በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ፦ የኢየሱስ ትንሣኤ​—ለአንተ ምን ትርጉም አለው?

የኢየሱስ ትንሣኤ—በእርግጥ ተፈጽሟል?

የኢየሱስ ትንሣኤ—በእርግጥ ተፈጽሟል?

ከዛሬ 2,500 ዓመታት በፊት፣ ሄሮዶተስ የተባለ ግሪካዊ የታሪክ ምሁር በዘመኑ ስለነበሩት ግብፃውያን አንድ ታሪክ ተናግሮ ነበር። እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ሀብታሞች በሚያዘጋጁት ግብዣ ላይ ራት ከተበላ በኋላ አንድ ሰው አስከሬን የሚመስል ምስል በሬሳ ሣጥን ውስጥ ይዞ ይዞራል፤ ይህ ምስል ከእንጨት የተሠራና ቀለም የተቀባ ሲሆን አንድ ወይም ሁለት ክንድ ርዝመት ሊኖረው ይችላል። ይህንንም በግብዣው ላይ ለሚገኙት በሙሉ እያሳየ ‘ጠጡ፣ ተደሰቱ፤ ይህን ምስል ግን እዩት፤ ምክንያቱም ስትሞቱ እናንተም እንደዚህ ምስል በድን ትሆናላችሁ’ ይላቸዋል።”

ስለ ሕይወትና ስለ ሞት እንዲህ ያለ አመለካከት የነበራቸው ግብፃውያን ብቻ አልነበሩም። በዛሬው ጊዜም “እንብላ፣ እንጠጣ፣ እንደሰት” የሚለውን አባባል መስማት የተለመደ ነው። ሰዎች እንደሚያስቡት ሞት የሁሉ ነገር ፍጻሜ ከሆነ በሕይወት እስካለን ድረስ ለምን አንደሰትም? ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ምን አታገለን? እርግጥ ነው፣ ሁሉም ነገር በሞት የሚደመደም ቢሆን ኖሮ ለዛሬ ብቻ መኖር ምክንያታዊ ይሆን ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስም የተናገረው ይህንኑ ነው። ጳውሎስ በትንሣኤ የማያምኑ ሰዎች “ሙታን የማይነሱ ከሆነማ ‘ነገ ስለምንሞት እንብላ፣ እንጠጣ’” የሚል አመለካከት እንዳላቸው ገልጿል።—1 ቆሮንቶስ 15:32

እርግጥ ነው፣ ጳውሎስ ሙታን ለዝንተ ዓለም ይረሳሉ ብሎ አያስብም ነበር። ሙታን እንደሚነሱና ከዚያ በኋላ ለዘላለም እንደሚኖሩ በእርግጠኝነት ያምን ነበር። ይህ እምነቱ የተመሠረተው ትልቅ ክንውን በሆነው በክርስቶስ ኢየሱስ ትንሣኤ * ላይ ነበር፤ ጳውሎስ የኢየሱስ ትንሣኤ ለመከናወኑ ቅንጣት ታክል ጥርጣሬ አልነበረውም። እንዲያውም ይህ ትንሣኤ የጥንቶቹን ደቀ መዛሙርት እምነት ያጠናከረ ትልቅ ክንውን ነበር።

ይሁንና የኢየሱስ ትንሣኤ ለእኛ ምን ትርጉም አለው? ይህ ትንሣኤ እንደተከናወነ እርግጠኛ የምንሆነውስ እንዴት ነው? ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለነበሩ ክርስቲያኖች ደብዳቤ ሲጽፍ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ምን አሳማኝ ማስረጃ እንዳቀረበ እስቲ እንመልከት።

ክርስቶስ ከሞት ባይነሳ ኖሮስ?

በጥንቷ ቆሮንቶስ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች የትንሣኤ ጉዳይ ግራ አጋብቷቸው የነበረ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ትንሣኤ ቃል በቃል የሚፈጸም ነገር እንደሆነ ጭራሹኑ አያምኑም ነበር። ሐዋርያው በዚያ ለነበሩ ክርስቲያኖች በጻፈላቸው የመጀመሪያ ደብዳቤ ላይ፣ ትንሣኤ ውሸት ከሆነ ምን ውጤት ሊከተል እንደሚችል ዘርዝሯል። እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “የሙታን ትንሣኤ ከሌለማ ክርስቶስም አልተነሳም ማለት ነዋ! ክርስቶስ ካልተነሳ ደግሞ ስብከታችን ከንቱ ነው፤ እምነታችንም ከንቱ ነው። ከዚህም በተጨማሪ . . . ሐሰተኞች የአምላክ ምሥክሮች ሆነን ተገኝተናል ማለት ነው። . . . [ደግሞም] እምነታችሁ ከንቱ ነው፤ አሁንም ገና ከነኃጢአታችሁ ናችሁ ማለት ነው። . . . የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ሆነው በሞት ያንቀላፉትም ጠፍተዋል ማለት ነው።”—1 ቆሮንቶስ 15:13-18

“በአንድ ጊዜ ከአምስት መቶ ለሚበልጡ ወንድሞች የታየ ሲሆን . . . ከዚያም ለያዕቆብ ታየ፤ ቀጥሎም ለሐዋርያቱ በሙሉ ታየ፤ በመጨረሻ ደግሞ . . . ለእኔ ተገለጠልኝ።”​—1 ቆሮንቶስ 15:6-8

ጳውሎስ ማብራሪያውን የጀመረው ማንም ሊያስተባብለው የማይችለውን አንድ ሐቅ በመናገር ነበር፤ ይኸውም ሙታን የማይነሱ ከሆነ ሞቶ የነበረው ክርስቶስም አልተነሳም ማለት ነው የሚል የመከራከሪያ ነጥብ በማንሳት ነበር። ክርስቶስ አልተነሳም ብለን ካመንን ቀጥሎ የሚሆነው ነገር ምንድን ነው? እንዲህ ቢሆን ኖሮ ምሥራቹን መስበክ ከንቱና እልም ያለ ውሸት ይሆን ነበር። ደግሞም የክርስቶስ ትንሣኤ ከአምላክ ሉዓላዊነት፣ ከስሙ፣ ከመንግሥቱ እንዲሁም ከመዳናችን ጋር ከተያያዙ መሠረታዊ የሆኑ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጋር በእጅጉ የተቆራኘ በመሆኑ በክርስትና እምነት ውስጥ ቁልፍ ቦታ ያለው ነገር ነው። እንዲሁም ትንሣኤ በእርግጥ ያልተፈጸመ ቢሆን ኖሮ ጳውሎስና ሌሎቹ ሐዋርያት የሰበኩት መልእክት ባዶና ዋጋ ቢስ ከመሆን የዘለለ ትርጉም አይኖረውም ነበር።

ክርስቶስ ከሞት አልተነሳም ብሎ ማመን የሚያስከትለው ውጤት በዚህ ብቻ አያበቃም። ክርስቶስ ከሞት ካልተነሳ የክርስትና እምነት ከንቱ፣ ባዶና ውሸት ይሆን ነበር። በተጨማሪም ጳውሎስና ሌሎች ደቀ መዛሙርት እየዋሹ ያሉት ስለ ኢየሱስ ትንሣኤ ብቻ ሳይሆን ኢየሱስን አስነስቶታል ብለው ስለሚናገሩለት ስለ ይሖዋ አምላክም ጭምር ይሆን ነበር። ከዚህም በላይ “ክርስቶስ ስለ ለኃጢአታችን ሞተ” የሚለው አባባልም ሐሰት ይሆን ነበር፤ ምክንያቱም አዳኙ ራሱ ከሞት ካልዳነ ሌሎችን ሊያድን አይችልም። (1 ቆሮንቶስ 15:3) ይህ ደግሞ፣ በተለያየ ምክንያት የሞቱና አንዳንዶቹም ሰማዕታት እስከመሆን የደረሱ ክርስቲያኖች ትንሣኤ እናገኛለን በሚል ከንቱ ተስፋ ጠፍተው ቀርተዋል ማለት ይሆን ነበር።

ጳውሎስ ሐሳቡን ሲያጠቃልል እንዲህ ብሏል፦ “በክርስቶስ ተስፋ ያደረግነው ለዚህ ሕይወት ብቻ ከሆነ ከሰው ሁሉ ይልቅ የምናሳዝን ነን።” (1 ቆሮንቶስ 15:19) እንደ ሌሎች ክርስቲያኖች ሁሉ ጳውሎስም በትንሣኤና በሚያስገኛቸው በረከቶች በማመኑ ምክንያት ብዙ ነገር አጥቷል፣ ስደት አጋጥሞታል፣ መከራ ደርሶበታል እንዲሁም ሞትን ተጋፍጧል። ትንሣኤ ውሸት ቢሆን ኖሮ ልፋቱ ሁሉ ከንቱ ይሆን ነበር!

በትንሣኤ ማመን የሚኖርብህ ለምንድን ነው?

ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖች ስለ ትንሣኤ ያላቸው እምነት በውሸት ላይ የተመሠረተ ነው የሚል አመለካከት አልነበረውም። ኢየሱስ ከሞት እንደተነሣ ያውቅ ስለነበረ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ማስረጃዎቹን ጠቅለል አድርጎ ሲያስቀምጥላቸው እንዲህ አላቸው፦ “ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚሉት ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፤ ተቀበረም፤ ደግሞም ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚሉት በሦስተኛው ቀን ተነሳ፤ ለኬፋም ታየ፤ ከዚያም ለአሥራ ሁለቱ ታየ።” * አክሎም እንዲህ አለ፦ “በኋላ ደግሞ በአንድ ጊዜ ከአምስት መቶ ለሚበልጡ ወንድሞች የታየ ሲሆን አብዛኞቹ እስካሁን በሕይወት አሉ፤ አንዳንዶቹ ግን በሞት አንቀላፍተዋል። ከዚያም ለያዕቆብ ታየ፤ ቀጥሎም ለሐዋርያቱ በሙሉ ታየ፤ በመጨረሻ ደግሞ . . . ለእኔ ተገለጠልኝ።”—1 ቆሮንቶስ 15:3-8

ጳውሎስ ማስረጃውን ማቅረብ የጀመረው ክርስቶስ ለኃጢአታችን እንደሞተ፣ እንደተቀበረና እንደተነሳ በእርግጠኝነት በመናገር ነው። ይህን ያህል እርግጠኛ እንዲሆን ያደረገው ምንድን ነው? አንዱ ምክንያት ብዙ የዓይን ምሥክሮች የነበሩ መሆናቸው ነው። ትንሣኤ ያገኘው ኢየሱስ ለግለሰቦች (ጳውሎስን ጨምሮ)፣ አነስተኛ ቁጥር ላላቸው ሰዎች አልፎ ተርፎም 500 ለሚያህል ሕዝብ ተገልጦ የነበረ ሲሆን ከእነዚህ ሰዎች መካከል ብዙዎቹ መጀመሪያ ላይ የኢየሱስን መነሳት ሲሰሙ ተጠራጥረው እንደነበረ ጥርጥር የለውም! (ሉቃስ 24:1-11) በጳውሎስ ዘመን አብዛኞቹ የዓይን ምሥክሮች ገና በሕይወት የነበሩ ሲሆን ኢየሱስ ከሞት ተነስቶ ለሰዎች መታየቱን ማረጋገጥ የሚፈልግ ሰው ሊጠይቃቸው ይችል ነበር። (1 ቆሮንቶስ 15:6) የአንድ ወይም የሁለት ሰዎችን የምሥክርነት ቃል ማጣጣል ቀላል ሊሆን ቢችልም 500ና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች የሰጡትን ምሥክርነት ውድቅ ማድረግ ግን ቀላል አይሆንም።

በተጨማሪም ጳውሎስ ኢየሱስ የሞተው፣ የተቀበረውና ከሞት የተነሳው ‘ቅዱሳን መጻሕፍት በሚሉት’ መሠረት እንደሆነ ሁለት ጊዜ መጥቀሱን ልብ በል። ኢየሱስ መሞቱ፣ መቀበሩና መነሳቱ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ስለ መሲሑ የተናገሯቸው ትንቢቶች መፈጸማቸውን ያረጋግጣሉ፤ ይህ ደግሞ ኢየሱስ በእርግጥም ተስፋ የተደረገበት መሲሕ ለመሆኑ ማስረጃ ነው።

የዓይን እማኞችና የቅዱሳን መጻሕፍት ምሥክርነት ቢኖርም ኢየሱስ ከሙታን መነሣቱን የሚጠራጠሩ ሰዎች ድሮም ነበሩ፤ አሁንም አሉ። አንዳንዶች ደቀ መዛሙርቱ የኢየሱስን አስከሬን እንደሰረቁትና በኋላም ከሞት መነሳቱን ለመመሥከር እንደሞከሩ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ደቀ መዛሙርቱ፣ መቃብሩን እንዲጠብቁ የተመደቡትን የሮም ጠባቂዎች ለማስገደድ ወይም ለማግባባት የሚያስችል አቅም አልነበራቸውም። ሌሎች ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ከሞት እንደተነሳ የተናገሩት እሱን ያዩት መስሏቸው እንጂ የእውነት ታይቷቸው እንዳልሆነ ሲናገሩ ይሰማል። ኢየሱስ የተገለጠው ለብዙ ሰዎችና በተለያዩ ጊዜያት መሆኑ ግን ይህን አመለካከት ውድቅ ያደርገዋል። ደግሞስ ከሞት የተነሳው ኢየሱስ እውን ካልሆነ ዓሣ ጠብሶ ሊያበላቸው ይችል ነበር? (ዮሐንስ 21:9-14) ወደ እሱ ቀርበው እንዲዳስሱትስ ያደርግ ነበር?—ሉቃስ 24:36-39

በሌላ በኩል ደግሞ የኢየሱስ ትንሣኤ፣ ደቀ መዛሙርቱ ለማታለል ብለው ያቀናበሩት የፈጠራ ታሪክ ነው የሚሉ ሰዎችም አልጠፉም። ነገር ግን ደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ቢያደርጉ ምን ይጠቀማሉ? ስለ ትንሣኤ በመመሥከራቸው ለፌዝ፣ ለሥቃይ አልፎ ተርፎም ለሞት ተጋልጠዋል። ውሸት የሆነን ነገር ለመደገፍ ሲሉ እዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ ምን አስገባቸው? ከዚህም በላይ በኢየሩሳሌም ለመጀመሪያ ጊዜ ምሥክርነታቸውን የሰጡት ሰበብ ፈልገው በእነሱ ላይ ሊፈርዱባቸው በተዘጋጁ ተቃዋሚዎች ፊት ነበር።

ደቀ መዛሙርቱ እጅግ ኃይለኛ ስደት እየደረሰባቸውም እንኳ ስለ ጌታቸው ለመመሥከር ድፍረት የሰጣቸው ነገር ኢየሱስ ትንሣኤ ማግኘቱ ነበር። የኢየሱስ ከሞት መነሳት እርግጠኛ ነገር ስለሆነ ለክርስትና እምነት መሠረት ሆኗል። የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ሕይወታቸውን አደጋ ላይ የጣሉት በሰዎች እጅ ስለሞተው አንድ ጠቢብ መምህራቸው ለመመሥከር ብለው ብቻ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ስለ ኢየሱስ ትንሣኤ ለመመሥከር ሕይወታቸውን አደጋ ላይ የጣሉት በእርግጥም እሱ ክርስቶስና የአምላክ ልጅ እንዲሁም እነሱን የሚደግፍና የሚመራ ኃያልና ሕያው አካል እንደሆነ ስላረጋገጠላቸው ነው። የእሱ ትንሣኤ እነሱም ጭምር ከሙታን እንደሚነሱ የሚያረጋግጥ ነበር። ኢየሱስ ከሞት ባይነሳ ኖሮ ክርስትና አይኖርም ነበር። እንዲሁም ስለ እሱ ምንም ነገር ላንሰማ እንኳ እንችል ነበር።

ይሁንና የክርስቶስ ትንሣኤ በዛሬው ጊዜ ላለነው ለእኛ ምን ትርጉም አለው?

^ አን.5 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ትንሣኤ” የሚለው ቃል ቀጥታ ሲተረጎም “እንደገና መነሳት” የሚል ፍቺ አለው። ይህም አንድ ሰው የራሱን ማንነት፣ ባሕርይና ትውስታ ይዞ ወደ ሕይወት መመለሱን የሚያመለክት ነው።

^ አን.13 የአስቆሮቱ ይሁዳ ከሞተ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ የሐዋርያቱ ቁጥር 11 የነበረ ቢሆንም “አሥራ ሁለቱ” የሚለው አገላለጽ ያሉትን ሐዋርያት ለማመልከትም ተሠርቶበታል። በአንድ ወቅት ኢየሱስ፣ ቶማስ በሌለበት ለሐዋርያቱ በተገለጠላቸው ጊዜ ቁጥራቸው 10 ብቻ ቢሆንም 12ቱ ተብለዋል።—ዮሐንስ 20:24