በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለልጆቻችሁ ተግሣጽ መስጠት የሚኖርባችሁ እንዴት ነው?

ለልጆቻችሁ ተግሣጽ መስጠት የሚኖርባችሁ እንዴት ነው?

“የመኪና ድምፅ በሰማሁ ቁጥር ጆሮዬን ቀስሬ ሳዳምጥ ስለቆየሁ ትዕግሥቴ እያለቀ መጣ። ጆርዳን ቤት እንዲገባ ከነገርነው ሰዓት ሲያሳልፍ ይህ ሦስተኛ ጊዜው ነበር። ‘ልጁ የት ገባ? የሆነ ችግር አጋጥሞት ይሆን? ምን ያህል እንዳስጨነቀን ይገባው ይሆን?’ የሚሉት ጥያቄዎች በአእምሮዬ ይጉላሉ ነበር። በመጨረሻም ጆርዳን ሲመጣ በንዴት ቱግ ብዬ ልናገረው ምንም አልቀረኝ።”ጆርጅ

“ልጄ ድንገት በኃይል ጮኸች፤ ደንግጬ ዘወር ብዬ ሳያት ራሷን ይዛ እያለቀሰች ነው። የጮኸችው የአራት ዓመት ልጅ የሆነው ወንድሟ መትቷት ነበር።”—ኒኮል

የስድስት ዓመቷ ናታሊ ሐቀኛ ለመምሰል ዓይኖቿን እያቁለጨለጨች “‘ቀለበቱን ሰርቄው አይደለም። አግኝቼው ነው!’ አለችን። ጥፋቷን ሽምጥጥ አድርጋ መካዷ አንጀታችንን ስላሳረረው አለቀስን። እየዋሸች መሆኗን አውቀን ነበር።”—ስቲቨን

ወላጅ ከሆንክ ከላይ ያሉትን ሐሳቦች የተናገሩትን ወላጆች ስሜት እንደምትረዳላቸው ግልጽ ነው። አንተም እንደ እነዚህ ያሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙህ ለልጅህ እንዴት ተግሣጽ መስጠት እንዳለብህ ግራ ትጋባለህ? አሊያም ደግሞ ‘ተግሣጽ መስጠት አለብኝ ወይስ የለብኝም’ ብለህ ታስባለህ? ለልጆችህ ተግሣጽ መስጠትህ ስህተት ነው?

ተግሣጽ ምንድን ነው?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ተግሣጽ” የሚለው ቃል የተሠራበት ቅጣትን ብቻ ለማመልከት አይደለም። ተግሣጽ በዋነኝነት የሚያመለክተው ትምህርት፣ ሥልጠናና እርማት መስጠትን ነው። ልጆችን መበደልን ወይም በጭካኔ መያዝን ለማመልከት ተሠርቶበት አያውቅም።—ምሳሌ 4:1, 2

ወላጆች የሚሰጡት ተግሣጽ አትክልትን ከመንከባከብ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። አንድ አትክልተኛ አፈሩን ያዘጋጃል፣ ተክሉ ውኃና ማዳበሪያ እንዲያገኝ ያደርጋል፤ እንዲሁም በጎጂ ነፍሳትና በአረም እንዳይጠቃ ይከላከላል። ተክሉ እያደገ ሲሄድ ደግሞ የሚፈለገውን አቅጣጫ እንዲይዝ ለማድረግ ሲል አትክልተኛው ተክሉን መግረዝ ሊያስፈልገው ይችላል። አትክልተኛው፣ ተክሉ ጤናማ እንዲሆን የተለያዩ ዘዴዎችን ጥሩ አድርጎ መጠቀም እንደሚኖርበት ይገነዘባል። በተመሳሳይም ወላጆች ለልጆቻቸው በተለያየ መንገድ እንክብካቤ ያደርጉላቸዋል። አንዳንድ ጊዜ ግን የተሳሳቱ ዝንባሌዎች ሥር ከመስደዳቸው በፊት ለማረምና ልጆቻቸው ትክክለኛውን አቅጣጫ ይዘው እንዲያድጉ ለመርዳት ተግሣጽ መስጠት ያስፈልጋቸዋል፤ ይህም ተክልን ከመግረዝ ጋር ይመሳሰላል። ይሁን እንጂ አንድ ተክል ሲገረዝ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፤ አለበለዚያ ተክሉ ዘላቂ ጉዳት ሊደርስበት ይችላል። በተመሳሳይም ወላጆች ተግሣጽ የሚሰጡት በፍቅር ሊሆን ይገባል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሰው ይሖዋ የተባለው አምላክ በዚህ ረገድ ለወላጆች ግሩም ምሳሌ ይሆናቸዋል። ይሖዋ ለምድራዊ አገልጋዮቹ የሚሰጠው ተግሣጽ በጣም ውጤታማና ጠቃሚ ከመሆኑ የተነሳ ተግሣጹን የተቀበሉት ሰዎች ‘ተግሣጽን የሚወዱ’ ይሆናሉ። (ምሳሌ 12:1) ምክርን ወይም ተግሣጽን ‘አጥብቀው ይይዛሉ’ ደግሞም ‘አይለቁትም።’ (ምሳሌ 4:13) እናንተም አምላክ ተግሣጽ የሚሰጥባቸውን ሦስት መንገዶች  በመከተል ልጃችሁን ከምትሰጡት ተግሣጽ እንዲጠቀም ልትረዱት ትችላላችሁ፤ ይሖዋ የሚሰጠው ተግሣጽ (1) በፍቅር ላይ የተመሠረተ፣ (2) ምክንያታዊ እና (3) የማይለዋወጥ ነው።

በፍቅር ላይ የተመሠረተ ተግሣጽ

አምላክ የሚሰጠው ተግሣጽ በፍቅር ላይ የተመሠረተ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “አባት ደስ የሚሰኝበትን ልጁን እንደሚቀጣ ሁሉ፣ እግዚአብሔርም የሚወደውን ይገሥጻል” ይላል። (ምሳሌ 3:12) ከዚህም በላይ ይሖዋ ‘ርኅሩኅና መሐሪ እንዲሁም ለቊጣ የዘገየ’ አምላክ ነው። (ዘፀአት 34:6 የታረመው የ1980 ትርጉም) በመሆኑም ይሖዋ የሚሰጠው ተግሣጽ የሚጎዳ ወይም ጭካኔ የተሞላበት አይደለም። ወይም ደግሞ መጥፎ ቃላት አይጠቀምም፤ ነቃፊ አይደለም እንዲሁም በአሽሙር አይናገርም፤ እንደ እነዚህ ያሉት አነጋገሮች ‘እንደ ሰይፍ ይወጋሉ።’—ምሳሌ 12:18

አዳምጡ

እርግጥ ነው፣ ወላጆች ራስን በመግዛት ረገድ እንደ አምላክ ፍጹም መሆን አትችሉም። አንዳንድ ጊዜ ትዕግሥታችሁ ሊያልቅ ይችላል፤ ይሁን እንጂ እንደ እነዚህ ባሉት አስቸጋሪ ወቅቶች ተቆጥቶ የሚሰጥ ቅጣት በአብዛኛው ጎጂና ከልክ ያለፈ እንደሚሆን እንዲሁም ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን አስታውሱ። ከዚህም በላይ በቁጣ ወይም በብስጭት የሚሰጥ ቅጣት፣ ተግሣጽ ሊባል አይችልም። እንዲህ ማድረግ ራስን መግዛት አለመቻል ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ፍቅርና ራስን መግዛት የተንጸባረቀበት ተግሣጽ የተሻለ ውጤት ያስገኛል። በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሱት ጆርጅና ኒኮል ምን እንዳደረጉ እንመልከት።

ጸልዩ

“ጆርዳን ቤት ሲገባ እኔና ባለቤቴ በንዴት ብግን ብለን ነበር፤ ይሁን እንጂ ራሳችንን ተቆጣጥረን ያመሸበትን ምክንያት ሲናገር አዳመጥነው። በጣም መሽቶ ስለነበር ጉዳዩን በነጋታው ልንወያይበት ወሰንን። ሁላችንም አንድ ላይ ጸለይንና ወደ መኝታችን ሄድን። በቀጣዩ ቀን በጉዳዩ ላይ ይበልጥ በተረጋጋና የልጃችንን ልብ ለመንካት በሚያስችል መንገድ ተነጋገርን። ጆርዳን የጣልንበትን እገዳ ለመቀበል የተስማማ ሲሆን ጥፋተኛ መሆኑን አምኖ ተቀበለ። እኛም፣ አንድ ሰው በተናደደበት ሰዓት በችኮላ እርምጃ መውሰዱ የሚፈለገውን ውጤት እንደማያስገኝ መገንዘባችን አስደስቶናል። የመጀመሪያው እርምጃችን ማዳመጥ ከሆነ አብዛኛውን ጊዜ ነገሮች የተሻለ ውጤት ይኖራቸዋል።”—ጆርጅ

ተነጋገሩ

“ልጄ እህቱን ምን ያህል እንደጎዳት ስመለከት በጣም ተናድጄ ነበር። በወቅቱ በጣም በመበሳጨቴ በሰከነ አእምሮ መወሰን እንደማልችል ስለተሰማኝ ወዲያውኑ እርምጃ አልወሰድኩም፤ ከዚህ ይልቅ ልጄን ወደ ክፍሉ እንዲሄድ አዘዝኩት። ከተረጋጋሁ በኋላ፣ የዓመፅ ድርጊት ተገቢ እንዳልሆነ ለልጄ ጠበቅ አድርጌ አስረዳሁት፤ እንዲሁም እህቱን ምን ያህል እንደጎዳት አሳየሁት። ይህ ዘዴ ጥሩ ውጤት አስገኝቷል። እህቱን ይቅርታ የጠየቃት ሲሆን አቅፎ አባበላት።”ኒኮል

በእርግጥም፣ ተገቢ የሆነ ተግሣጽ ቅጣትን ሊጨምር ቢችልም እንኳ ምንጊዜም በፍቅር ላይ የተመሠረተ ነው።

 ምክንያታዊ የሆነ ተግሣጽ

ይሖዋ ምንጊዜም ተግሣጽ የሚሰጠው በተገቢው ‘መጠን’ ነው። (ኤርምያስ 30:11፤ 46:28) ይሖዋ ተግሣጽ ሲሰጥ በግልጽ የማይታዩትን ጨምሮ ሁሉንም ሁኔታዎች ከግምት ያስገባል። ወላጆችስ እንዲህ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ስቲቨን እንዲህ ብሏል፦ “ናታሊ ቀለበቱን መስረቋን መካዷ ያሳዘነን ከመሆኑም ሌላ እንዲህ ያደረገችበትን ምክንያት መረዳት ቢከብደንም ዕድሜዋንና የብስለት ደረጃዋን ከግምት ለማስገባት ጥረት አደረግን።”

የኒኮል ባል ሮበርትም ሁኔታዎችን ሁሉ ከግምት ለማስገባት ጥረት ያደርጋል። ልጆቹ አጓጉል ጠባይ ሲያሳዩ ራሱን እንደሚከተለው በማለት ይጠይቃል፦ ‘ልጁ እንዲህ ዓይነት ድርጊት ሲፈጽም የመጀመሪያው ነው ወይስ ልማድ ሆኖበታል? ደክሞት ወይም አሞት ይሆን? ይህ ጠባይ ሌላ ችግር እንዳለበት የሚጠቁም ይሆን?’

በተጨማሪም ምክንያታዊ የሆኑ ወላጆች፣ ልጆች እንደ አዋቂ ሊያስቡ እንደማይችሉ ይገነዘባሉ። ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጳውሎስ “ሕፃን በነበርኩበት ጊዜ እንደ ሕፃን እናገር፣ እንደ ሕፃን አስብ . . . ነበር” ብሎ ሲጽፍ ይህን ገልጿል። (1 ቆሮንቶስ 13:11) ሮበርት እንዲህ ይላል፦ “ነገሮችን እንዳመዛዝንና ከመጠን በላይ እንዳልናደድ የሚረዳኝ አንዱ ነገር እኔ ራሴ ልጅ ሳለሁ ምን አደርግ እንደነበረ መለስ ብዬ ማሰቤ ነው።”

ከልጃችሁ በምትጠብቁት ነገር ረገድ ምክንያታዊ መሆን የሚያስፈልጋችሁ ቢሆንም በአንፃሩ ደግሞ መጥፎ ምግባርን ወይም ዝንባሌን ችላ ማለት አሊያም እንዲህ ላለው ነገር ሰበብ መፍጠር ተገቢ አይደለም። የልጃችሁን ችሎታዎች፣ የአቅም ገደቦችና ሌሎችንም ሁኔታዎች ከግምት የምታስገቡ ከሆነ ሚዛናዊና ምክንያታዊ ተግሣጽ መስጠት ትችላላችሁ።

የማይለዋወጥ ተግሣጽ

ሚልክያስ 3:6 “እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም” በማለት ይናገራል። የአምላክ አገልጋዮች በዚህ እውነት የሚተማመኑ ሲሆን ይሖዋ የማይለዋወጥ መሆኑን በማወቃቸው የደኅንነት ስሜት ይሰማቸዋል። ልጆችም የሚሰጣቸው ተግሣጽ የማይለዋወጥ ከሆነ በወላጆቻቸው ይተማመናሉ። በሌላ በኩል ግን የምታወጡት ደንብ እንደ ስሜታችሁ የሚለዋወጥ ከሆነ ልጃችሁ ግራ ሊገባውና ሊበሳጭ ይችላል።

ኢየሱስ “ቃላችሁ አዎ ከሆነ አዎ ይሁን፣ አይደለም ከሆነ አይደለም ይሁን፤ ከዚህ ውጭ የሆነ ግን ከክፉው ነው” ብሎ እንደተናገረ አስታውሱ። ይህ ሐሳብ ልጆችን ከማሳደግ ጋር በተያያዘም ይሠራል። (ማቴዎስ 5:37) ከቅጣት ጋር በተያያዘ፣ በኋላ ላይ እንደማታደርጉት የምታውቁትን ነገር ከመናገራችሁ በፊት ቆም ብላችሁ አስቡ። ልጃችሁ ካጠፋ አንድ ዓይነት ቅጣት እንደሚከተለው አስጠንቅቃችሁት ከሆነ የተናገራችሁትን መፈጸም አለባችሁ።

የማይለዋወጥ ተግሣጽ ለመስጠት በሁለቱ ወላጆች መካከል ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ሊኖር ይገባል። ሮበርት እንዲህ ብሏል፦ “ልጆቻችን ባለቤቴ የከለከለቻቸውን ነገር እኔ እንድፈቅድላቸው ካደረጉ ጉዳዩን ሳውቅ፣ የፈለጉትን ነገር እኔም እንደማልፈቅድላቸው በመግለጽ እሷን እደግፋታለሁ።” ወላጆች በአንድ ሁኔታ ላይ አቋማቸው ከተለያየ ለብቻቸው ሆነው በልዩነቶቻቸው ላይ መወያየታቸውና ስምምነት ላይ መድረሳቸው ጥሩ ነው።

ተግሣጽ አስፈላጊ ነው

እንደ ይሖዋ ሁሉ እናንተም በፍቅር ላይ የተመሠረተ፣ ምክንያታዊና የማይለዋወጥ ተግሣጽ የምትሰጡ ከሆነ የምታደርጉት ጥረት ልጆቻችሁን እንደሚጠቅማቸው እርግጠኞች መሆን ትችላላችሁ። የምትሰጧቸው ፍቅራዊ አመራር ልጆቻችሁ ሲያድጉ ብስለት ያላቸው፣ ኃላፊነት የሚሰማቸውና ሚዛናዊ እንዲሆኑ ሊረዳቸው ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው “ልጅን የሚሄድበትን መንገድ አስተምረው፤ በሚሸመግልበት ጊዜ ከዚያ ፈቀቅ አይልም።”—ምሳሌ 22:6