ይህን ያውቁ ኖሯል?
ይህን ያውቁ ኖሯል?
ኢየሱስ ሳኦልን “መውጊያውን መራገጥህን ከቀጠልክ ለአንተው የባሰ ይሆንብሃል” ሲለው ምን ማለቱ ነው?—የሐዋርያት ሥራ 26:14
▪ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ገበሬዎች በሚያርሱበት ጊዜ ከብቶቻቸውን ለመምራት መውጊያ ወይም መንጃ ይጠቀሙ ነበር። መውጊያ፣ ርዝመቱ ምናልባት እስከ 2.5 ሜትር ሊደርስ የሚችል ጫፉ ሹል የሆነ ዘንግ ነው። በአንደኛው ጫፍ ላይ እንደ ጦር ያለ ብረት ይገጠምለት ነበር። እንስሳው መውጊያውን የሚራገጥ ከሆነ የሚጎዳው ራሱን ነው። በሌላኛው ጫፍ ላይ ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ እንደ መሮ ያለ ጠፍጣፋ ብረት የሚገጠምለት ሲሆን ማረሻው ላይ የሚጣበቀውን አፈር ለማስለቀቅ ያገለግል ነበር።
መውጊያ እንደ ጦር መሣሪያ ሆኖ ያገለገለባቸው ጊዜያትም ነበሩ። ለምሳሌ የእስራኤል መስፍንና ተዋጊ የነበረው ሰሜጋር 600 ፍልስጥኤማውያንን የገደለው “በበሬ መንጃ” ነበር።—መሳፍንት 3:31
በተጨማሪም በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ይህ መሣሪያ ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ተሠርቶበታል። ለምሳሌ ንጉሥ ሰለሞን አንድ ወዳጁ ትክክለኛ ውሳኔ እንዲያደርግ የሚጎተጉት ጠቢብ ሰው የሚናገረው ቃል ሹል ከሆነ “የከብት መንጃ” ጋር ሊመሳሰል እንደሚችል ጽፏል።—መክብብ 12:11
ኢየሱስ ትንሣኤ አግኝቶ ወደ ሰማይ ከሄደ በኋላ ተመሳሳይ የሆነ ምሳሌያዊ አገላለጽ ተጠቅሟል። ክርስቲያኖችን ያሳድድ ለነበረው ለሳኦል ‘መውጊያውን መራገጡን’ እንዲተው ምክር ሰጥቶታል። ይህ አገላለጽ ባለቤቱ የሚሰጠውን መመሪያ ለመቀበል አሻፈረኝ የሚልን አንድ እልኸኛ እንስሳ እንድናስብ ያደርገናል። ደስ የሚለው ነገር ሳኦል ኢየሱስ የሰጠውን ምክር ተቀብሎ አኗኗሩን በመለወጥ ሐዋርያ መሆን ችሏል።
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አይሁዳውያን ምሽት ላይ ሰዓት የሚቆጥሩት እንዴት ነበር?
▪ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. አይሁዳውያን ቀን ላይ ሰማዩ ጥርት ያለ በሚሆንበት ጊዜ በጥላ ተጠቅመው ሰዓት መቁጠር ይችሉ ነበር። ሆኖም ፀሐይዋን ደመና በሚጋርዳት ወይም ምሽት በሚሆንበት ጊዜ ክሌፕስድረ (የውኃ ሰዓት) ይጠቀማሉ። ከአይሁዳውያን በተጨማሪ ግብፃውያን፣ ፋርሳውያን፣ ግሪካውያንና ሮማውያን በዚህ መሣሪያ ይጠቀሙ ነበር።
ዘ ጂዊሽ ኢንሳይክሎፒዲያ እንደገለጸው ከሆነ ሚሽናም ሆነ ታልሙድ ክሌፕስድረን የሚጠሩት “በተለያየ መንገድ ሲሆን ምናልባትም ይህ የሆነው አንዱ ከሌላው ያለውን የቅርጽና የንድፍ ልዩነት ለማመልከት ሊሆን ይችላል፤ ይሁንና ሁሉም ስያሜዎች አንድን ነገር ይኸውም ውኃው ጠብ ጠብ እያለ በቀስታ መውጣቱን፣ ቃል በቃል ከተተረጎመ ውኃው እየሰረቀ መውጣቱን የሚያመለክቱ ሲሆን ‘ክሌፕስድረ’ የሚለው ቃል ደግሞ በግሪክኛ የሚያስተላልፈው ትርጉም ይህ ነው።”
ክሌፕስድረ የሚሠራው እንዴት ነው? በአንድ ዕቃ ውስጥ ያለ ውኃ ከሥር በኩል ባለ ትንሽ ቀዳዳ እየተንጠባጠበ ወደ ሌላኛው ዕቃ ይወርዳል። አንድ ሰው በላይኛው አሊያም በታችኛው ዕቃ ውስጥ ያለውን የውኃ መጠን በመመልከት ስንት ሰዓት እንደሆነ ማወቅ ይችላል፤ ብዙ ጊዜ በሁለቱም ዕቃዎች ላይ ሰዓቱን ለማወቅ የሚረዱ ምልክቶች ይደረግባቸዋል።
የሮማውያን የጦር ሠራዊት የሌሊቱን ክፍለ ጊዜ ለማወቅ እንዲህ ባሉ ሰዓቶች ይጠቀም ነበር። አንደኛው ክፍለ ሌሊት አልቆ ሌላኛው ክፍለ ሌሊት መጀመሩን ለማሳወቅ መለከት ይነፋ ነበር። አንድ ሰው የመለከቱን ድምፅ ልብ ብሎ የሚሰማ ከሆነ አራቱ ክፍለ ሌሊቶች መቼ ጀምረው መቼ እንዳለቁ ማወቅ ይችላል።—ማርቆስ 13:35