በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቶማስ ኤምለን—አምላክን የሰደበ ወይስ ለእውነት ጥብቅና የቆመ?

ቶማስ ኤምለን—አምላክን የሰደበ ወይስ ለእውነት ጥብቅና የቆመ?

ቶማስ ኤምለን ማን ነው? ለእውነት ጥብቅና እንዲቆም ያነሳሳው ምንድን ነው? እኛስ ከእሱ ምን ትምህርት እናገኛለን?

የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት በ17ኛው መቶ ዘመን መጨረሻ እና በ18ኛው መቶ ዘመን መባቻ ላይ በእንግሊዝና በአየርላንድ የነበረው ሁኔታ ምን ይመስል እንደነበር መለስ ብለን እንመልከት። በዚያን ወቅት የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ሥልጣን ነበረው። የተለያዩ የፕሮቴስታንት ቡድኖችና ግለሰቦች ቤት ክርስቲያኑ የሚያስተምረውን ትምህርት ይቃወሙ ነበር።

ቶማስ ኤምለን ማን ነው?

በዚህ ወቅት ላይ ነበር ቶማስ ኤምለን፣ ግንቦት 27 ቀን 1663 እንግሊዝ ውስጥ በስታምፎርድ፣ ሊንከንሸር የተወለደው። አሥራ ዘጠኝ ዓመት ሲሆነው የመጀመሪያ ስብከቱን አቀረበ። ከጊዜ በኋላ፣ በለንደን ውስጥ ለምትኖር አንዲት ከበርቴ የቤተሰብ ቄስ ሆነ፤ በኋላም ወደ ቤልፋስት፣ አየርላንድ ሄዶ መኖር ጀመረ።

ውሎ አድሮ በቤልፋስት በአንድ ደብር ውስጥ ማገልገል ጀመረ። ከዚያ በኋላ ባሉት ጊዜያት ኤምለን ደብሊንን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሆኖ ሠርቷል።

አምላክን በመስደብ ወንጀል የተከሰሰው ለምንድን ነው?

በዚህ ወቅት ኤምለን መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት ያጠና ነበር። ይህም ቀደም ሲል ያምንበት የነበረውን የሥላሴ መሠረተ ትምህርት እንዲጠራጠር አደረገው። በወንጌሎች ላይ ያደረገው ምርምር ደግሞ ሥላሴን በተመለከተ ያገኘውን አዲስ ግንዛቤ ይበልጥ አጠናከረለት።

ኤምለን አዲስ ያገኘውን ሐሳብ ወዲያውኑ ለሌሎች አልተናገረም። ሆኖም በደብሊን ቤተ ክርስቲያን የነበሩ አንዳንዶች ኤምለን በስብከቱ ላይ ስለ ሥላሴ መጥቀሱን እንዳቆመ አስተውለው ነበር። አዲስ ያገኘው ግንዛቤ በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት እንደማያገኝ ያውቅ ስለነበር እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ስለማምንበት ነገር ከተናገርኩ አሁን ባለኝ የኃላፊነት ቦታ መቀጠል እንደማልችል አውቃለሁ።” ሰኔ 1702 ሁለት የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች፣ በስብከቱ ላይ ስለ ሥላሴ መጥቀስ ያቆመው ለምን እንደሆነ አፋጠጡት። ኤምለን በሥላሴ ማመኑን እንዳቆመ በመናገር በቤተ ክርስቲያኑ የነበረውን ኃላፊነት ለመተው ጥያቄ አቀረበ።

ኢየሱስ ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ጋር እኩል ያልሆነበትን ምክንያት የሚያሳዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎችን የያዘ ኤምለን ያዘጋጀው ጽሑፍ

ከጥቂት ቀናት በኋላ ከደብሊን፣ አየርላንድ ወደ እንግሊዝ ሄደ። ይሁን እንጂ ከአሥር ሳምንታት በኋላ ወደ ደብሊን ተመለሰ፤ ኑሮውን በለንደን ለማድረግ አቅዶ ስለነበረ ወደ ደብሊን የተመለሰው አንዳንድ ጉዳዮቹን ለማስጨረስ ነበር። ደብሊን ሳለ፣ ለሚያምንበት ነገር ማስረጃ ለማቅረብ ሲል ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ላይ የተደረገ ምርምር (እንግሊዝኛ) የተባለ ጽሑፍ አዘጋጀ። በዚህ ጽሑፍ ላይ፣ ኢየሱስ ሁሉን ቻይ አምላክ ያልሆነበትን ምክንያት ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ግልጽ ማስረጃ አቅርቧል። ይህም የኤምለን የቀድሞ ጉባኤ አባላትን አስቆጣቸው። በመሆኑም በኤምለን ላይ ክስ ተመሠረተበት።

ኤምለን ከታሰረ በኋላ ሰኔ 14 ቀን 1703 ደብሊን በሚገኘው ፍርድ ቤት ቀረበ። የፍርድ ሂደቱን የሚገልጽ ትክክለኛ ዘገባ (እንግሊዝኛ) በተባለው ጽሑፉ ላይ ኤምለን፣ የተሰነዘረበት ክስ “ኢየሱስ ከአብ ጋር እኩል እንዳልሆነ በመግለጽ አምላክን የሚሰድብ፣ የሚያዋርድ ወዘተ መጽሐፍ መጻፍና ማሳተም” እንደሆነ ገልጿል። የፍርድ ውሳኔ የተሰጠው ሂደቱ ከመጀመሩ በፊት በመሆኑ ችሎቱ ኢፍትሐዊ ነበር። በችሎቱ ላይ የአየርላንድ ቤተ ክርስቲያን ሰባት ጳጳሳት ከዳኞቹ ጋር ተቀምጠው ነበር። ኤምለን የመከላከያ ሐሳብ እንዲያቀርብ አልተፈቀደለትም። የታወቀ ጠበቃ የነበረው ሪቻርድ ሊቨንስ ለኤምለን “ያለምንም ሕግ ወይም ደንብ እንደ ተኩላ” ታድኖ እርምጃ እንደሚወሰድበት ነገረው። የአየርላንድ ዋና  ዳኛ የነበሩት ሪቻርድ ፓይን፣ ፍርድ እንዲሰጡ ከሕዝብ መካከል ተመርጠው ለተሰየሙት ሰዎች በችሎቱ መደምደሚያ ላይ የሚጠብቁትን ፍርድ ካላስተላለፉ “ጌቶች ጳጳሳት እዚህ አሉ” አሏቸው፤ ዳኛው ይህን ያሉት እነዚህ ሰዎች ተፈላጊውን ብይን ካልሰጡ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ለመግለጽ ሊሆን ይችላል።

“መከራ የምቀበለው የእሱ [የአምላክ] እውነትና ክብር እንደሆነ ለማምንበት ነገር ነው።”—ቶማስ ኤምለን

ኤምለን ጥፋተኛ መሆኑን የሚገልጽ ብይን ሲተላለፍ የችሎቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን አቋሙን መቀየር ይፈልግ እንደሆነ ኤምለንን ጠየቀው። ኤምለን እንዲህ ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆነም። በመሆኑም የገንዘብ ቅጣትና የአንድ ዓመት እስር ተፈረደበት። ኤምለን የገንዘብ ቅጣቱን መክፈል ስላልቻለ ለሁለት ዓመት እስር ቤት ቆየ፤ በኋላ ግን አንድ ወዳጁ የገንዘብ ቅጣቱ እንዲቀነስለት ባለሥልጣናቱን አግባባቸው። በመጨረሻም ኤምለን ሐምሌ 21 ቀን 1705 ከእስር ተለቀቀ። ኤምለን በመግቢያው ላይ የተጠቀሰውን “መከራ የምቀበለው የእሱ [የአምላክ] እውነትና ክብር እንደሆነ ለማምንበት ነገር ነው” የሚለውን ሐሳብ የተናገረው ይህ ውርደት ከደረሰበት በኋላ ነው።

ኤምለን ወደ ለንደን ሄዶ መኖር የጀመረ ሲሆን በዚያም ዊልያም ዊስተን ከተባለ ሰው ጋር ተገናኘ፤ ይህ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር ሲሆን እውነት እንደሆነ የተሰማውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በጽሑፍ ላይ አዘጋጅቶ በማውጣቱ የተጠላ ሆኖ ነበር። ዊስተን ለኤምለን አክብሮት ነበረው፤ እንዲያውም ስለ ኤምለን ሲናገር “‘የጥንቱን ክርስትና’ በድፍረት በመስበክ ረገድ የመጀመሪያውና ግንባር ቀደሙ ሰው” እንደሆነ ተናግሯል።

የሥላሴን ትምህርት ያልደገፈው ለምንድን ነው?

እንደ ዊልያም ዊስተንና የተከበረ ምሁር እንደነበረው እንደ አይዛክ ኒውተን ሁሉ ኤምለንም መጽሐፍ ቅዱስ በአትናቴዎስ ድንጋጌ ላይ ያለውን የሥላሴ መሠረተ ትምህርት እንደማይደግፍ አረጋግጧል። እንዲህ ብሏል፦ “ጉዳዩን በጥልቅ ካሰብኩበትና . . . ቅዱሳን መጻሕፍት ምን እንደሚሉ ምርምር ካደረግሁ በኋላ ቀደም ሲል አምንበት ከነበረው የሥላሴ ትምህርት ጋር በተያያዘ . . . አመለካከቴን እንድለውጥ የሚያደርግ አጥጋቢ ምክንያት እንዳለ ተረዳሁ።” ኤምለን ሐሳቡን ሲደመድም “ከሁሉም በላይ ሥልጣን ያለው፣ የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ብቻ ነው” ብሏል።

ኤምለን እዚህ መደምደሚያ ላይ እንዲደርስ ያደረገው ምንድን ነው? በኢየሱስና በአባቱ መካከል ልዩነት መኖሩን የሚጠቁሙ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ማግኘቱ ነው። ከእነዚህ ጥቅሶች መካከል አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው (ከጥቅሶቹ ቀጥሎ በሰያፍ የተጻፈው ሐሳብ ኤምለን በጥቅሶቹ ላይ የሰጠው ሐሳብ ነው)፦

  •  ዮሐንስ 17:3“ክርስቶስ፣ ብቸኛው አንዱ አምላክ ወይም ሁሉን ቻይ አምላክ እንደሆነ ተደርጎ የተገለጸበት ቦታ የለም።” “ብቸኛው እውነተኛ አምላክ” ተብሎ የተጠራው አብ ብቻ ነው።

  •  ዮሐንስ 5:30“ወልድ የአብን ፈቃድ እንጂ የራሱን ፈቃድ አያደርግም።”

  •  ዮሐንስ 5:26“ሕይወት የሰጠው አብ ነው።”

  •  ኤፌሶን 1:3“ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ቦታ ላይ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ልጅ እንደሆነ ተገልጿል፤ ይሁን እንጂ አብ አንድም ቦታ ላይ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ አባት እንደሆነ ተገልጾ አናገኝም፤ ከዚህ ይልቅ ብዙውን ጊዜ የጌታችን የኢየሱስ አባት ተብሎ ተጠርቷል።”

ኤምለን ማስረጃውን በሙሉ ከመረመረ በኋላ በእርግጠኝነት እንዲህ ብሏል፦ “አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ እኩል እንደሆኑ ወይም አንድን አካል እንደሚያመለክቱ የሚጠቁም አንድም ጥቅስ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አይገኝም።”

ምን ትምህርት እናገኛለን?

በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሚገኘው ትክክለኛ ትምህርት ጥብቅና ከመቆም ወደኋላ ይላሉ። ይሁን እንጂ ኤምለን ለሚያምንበት የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጥብቅና ቆሟል። እንዲህ የሚል ጥያቄ አንስቶ ነበር፦ “አንድ ሰው በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ግልጽ በሆነና በማያሻማ መንገድ የተቀመጡትን በጣም አስፈላጊ እውነቶች ለሌሎች በይፋ ከመናገር ወደኋላ የሚል ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበቡና መመርመሩ ምን ጥቅም አለው?” ኤምለን እውነት እንደሆነ ያመነበትን ነገር ለድርድር የሚያቀርብ ሰው አልነበረም።

ኤምለንና ሌሎች ሰዎች የተዉት ምሳሌ፣ እኛም ተቃውሞ ቢደርስብንም እንኳ ለእውነት እንቆም እንደሆነና እንዳልሆነ ራሳችንን እንድንመረምር ሊያነሳሳን ይገባል። ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቃችን አስፈላጊ ነው፦ ‘ከሁሉ የበለጠ ትልቅ ቦታ ልሰጠው የሚገባው ማኅበረሰቡ ለሚሰጠኝ ክብርና ድጋፍ ነው ወይስ በአምላክ ቃል ውስጥ ለሚገኙ እውነቶች?’