የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ማጨስ በአምላክ ዘንድ እንዴት ይታያል?
ማጨስ በአምላክ ዘንድ እንዴት ይታያል?
በፊተኛው ርዕስ ላይ የተጠቀሰችው ናኦኮ ማጨስ ለማቆም የረዳት ምን እንደሆነ ስትናገር “ስለ አምላክ ባሕርያትና ዓላማዎች እውነቱን በመማሬ ሕይወቴን መለወጥ ቻልኩ” ብላለች። ናኦኮ የተማረችው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን እውነት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ትንባሆ ፈጽሞ ባይጠቀስም በውስጡ የያዘው ሐሳብ ትንባሆ ማጨስ በአምላክ ዘንድ እንዴት እንደሚታይ ማወቅ እንድንችል ይረዳናል። * ብዙዎች እንዲህ ዓይነት እውቀት ማግኘታቸው ከማጨስ እንዲቆጠቡ ወይም ከዚህ ሱስ እንዲላቀቁ ረድቷቸዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ማጨስ የሚያስከትላቸውን በግልጽ የታወቁ ሦስት ችግሮችና መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ ጋር በተያያዘ ምን እንደሚል እስቲ እንመልከት።
ማጨስ ሱስ ያስይዛል
ትንባሆ፣ ሱስ የማስያዝ ከፍተኛ ኃይል ካላቸው ንጥረ ነገሮች አንዱ የሆነው ኒኮቲን አለው። ኒኮቲን አእምሮን ለማነቃቃት አሊያም ለማደንዘዝ ሊያገለግል ይችላል። አንድ ሰው ሲያጨስ ኒኮቲኑ ወደ አንጎሉ በፍጥነትና በተደጋጋሚ ይሄዳል። በቀን አንድ ፓኬት ሲጋራ የሚያጨስ ሰው ወደ ሰውነቱ የሚያስገባው የኒኮቲን መጠን ሲጋራ አንድ ጊዜ ብቻ ሲስብ ከሚያስገባው በ200 እጥፍ ይበልጣል፤ ይህ ደግሞ ሌላ ማንኛውንም ዓይነት ዕፅ ቢወስድ ወደ ሰውነቱ ከሚያስገባው መጠን በእጅጉ የበለጠ ነው። አንድ ሰው ይህን ያህል መጠን ያለው ኒኮቲን አዘውትሮ መውሰዱ ከሌሎች ንጥረ ነገሮች ሁሉ በላይ በቀላሉ በኒኮቲን ሱስ የመያዝ አጋጣሚው ከፍ ያለ እንዲሆን ያደርጋል። አንድ ጊዜ ሱስ ከተጠናወተው በኋላ ደግሞ የኒኮቲን አምሮቱን ካላረካ ይህን ንጥረ ነገር እንዲወስድ የሚጎተጉት ኃይለኛ ስሜት ይኖረዋል።
‘ለምትታዘዙለት ነገር ባሪያዎች ናችሁ።’—ሮም 6:16
የትንባሆ ሱስ ባሪያ ከሆንክ በእርግጥ አምላክን መታዘዝ የምትችል ይመስልሃል?
መጽሐፍ ቅዱስ፣ በዚህ ረገድ ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖረን ይረዳናል፤ እንዲህ ይላል፦ “ለማንም ቢሆን እንደ ባሪያዎች ሆናችሁ ለመታዘዝ ራሳችሁን ካቀረባችሁ ለእሱ ስለምትታዘዙ የእሱ ባሪያዎች እንደሆናችሁ አታውቁም?” (ሮም 6:16) የአንድን ግለሰብ አስተሳሰብና ድርጊት የትንባሆ አምሮት የሚቆጣጠረው ከሆነ ግለሰቡ ብዙም ሳይቆይ ለዚህ የሚያዋርድ ልማድ ባሪያ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይሖዋ የተባለው አምላክ፣ ሰውነታችንን ከመጉዳት አልፈው መንፈሳችንን ይኸውም አስተሳሰባችንንም ከሚበክሉ ልማዶች ነፃ እንድንሆን ይፈልጋል። (ዘፀአት 6:3 የ1879 እትም፤ 2 ቆሮንቶስ 7:1) በመሆኑም አንድ ሰው ለይሖዋ ያለው አድናቆትና አክብሮት እየጨመረ ሲሄድ ለይሖዋ ምርጡን ሊሰጥ እንደሚገባ እንዲሁም ለዚህ ገዳይ ልማድ ባሪያ ከሆነ ለእሱ ምርጡን መስጠት እንደማይችል ይገነዘባል። ይህ ደግሞ ጎጂ ምኞቶችን ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል ይሰጠዋል።
በጀርመን የሚኖረው ኦላፍ በ12 ዓመቱ የጀመረውንና ለ16 ዓመታት አብሮት የቆየውን የሲጋራ ሱስ ማሸነፍ ችሏል። ኦላፍ ሲጋራ ማጨስ ሲጀምር ያን ያህል ጉዳት እንደሌለው ተሰምቶት ነበር። ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ግን ይህ ልማድ ከባድ ሱስ ሆነበት። እንዲህ ብሏል፦ “በአንድ ወቅት ሲጋራ አለቀብኝ፤ የሲጋራ አምሮቴ በጣም ስላየለብኝ ከመተርኮሻው ላይ የሲጋራ ቁርጥራጮችን በመሰብሰብ በውስጣቸው ያለውን ትንባሆ ካራገፍኩ በኋላ በጋዜጣ ጠቅልዬ አጨስኩት። አሁን ወደኋላ መለስ ብዬ ሳስበው እዚህ ደረጃ መድረስ በጣም አሳፋሪ ነገር ነው።” ታዲያ ኦላፍ ከዚህ የሚያዋርድ ልማድ መላቀቅ የቻለው እንዴት ነው? “የረዳኝ ዋናው ነገር ይሖዋን ለማስደሰት ያለኝ ፍላጎት ነው” ብሏል። “ይሖዋ ለሰው ዘር ያለው ፍቅርና የሰጠው ተስፋ ከዚህ ሱስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመላቀቅ የሚያስችል ብርታት ሰጠኝ።”
ማጨስ ሰውነትን ይጎዳል
“ሲጋራ ማጨስ አብዛኛውን የአካል ክፍል የሚጎዳ ከመሆኑም በላይ በበሽታ የመጠቃትና ለሕልፈተ ሕይወት የመዳረግ አጋጣሚ ከፍ እንዲል እንደሚያደርግ በሳይንስ ተረጋግጧል” በማለት ዘ ቶባኮ አትላስ ይናገራል። ማጨስ እንደ ካንሰር፣ የልብ ሕመምና የሳንባ ሕመሞች ያሉትን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እንደሚያስከትል በደንብ ይታወቃል። በተጨማሪም የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው ከሆነ ማጨስ፣ እንደ ሳንባ ነቀርሳ ባሉ ተላላፊ በሽታዎች ምክንያት ለሚከሰተው ሞት ዋና መንስኤ ነው።
አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ።”—ማቴዎስ 22:37
አምላክ የሰጠህን ሰውነት፣ በሚያረክስ ልማድ የምታበላሸው ከሆነ ለአምላክ ፍቅርና አክብሮት አለህ ሊባል ይችላል?
ይሖዋ አምላክ ለሕይወታችን፣ ለሰውነታችንና ለአእምሯችን ተገቢ አመለካከት እንዲኖረን በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ያስተምረናል። ልጁ ኢየሱስ “አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ” ብሎ መናገሩ ይህን ያሳያል። (ማቴዎስ 22:37) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው አምላክ ሕይወታችንንም ሆነ ሰውነታችንን በአግባቡ እንድንጠቀምበት ብሎም በአክብሮት እንድንይዘው ይፈልጋል። ስለ ይሖዋና ስለሰጣቸው ተስፋዎች እየተማርን ስንሄድ አምላክን መውደድና ያደረገልንን ነገሮች ሁሉ ማድነቅ እንጀምራለን። ይህ ደግሞ ሰውነታችንን ከሚያረክስ ከማንኛውም ነገር እንድንርቅ ያነሳሳናል።
በሕንድ የሚኖሩ ጄቨንዝ የሚባሉ አንድ ሐኪም ለ38 ዓመታት ያጨሱ ነበር። እንዲህ ብለዋል፦ “ማጨስ ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ የሕክምና መጽሔቶች ላይ አንብቤያለሁ። ማጨስ ስህተት እንደሆነ አውቃለሁ፤ ታካሚዎቼም ከዚህ ልማድ እንዲላቀቁ እመክራቸዋለሁ። ያም ቢሆን እኔ ራሴ ማጨስ ለማቆም አምስት ወይም ስድስት ጊዜ ያህል ብሞክርም ሊሳካልኝ አልቻለም።” ታዲያ በመጨረሻ እንዲያቆሙ የረዳቸው ምንድን ነው? እንዲህ ብለዋል፦ “ማጨስ እንዳቆም የረዳኝ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቴ ነው። ይሖዋን ለማስደሰት ያለኝ ፍላጎት ይህን ልማድ ወዲያውኑ እንዳቆም አነሳሳኝ።”
ማጨስ ሌሎችን ይጎዳል
የሚያጨስ ሰው ወደ ውጭ የሚያስወጣው የሲጋራ ጭስም ሆነ በቀጥታ ከሲጋራው የሚወጣው ጭስ መርዛማ ነው። ሌላ ሰው ለሚያጨሰው ሲጋራ ጭስ መጋለጥ ካንሰርና ሌሎች በሽታዎችን ሊያስከትል የሚችል ሲሆን አጫሽ ያልሆኑ 600,000 ሰዎች በየዓመቱ በዚህ ምክንያት ይሞታሉ፤ ከእነዚህም መካከል አብዛኞቹ ሴቶችና ሕፃናት ናቸው። የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣው አንድ ዘገባ “ለሲጋራ ጭስ በትንሹም ቢሆን መጋለጥ አደገኛ ነው” በማለት ያስጠነቅቃል።
“ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።”—ማቴዎስ 22:39
ባልንጀራህና ቤተሰብህ አንተ በማጨስህ ለሲጋራ ጭስ የሚጋለጡ ከሆነ በእርግጥ ትወዳቸዋለህ ማለት ይቻላል?
ኢየሱስ በተናገረው መሠረት አምላክን ከመውደድ ቀጥሎ ያለው ትልቁ ትእዛዝ ባልንጀራችንን ማለትም ቤተሰባችንን፣ ጓደኞቻችንንና በዙሪያችን ያሉ ሌሎች ሰዎችን መውደድ ነው። ኢየሱስ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” ብሏል። (ማቴዎስ 22:39) አጠገባችን ያሉ ሰዎችን የሚጎዳ ልማድ ካለን ለባልንጀራችን ፍቅር እያሳየን አይደለም። እውነተኛ ፍቅር “እያንዳንዱ ሰው ዘወትር የራሱን ጥቅም ሳይሆን የሌላውን ሰው ጥቅም ይፈልግ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተግባራዊ እንድናደርግ ያነሳሳናል።—1 ቆሮንቶስ 10:24
በአርሜንያ የሚኖረው አርመን እንደሚከተለው በማለት ያስታውሳል፦ “ቤተሰቤ፣ የእኔ ማጨስ ስለሚጎዳቸው እንዳላጨስ ለምነውኝ ነበር። እኔ ግን ሊጎዳቸው እንደሚችል ማመን አልፈለግሁም።” አመለካከቱን እንዲለውጥ ያደረገው ምን እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያገኘሁት እውቀትና ለይሖዋ ያለኝ ፍቅር ማጨስ እንዳቆም የረዳኝ ከመሆኑም ሌላ ማጨሴ እኔን ብቻ ሳይሆን በዙሪያዬ ያሉትንም እንደሚጎዳ እንድቀበል አደረገኝ።”
ማጨስ ለዘለቄታው ይወገዳል!
ኦላፍን፣ ጄቨንዝንና አርመንን በእነሱም ሆነ በሌሎች ላይ ጉዳት እያስከተለ ከነበረው ከዚህ የሚያዋርድ ልማድ እንዲላቀቁ የረዳቸው የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ነው። ሊሳካላቸው የቻለው ማጨስ ጎጂ እንደሆነ ስላወቁ ብቻ ሳይሆን ለይሖዋ ፍቅር ስላዳበሩና እሱን ለማስደሰት ስለሚፈልጉ ነው። ፍቅር የሚጫወተውን ወሳኝ ሚና 1 ዮሐንስ 5:3 እንደሚከተለው በማለት ያጎላል፦ “አምላክን መውደድ ማለት ትእዛዛቱን መጠበቅ ማለት ነውና፤ ትእዛዛቱ ደግሞ ከባዶች አይደሉም።” እርግጥ ነው፣ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች መከተል ቀላል የሚሆነው ሁልጊዜ አይደለም፤ ያም ቢሆን አንድ ሰው ለአምላክ ጥልቅ ፍቅር ካለው መታዘዝ ከባድ አይሆንበትም።
ይሖዋ አምላክ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ባለ የትምህርት ዘመቻ አማካኝነት በአሁኑ ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከትንባሆ ሱስ እንዲላቀቁ አሊያም መጀመሪያውኑ እንዲህ ያለ ባርነት ውስጥ እንዳይገቡ እየረዳቸው ነው። (1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) በቅርቡ ደግሞ ይሖዋ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በሚመራው ሰማያዊ መንግሥቱ አማካኝነት፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የትንባሆ ባሪያዎች ያደረገውን ስግብግብነት የሚንጸባረቅበት የንግድ ሥርዓት ያጠፋዋል። ይሖዋ፣ እንደ ወረርሽኝ የተስፋፋውን ይህን ልማድ ለዘለቄታው በማጥፋት ታዛዥ የሰው ዘሮችን በአካልም ሆነ በአእምሮ ወደ ፍጽምና ደረጃ እንዲደርሱ ይረዳቸዋል።—ኢሳይያስ 33:24፤ ራእይ 19:11, 15
ማጨስ ለማቆም እየታገልክ ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። አንተም ለይሖዋ ፍቅር ካዳበርክና ከማጨስ ጋር በተያያዘ የእሱ ዓይነት አመለካከት ካለህ ከዚህ ልማድ መላቀቅ ትችላለህ። የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በግለሰብ ደረጃ ሊያስተምሩህና በሥራ እንድታውል ሊረዱህ ፈቃደኞች ናቸው። ከትንባሆ ሱስ ለመላቀቅ የይሖዋን እርዳታ የምትፈልግ ከሆነ የሚያስፈልግህን ኃይልና ብርታት እንደሚሰጥህ እርግጠኛ ሁን።—ፊልጵስዩስ 4:13
^ አን.3 እዚህ ላይ ማጨስ ስንል ሲጋራና ፒፓ ማጨስን፣ የትንባሆ ቅጠል ጠቅልሎ ማጨስን ወይም እንደ ሺሻ ባሉ ዕቃዎች ተጠቅሞ ማጨስንም ይጨምራል። በሌላ በኩል ደግሞ እዚህ ላይ የተገለጸው ሐሳብ ትንባሆ ከማኘክ ወይም በአፍንጫ ከመሳብ እንዲሁም ኒኮቲን ያለው የኤሌክትሮኒክ ሲጋራ እና ሌሎች ተመሳሳይ ነገሮችን ከመጠቀም ጋር በተያያዘም በእኩል ደረጃ ይሠራል።