የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | አምላክን መውደድ ከባድ እንዲሆን ያደረጉ ውሸቶች
ውሸት 3—አምላክ ጨካኝ ነው
ብዙዎች ምን ብለው ያምናሉ?
“ከባድ ኃጢአት የሠሩ ሰዎች፣ ልክ ሲሞቱ ነፍሳቸው ወደ ሲኦል ይወርዳል፤ በዚያም ‘በዘላለማዊ እሳት’ ይሠቃያሉ።” (ካቴኪዝም ኦቭ ዘ ካቶሊክ ቸርች) አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች፣ ሲኦል ከአምላክ መገለልን ወይም መራቅን እንደሚያመለክት ይናገራሉ።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው እውነት
“ኀጢአት የምትሠራ ነፍስ እርሷ ትሞታለች።” (ሕዝቅኤል 18:4) “ሙታን . . . ምንም አያውቁም።” (መክብብ 9:5) ነፍስ የምትሞትና ከሞት በኋላ ምንም የማታውቅ ከሆነ ዘላለማዊ እሳት ወይም ከአምላክ መራቅ የሚያስከትለው ሥቃይ ሊሰማት የሚችለው እንዴት ነው?
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙውን ጊዜ “ሲኦል” ተብለው የተተረጎሙት የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት የሚያመለክቱት የሰው ልጆችን መቃብር ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ኢዮብ የሚያሠቃይ ሕመም ይዞት ሳለ “በሲኦል ውስጥ ምነው በሰወርኸኝ ኖሮ!” ብሎ ጸልዮአል። (ኢዮብ 14:13 የ1954 እትም) ኢዮብ የተመኘው፣ በመቃብር ውስጥ እረፍት ማግኘትን እንጂ ወደ ሥቃይ ሥፍራ መግባትን ወይም ከአምላክ መነጠልን አልነበረም።
ይህን ማወቅ ለምን አስፈለገ?
ጭካኔ አምላክን እንድንወደውና እንድንቀርበው አያደርገንም፤ ከዚህ ይልቅ ከእሱ እንድንርቅ ያደርገናል። በሜክሲኮ የምትኖረው ሮሲዮ እንዲህ ብላለች፦ “ከሕፃንነቴ ጀምሮ ስለ ገሃነም እሳት እማር ነበር። አምላክን በጣም ከመፍራቴ የተነሳ ምንም ዓይነት ጥሩ ባሕርያት ሊኖሩት እንደሚችሉ ማሰብ አልቻልኩም። ቁጡ እንደሆነና ትዕግሥት እንደሌለው ይሰማኝ ነበር።”
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ስለሚወስዳቸው የፍርድ እርምጃዎችና ሙታን ስላሉበት ሁኔታ የሚናገረው ግልጽ ሐሳብ ሮሲዮ ለአምላክ የነበራትን አመለካከት እንድትለውጥ ረድቷታል። እንዲህ ብላለች፦ “ነፃ እንደወጣሁ፣ ይኸውም ከባድ ሸክም ከላዬ ላይ እንደወረደልኝ ተሰማኝ። አምላክ ከሁሉ የተሻለውን እንደሚመኝልንና እንደሚወደን መተማመን ቻልኩ፤ እኔም ልወደው እንደምችል ተሰማኝ። አምላክ፣ ልጆቹን እጃቸውን ይዞ እንደሚመራና ለእነሱ ከሁሉ የተሻለውን እንደሚመኝ አባት ነው።”—ኢሳይያስ 41:13
ብዙዎች ገሃነመ እሳትን በመፍራት ሃይማኖተኛ ለመሆን ጥረት ያደርጋሉ፤ አምላክ ግን እሱን በመፍራት እንድታገለግለው አይፈልግም። ኢየሱስ “አምላክህን ይሖዋን . . . ውደድ” ብሏል። (ማርቆስ 12:29, 30) በተጨማሪም አምላክ በዛሬው ጊዜ ፍትሕ የጎደለው ነገር እንደማያደርግ ስንገነዘብ ወደፊት የሚወስዳቸው የፍርድ እርምጃዎችም ፍትሐዊ እንደሚሆኑ እንተማመናለን። እኛም የኢዮብ ወዳጅ እንደሆነው እንደ ኤሊሁ “ክፋትን ማድረግ ከእግዚአብሔር ዘንድ፣ በደልንም መፈጸም ሁሉን ከሚችል አምላክ ይራቅ” ብለን አፋችንን ሞልተን መናገር እንችላለን።—ኢዮብ 34:10