የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ጥሩ ሰዎች መጥፎ ነገሮች የሚደርሱባቸው ለምንድን ነው?
መጥፎ ነገሮች በዝተዋል!
ስሚታ * በዳካ፣ ባንግላዴሽ የምትኖር የ35 ዓመት ሴት ስትሆን አፍቃሪና አሳቢ በመሆኗ መልካም ስም አትርፋለች። ባለትዳር የሆነችው ስሚታ፣ ስለ አምላክ የተማረችውን ነገር ሌሎችም እንዲያውቁ መርዳት የምትፈልግ ታታሪና ደስተኛ ሴት በመሆኗ ትታወቃለች። ስሚታ በድንገት ታምማ አንድ ሳምንት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ስትሞት ቤተሰቧና ወዳጆቿ ምን ያህል እንደደነገጡ መገመት አያዳግትም!
በ30ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙት ጄምስና ባለቤቱም እንደ ስሚታ በሰዎች ዘንድ በመልካም የሚነሱ ባልና ሚስት ነበሩ። አንድ የጸደይ ወቅት በዩናይትድ ስቴትስ ምዕራባዊ ዳርቻ የሚኖሩ ወዳጆቻቸውን ለመጠየቅ ሄዱ። ሆኖም በኒው ዮርክ ወደሚገኘው ቤታቸው አልተመለሱም። በዚያ ሳሉ ባጋጠማቸው የመኪና አደጋ ምክንያት ሁለቱም ሕይወታቸውን አጡ፤ የእነሱ ሞት በቤተሰቦቻቸውና በሥራ ባልደረቦቻቸው ላይ ከፍተኛ ሐዘን አስከትሏል።
በዛሬው ጊዜ ክፋትና መከራ መብዛቱን ለመመልከት ሩቅ መሄድ አያስፈልግህም። በርካታ ወታደሮችና ሰላማዊ ሰዎች በጦርነት ይሞታሉ። ንጹሐን ሰዎች የወንጀልና የዓመፅ ሰለባ ይሆናሉ። በየትኛውም ዕድሜ ወይም የኑሮ ደረጃ ያሉ ሰዎች ሕይወትን የሚያሳጡ አደጋዎች እንዲሁም ከባድ የጤና እክሎች ያጋጥሟቸዋል። የትኛውም ማኅበረሰብ በተፈጥሮ አደጋዎች ይጠቃል። ጭፍን ጥላቻና የፍትሕ መዛባት ተስፋፍቷል። ምናልባትም አንተ ራስህ እንዲህ ዓይነት ነገር አጋጥሞህ ይሆናል።
ከዚህ አንጻር የሚከተሉትን ጥያቄዎች ብንጠይቅ የሚያስገርም አይሆንም፦
ጥሩ ሰዎች መጥፎ ነገሮች የሚደርሱባቸው ለምንድን ነው?
እንዲህ ላሉት ነገሮች ተጠያቂው አምላክ ነው?
አስከፊ ነገሮች የሚከሰቱት በአጋጣሚ ነው ወይስ ለእነዚህ ነገሮች ተጠያቂው የሰው ልጅ ነው?
አንድ ሰው መከራ የሚደርስበት በቀድሞ ሕይወቱ በሠራቸው ነገሮች (ካርማ) ምክንያት ነው?
ሁሉን ቻይ የሆነ አምላክ ካለ ጥሩ ሰዎች መጥፎ ነገር እንዳይደርስባቸው የማይጠብቃቸው ለምንድን ነው?
ክፋትና መከራ የሌለበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?
እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ‘መጀመሪያውኑ መጥፎ ነገሮች የሚደርሱት ለምንድን ነው? አምላክስ መጥፎ ነገሮችን ለማስወገድ ምን ያደርግ ይሆን?’ ለሚሉት ሁለት መሠረታዊ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ያስፈልገናል።
^ አን.3 ስሞቹ ተቀይረዋል።