መለኮታዊ የጥፋት ፍርዶች—አምላክ ጨካኝ እንደሆነ ያሳያሉ?
ይህን ጥያቄ ለመመለስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹ ሁለት መለኮታዊ የጥፋት ፍርዶችን ይኸውም በኖኅ ዘመን የደረሰውን የጥፋት ውኃና ከነዓናውያንን ለማጥፋት የተወሰደውን እርምጃ በአጭሩ እንመልከት።
የኖኅ ዘመን የጥፋት ውኃ
ሰዎች ምን ይላሉ? “አምላክ፣ ከኖኅና ከቤተሰቡ በስተቀር መላውን የሰው ዘር ለማጥፋት የጥፋት ውኃ ያመጣው ጨካኝ ቢሆን ነው።”
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? አምላክ “ከመንገዳቸው ተመልሰው በሕይወት እንዲኖሩ እንጂ በክፉዎች ሞት ደስ አልሰኝም” በማለት ተናግሯል። (ሕዝቅኤል 33:11) ስለዚህ በኖኅ ዘመን በክፉዎች ላይ የደረሰው ጥፋት አምላክን አላስደሰተውም ነበር ማለት ነው። ታዲያ ለምን አጠፋቸው?
አምላክ በቀደሙት ዘመናት እሱን በማይፈሩ ሰዎች ላይ እንዲህ ዓይነቶቹን የጥፋት ፍርዶች ያመጣው “ፈሪሃ አምላክ ለሌላቸው ሰዎች ለወደፊቱ ምሳሌ እንዲሆን” መሆኑን በመግለጽ መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጠናል። (2 ጴጥሮስ 2:5, 6) ታዲያ ከእነዚህ የጥፋት እርምጃዎች ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?
አንደኛ፣ አምላክ ሰዎችን ማጥፋት ሥቃይ የሚያስከትልበት ቢሆንም እንኳ በሌሎች ላይ መከራ የሚያደርሱ ጨካኝ ሰዎችን፣ በሠሩት ድርጊት እንደሚጠይቃቸው ያሳያል። ጊዜው ሲደርስ አምላክ ለማንኛውም የፍትሕ መዛባትና መከራ መቋጫ ያበጃል።
ሁለተኛ፣ አምላክ በቀድሞ ዘመን ከወሰዳቸው እርምጃዎች እንደምንመለከተው ጥፋት ከማምጣቱ በፊት በፍቅር ተገፋፍቶ ሰዎችን ያስጠነቅቃል። ኖኅ የጽድቅ ሰባኪ የነበረ ቢሆንም አብዛኞቹ ሰዎች አልሰሙትም። መጽሐፍ ቅዱስ “የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉንም ጠራርጎ እስከወሰዳቸው ጊዜ ድረስ ምንም አላስተዋሉም” በማለት ይናገራል።—ማቴዎስ 24:39
ታዲያ አምላክ በወሰዳቸው የፍርድ እርምጃዎች ሁሉ ይህንኑ አድርጓል? አዎን። ለምሳሌ ያህል፣ ሕዝቡ የነበሩት እስራኤላውያን በዙሪያቸው እንደነበሩት አሕዛብ የክፋት መንገድ ከተከተሉ ጠላቶቻቸው ምድራቸውን እንደሚወርሩ፣ ዋና ከተማቸውን ኢየሩሳሌምን እንደሚያጠፉና በግዞት እንደሚወስዷቸው አስጠንቅቋቸው ነበር። እስራኤላውያን ግን ሕፃናትን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብን ጨምሮ በርካታ ክፉ ድርጊቶችን መፈጸም ጀመሩ። ታዲያ ይሖዋ እርምጃ ወስዶ ነበር? አዎን! ይሁን እንጂ እርምጃ የወሰደው ሕዝቡ ከክፉ መንገዳቸው እንዲመለሱ ለማስጠንቀቅ ደጋግሞ ነቢያትን ከላከ በኋላ ነበር። እንዲያውም “በእውነት ጌታ እግዚአብሔር ምስጢሩን ለአገልጋዮቹ ለነቢያት ሳይገልጥ፣ ምንም ነገር አያደርግም” ብሎ ነበር።—አሞጽ 3:7
ይህ ለአንተ ምን ትርጉም አለው? ይሖዋ በቀድሞ ዘመን ከወሰዳቸው የጥፋት እርምጃዎች የምንመለከተው ነገር ተስፋ የሚሰጥ ነው። አምላክ ጨካኝ በሆኑና በሌሎች ላይ መከራ በሚያደርሱ ሰዎች ላይ እንደሚፈርድባቸው በእርግጠኝነት መጠበቅ እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ “ክፉ ሰዎች ይጠፋሉ፤ . . . ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ” በማለት ይናገራል። (መዝሙር 37:9-11) የሰውን ዘር ከመከራ ስለሚገላግል የጥፋት ፍርድ ምን ይሰማሃል? የጭካኔ ድርጊት ነው ወይስ የምሕረት እርምጃ?
ከነዓናውያንን ለማጥፋት የተወሰደ እርምጃ
ሰዎች ምን ይላሉ? “ከነዓናውያንን ለማጥፋት የተወሰደው እርምጃ በዘመናችን ከሚፈጸሙ የዘር ማጥፋት ዘመቻዎች ጋር የሚተካከል የጭካኔ ድርጊት ነው።”
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ሲናገር “መንገዱም ሁሉ ትክክል ነው፤ የማይሳሳት ታማኝ አምላክ [ነው]” ይላል። (ዘዳግም 32:4) መለኮታዊ የፍርድ እርምጃን ሰዎች ከሚያካሂዱት ጦርነት ጋር ልናወዳድረው አንችልም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ከሰዎች በተለየ መልኩ አምላክ ልብን ማንበብ ማለትም የሰዎችን ውስጣዊ ማንነት መረዳት ይችላል።
ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ በሰዶምና በገሞራ ላይ ጥፋት ለማምጣት በወሰነ ጊዜ ታማኝ ሰው የነበረው አብርሃም ፍርዱ ፍትሐዊ የመሆኑ ጉዳይ አሳስቦት ነበር። ለአብርሃም፣ ፍትሐዊ የሆነው አምላክ ‘ጻድቁን ከኃጢአተኛው ጋር አብሮ ያጠፋል’ ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነበር። አምላክም ይህን በተመለከተ አብርሃም ላቀረበው ጥያቄ ሁሉ በትዕግሥት መልስ ሰጥቷል፤ በሰዶም አሥር ጻድቃን እንኳ ቢገኙ ለእነሱ ሲል ከተማዋን እንደማያጠፋ አረጋግጦለታል። (ዘፍጥረት 18:20-33) አምላክ በሰዶምና በገሞራ የነበሩትን ሰዎች ልብ በመመርመር ክፋታቸውን ተመልክቶ እንደነበር ግልጽ ነው።—1 ዜና መዋዕል 28:9
በተመሳሳይም አምላክ በከነዓናውያን ላይ መፍረዱና እንዲጠፉ መበየኑ ተገቢ ነበር። ምክንያቱም ከነዓናውያን በጭካኔያቸው የታወቁ ነበሩ፤ ልጆቻቸውን ከነሕይወታቸው በእሳት በማቃጠል መሥዋዕት ያደርጉ ነበር። * (2 ነገሥት 16:3) ይሖዋ ምድሪቱን እንዲይዙ እስራኤላውያንን እንዳዘዛቸው ከነዓናውያን ያውቁ ነበር። ምድሪቱን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ባለመሆን ከእስራኤላውያን ጋር ለመዋጋት የመረጡት ከነዓናውያን እስራኤላውያንን ብቻ ሳይሆን ከሕዝቡ ጋር እንደነበረ በግልጽ ያሳየውን ይሖዋን ጭምር ሆን ብለው ተቃውመዋል።
ከዚህም በላይ አምላክ የክፋት መንገዳቸውን በመተው የእሱን ከፍተኛ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ለመከተል ፈቃደኛ ለሆኑ ከነዓናውያን ምሕረት አሳይቷቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ጋለሞታ የነበረችው ከነዓናዊቷ ረዓብ እስከነቤተሰቧ ከጥፋት ተርፋለች። በተጨማሪም የከነዓናውያን ከተማ የነበረችው የገባዖን ነዋሪዎች ምሕረት እንዲደረግላቸው በጠየቁ ጊዜ እነሱና ልጆቻቸው በሙሉ ከመጥፋት ድነዋል።—ኢያሱ 6:25፤ 9:3, 24-26
ይህ ለአንተ ምን ትርጉም አለው? በከነዓናውያን ላይ ከተበየነው የጥፋት ፍርድ አንድ አስፈላጊ ትምህርት እናገኛለን። እኛም በትንቢት ወደተነገረለት “ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች [ወደሚጠፉበት] የፍርድ ቀን” በፍጥነት እየቀረብን ነው። (2 ጴጥሮስ 3:7) ይሖዋን የምንወድ ከሆነ፣ እሱ ፍትሐዊ አገዛዙን የማይቀበሉ ሰዎችን ከምድር ላይ በማጥፋት በሰዎች ላይ የሚደርሰውን መከራ በሚያስወግድበት ጊዜ ጥቅም እናገኛለን።
ይሖዋ በፍቅር ተገፋፍቶ ወላጆች የሚያደርጉት ምርጫ ልጆቻቸውንም እንደሚነካ አስገንዝቦናል። የአምላክ ቃል “አንተና ልጆችህ በሕይወት እንድትኖሩ ሕይወትን ምረጥ፤ ይኸውም አምላክህን እግዚአብሔርን እንድትወድ፣ ቃሉን እንድታደምጥና ከእርሱ ጋር እንድትጣበቅ ነው” በማለት ይናገራል። (ዘዳግም 30:19, 20) እንዲህ ዓይነት ማሳሰቢያ ለሕዝቡ የሚሰጥ አምላክ ጨካኝ ይመስልሃል? ወይስ ሕዝቡን የሚወድና ትክክለኛውን ምርጫ እንዲያደርጉ የሚፈልግ አፍቃሪ አምላክ?
^ አን.15 የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች የከነዓናውያን አምልኮ ሕፃናትን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብን ይጨምር እንደነበር የሚያሳይ ማስረጃ በቁፋሮ አግኝተዋል።
ከነዓናውያን በጭካኔያቸው የታወቁ ነበሩ፤ እንዲሁም ሆን ብለው አምላክንና ሕዝቡን ተቃውመዋል