የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ምንድን ነው?
አምላክ የሰውን ዘር ለማዳን ዝግጅት አደረገ
አምላክ ለታማኙ አብርሃም፣ በትንቢት የተነገረለት ‘ዘር’ በእሱ የዘር ሐረግ እንደሚመጣ ቃል ገባለት። “ሕዝቦች ሁሉ” በዚህ ዘር አማካኝነት በረከት ያገኛሉ። (ዘፍጥረት 22:18) የአብርሃም የልጅ ልጅ የሆነው ያዕቆብ ከጊዜ በኋላ ወደ ግብፅ ሄዶ መኖር ጀመረ፤ ውሎ አድሮ ዘሮቹ እየበዙ ሄደው የጥንቱ የእስራኤል ብሔር ተመሠረተ።
ከጊዜ በኋላ በግብፅ አንድ ጨካኝ ፈርዖን ተነስቶ እስራኤላውያንን ባሪያዎች አደረጋቸው፤ አምላክ በነቢዩ በሙሴ አማካኝነት ሕዝቡን ከግብፅ ካወጣ በኋላ ቀይ ባሕርን በተአምር ከፍሎ አሻገራቸው። ከዚያም አምላክ፣ ለእስራኤላውያን አሥርቱን ትእዛዛት ጨምሮ በርካታ ሕጎችን ሰጣቸው፤ እነዚህ ሕጎች ለሕዝቡ መመሪያ እና ጥበቃ ሆነውላቸዋል። የኃጢአት ይቅርታ ለማግኘት ስለሚቀርብ መሥዋዕት የሚገልጽ ሐሳብ በሕጉ ውስጥ ተካትቷል። ሙሴ፣ አምላክ ሌላ ነቢይ እንደሚልክላቸው በአምላክ መንፈስ ተመርቶ ለእስራኤላውያን ነገራቸው። ይህ ነቢይ አስቀድሞ የተነገረለት ‘ዘር’ ነው።
ሙሴ ይህን ከተናገረ ከአራት መቶ ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ አምላክ፣ በኤደን ትንቢት የተነገረለት ‘ዘር’ ንጉሥ እንደሚሆንና መንግሥቱ ለዘላለም እንደሚጸና ለንጉሥ ዳዊት ቃል ገባለት። የሰውን ዘር እንዲያድንና ምድርን እንደገና ገነት እንዲያደርግ አምላክ የሾመው ይህ ዘር መሲሕ ይሆናል።
አምላክ በዳዊትና በሌሎች ነቢያት በኩል ስለ መሲሑ ደረጃ በደረጃ ተጨማሪ ነገሮችን ገልጿል። እነዚህ ሰዎች፣ መሲሑ ትሑትና ደግ እንደሚሆን እንዲሁም በእሱ አገዛዝ ሥር ረሃብ፣ የፍትሕ መዛባትና ጦርነት እንደሚያከትሙ ትንቢት ተናግረዋል። የሰው ዘር በሙሉ እርስ በእርሱ እና ከእንስሳት ጋር ጭምር በሰላም ይኖራል። መሲሑ በሽታን፣ መከራንና ሞትን በማስወገድ አምላክ ለሰው ልጆች በነበረው ዓላማ መሠረት እንዲኖሩ ያደርጋል፤ እንዲሁም የሞቱ ሰዎች ትንሣኤ አግኝተው በምድር ላይ ይኖራሉ።
አምላክ፣ በነቢዩ ሚክያስ አማካኝነት መሲሑ በቤተልሔም እንደሚወለድ፣ በነቢዩ ዳንኤል አማካኝነት ደግሞ መሲሑ ከጊዜ በኋላ እንደሚገደል ትንቢት አስነግሯል። ይሁን እንጂ አምላክ መሲሑን ከሞት በማስነሳት በሰማይ ንጉሥ አድርጎ ይሾመዋል። በተጨማሪም ዳንኤል፣ የመሲሑ መንግሥት ሌሎቹን መንግሥታት በሙሉ ለዘለቄታው እንደሚያስወግድና በምትካቸው መግዛት እንደሚጀምር አስቀድሞ ተናግሯል። ታዲያ በትንቢት በተነገረው መሠረት መሲሑ መጣ?