁኑ። የትዳር ጓደኛህ እያከናወነች ያለችውን ወርሃዊ ወጪ እንደመክፈልና ገበያ እንደ መውጣት ያሉ ሥራዎችን ማድነቅ እንድትችል አልፎ አልፎ ኃላፊነታችሁን ተለዋወጡ።
ውይይታችሁ ምን ያሳያል?
በገንዘብ ዙሪያ የምታደርጉት ውይይት ፍቅራችሁን ሊያቀዘቅዘው አይገባም። በትዳር ዓለም ለአምስት ዓመት የኖረችው ሊአ የዚህን እውነተኝነት በሕይወቷ ተመልክታለች። እንዲህ ብላለች፦ “እኔና ባለቤቴ ገንዘብን በተመለከተ በግልጽና በሐቀኝነት እንዴት መነጋገር እንደምንችል ተምረናል። በዚህም ምክንያት በአሁኑ ወቅት ተባብረን የምንሠራ ሲሆን ፍቅራችን ይበልጥ ተጠናክሯል።”
የትዳር ጓደኛሞች ገንዘባቸውን እንዴት ማውጣት እንደሚፈልጉ በሚወያዩበት ጊዜ አንዳቸው ለሌላው ተስፋቸውንና ሕልማቸውን እያጋሩ ብሎም ለትዳራቸው ታማኝ መሆናቸውን እያሳዩ ነው። ከበድ ያለ ወጪ ከማድረጋቸው በፊት መመካከራቸው አንዳቸው የሌላውን አመለካከትና ስሜት እንደሚያከብሩ ያሳያል። አንደኛው የትዳር ጓደኛ ሌላኛውን ሳያማክር የተወሰነ ገንዘብ እንዲያወጣ ነፃነት ማግኘቱ ባልና ሚስቱ እርስ በርስ እንደሚተማመኑ የሚያሳይ ነው። ከላይ የተገለጹት ባሕርያት፣ በፍቅር የታሠረ እውነተኛ ወዳጅነት ለመመሥረት አስፈላጊ ናቸው። እንዲህ ያለው ወዳጅነት ከገንዘብ የበለጠ ዋጋ እንዳለው ግልጽ ነው፤ ታዲያ በገንዘብ ጉዳይ ለምን ትጨቃጨቃላችሁ?
^ አን.3 ስሞቹ ተቀይረዋል።
^ አን.7 መጽሐፍ ቅዱስ “ባልም የሚስቱ ራስ ነው” ይላል። በመሆኑም አንድ ባል የሚከተሉትን ሁለት አስፈላጊ ኃላፊነቶች የመወጣት ግዴታ አለበት፤ ይኸውም የቤተሰቡ ገንዘብ ምን ላይ ሊውል እንደሚገባ መወሰንና ባለቤቱን ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ፍቅር መያዝ ይኖርበታል።—ኤፌሶን 5:23, 25
ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ . . .
-
እኔና ባለቤቴ ገንዘብ ነክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለመጨረሻ ጊዜ ሰላማዊ በሆነ መንገድ የተነጋገርነው መቼ ነው?
-
የትዳር ጓደኛዬ ለቤተሰባችን የሚያደርገውን የገንዘብ ድጋፍ በተመለከተ ያለኝን አድናቆት ለመግለጽ በንግግርም ሆነ በተግባር ምን ማድረግ እችላለሁ?