በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሲሪያክ ፐሺታ—በጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ ብርሃን ፈነጠቀ

ሲሪያክ ፐሺታ—በጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ ብርሃን ፈነጠቀ

በ1892 አግነስ ስሚዝ ሌዊስ እና ማርጋሬት ደንሎፕ ጊብሰን የተባሉ ሁለት መንትያ እህትማማቾች ለዘጠኝ ቀናት በበረሃ ላይ በግመል ጉዞ በማድረግ በሲና ተራራ ግርጌ ወዳለው ሴይንት ካተሪና ገዳም ደረሱ። በ40ዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ላይ የነበሩት እነዚህ ሁለት እህትማማቾች በዚያ ዘመን ለጉዞ በጣም አደገኛ እንደሆነ በሚታሰበው በዚህ አካባቢ እንዲህ ዓይነቱን ጉዞ ለማድረግ ቆርጠው የተነሱት ለምን ነበር? የዚህ ጥያቄ መልስ መጽሐፍ ቅዱስ ትክክል ስለ መሆኑ ያለህን እምነት ያጠናክርልሃል።

አግነስ ስሚዝ ሌዊስ እና ሴይንት ካተሪና ገዳም

ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከመመለሱ ከጥቂት ጊዜ በፊት “በኢየሩሳሌምም ሆነ በመላው ይሁዳ፣ በሰማርያ እንዲሁም እስከ ምድር ዳር ድረስ” ስለ እሱ እንዲመሠክሩ ለደቀ መዛሙርቱ ተልእኮ ሰጥቷቸው ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 1:8) ደቀ መዛሙርቱም ይህንን ተልእኮ በቅንዓትና በድፍረት ፈጽመዋል። ይሁን እንጂ በኢየሩሳሌም የሚያከናውኑት አገልግሎት ብዙም ሳይቆይ ከባድ ተቃውሞ አስነሳባቸው፤ በዚህም ምክንያት እስጢፋኖስ ተገደለ። አብዛኞቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ወደ ሶርያዋ አንጾኪያ ሸሹ፤ ከኢየሩሳሌም በስተ ሰሜን 550 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ የምትገኘው አንጾኪያ በሮም ግዛት ከነበሩት ትላልቅ ከተሞች አንዷ ነበረች።—የሐዋርያት ሥራ 11:19

ደቀ መዛሙርቱ በአንጾኪያ ስለ ኢየሱስ የሚገልጸውን “ምሥራች” መስበካቸውን የቀጠሉ ሲሆን አይሁዳውያን ያልሆኑ ብዙ ሰዎችም አማኞች ሆኑ። (የሐዋርያት ሥራ 11:20, 21) በአንጾኪያ ከተማ ውስጥ በስፋት የሚነገረው ቋንቋ ግሪክኛ ቢሆንም ከከተማው ውጭና በክፍለ አገሩ ግን ሕዝቡ የሚጠቀመው ሲሪያክ የሚባለውን ቋንቋ ነበር።

ምሥራቹ በሲሪያክ ቋንቋ ተተረጎመ

በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. አካባቢ የሲሪያክ ተናጋሪ ክርስቲያኖች ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ ምሥራቹ በቋንቋቸው መተርጎሙ አስፈላጊ ሆነ። በመሆኑም በዚያ አካባቢ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት በከፊል ለመጀመሪያ ጊዜ የተተረጎሙት በላቲን ሳይሆን በሲሪያክ ቋንቋ ሳይሆን አይቀርም።

 ቴሸን የሚባለው ሶርያዊ ጸሐፊ (120-173 ዓ.ም. ገደማ) በ170 ዓ.ም. ገደማ ትክክለኛዎቹን አራት ወንጌሎች በማዋሃድ በተለምዶ ዳያቴሳሮን በመባል የሚታወቀውን ጽሑፍ በግሪክኛ ወይም በሲሪያክ ቋንቋ አዘጋጀ፤ ዳያቴሳሮን የሚለው የግሪክኛ ቃል ትርጉሙ “ከአራቱ [ወንጌሎች]” ማለት ነው። ሶርያዊው ኢፍራይም (310-373 ዓ.ም. ገደማ) ከጊዜ በኋላ ዳያቴሳሮንን የሚያብራራ ጽሑፍ ማዘጋጀቱ ዳያቴሳሮን በሶርያ ክርስቲያኖች ዘንድ በስፋት ይታወቅ እንደነበረ ያረጋግጣል።

ዳያቴሳሮን በዛሬው ጊዜ ያለነውን የእኛንም ትኩረት ይስባል። ለምን? በ19ኛው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ምሁራን፣ ወንጌሎች የተጻፉት በሁለተኛው መቶ ዘመን ማለትም ከ130 እስከ 170 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ስለሆነ የኢየሱስን ሕይወት አስመልክቶ የያዙት ዘገባ እምነት ሊጣልበት አይችልም እያሉ ይከራከሩ ነበር። ይሁን እንጂ ከ19ኛው መቶ ዘመን ወዲህ የተገኙት በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ የዳያቴሳሮን ቅጂዎች የማቴዎስ፣ የማርቆስ፣ የሉቃስና የዮሐንስ ወንጌሎች በሁለተኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ በስፋት ተሰራጭተው እንደነበር አረጋግጠዋል። በመሆኑም ወንጌሎቹ የተጻፉት ከዚያ በጣም ቀደም ብሎ መሆን አለበት። በተጨማሪም ቴሸን ዳያቴሳሮንን ሲያዘጋጅ በዋነኝነት የተጠቀመው ተቀባይነት ያላቸውን አራቱን ወንጌሎች ነው፤ ይህም አዋልድ ተብለው የሚጠሩት ወንጌሎች እምነት የሚጣልባቸው ወይም ተቀባይነት ያላቸው እንደሆኑ ተደርገው ይታዩ እንዳልነበረ በግልጽ ያሳያል።

አምስቱን የኦሪት መጻሕፍት የያዘ ሲሪያክ ፐሺታ፣ 464 ዓ.ም.፣ የተዘጋጁበትን ዘመን በግልጽ ከሚናገሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በጥንታዊነቱ ሁለተኛውን ደረጃ ይይዛል

በሲሪያክ የተተረጎመ መጽሐፍ ቅዱስ በአምስተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ በሰሜን ሜሶጶጣሚያ በሰፊው ጥቅም ላይ ውሎ ነበር። በሁለተኛው ወይም በሦስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. እንደተዘጋጀ የሚታሰበው ይህ ትርጉም ከ2ኛ ጴጥሮስ፣ ከ2ኛ እና ከ3ኛ ዮሐንስ፣ ከይሁዳ እንዲሁም ከራእይ መጻሕፍት በቀር ሁሉንም የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ያካተተ ነበር። ይህ ትርጉም ፐሺታ በመባል የሚታወቅ ሲሆን ፐሺታ የሚለው ቃል “ቀላል” ወይም “ግልጽ” ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በጥንት ዘመን በሰፊው ተሰራጭቶ እንደነበር ከሚያሳዩት ጥንታዊና ወሳኝ ትርጉሞች አንዱ ፐሺታ ነው።

የሚገርመው ነገር በእጅ የተገለበጠ አንድ የፐሺታ ቅጂ በ459/460 ዓ.ም. እንደተጻፈ የሚጠቁም ጽሑፍ አለው፤ በዚህም የተነሳ ይህ ቅጂ፣ የተዘጋጁበትን ዘመን በግልጽ ከሚናገሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ሁሉ ጥንታዊው ሊሆን ችሏል። በ508 ዓ.ም. ገደማ ተሻሽሎ የወጣው የፐሺታ ትርጉም ቀደም ሲል ያልተካተቱትን አምስት መጻሕፍት አካትቶ ነበር። ይህ ትርጉም ፊሎሲኒያን ቨርዥን ተብሎ ይጠራል።

ሌሎች የሲሪያክ ጥንታዊ ጽሑፎች ተገኙ

እስከ 19ኛው መቶ ዘመን ድረስ ከተገኙት በግሪክኛ የተዘጋጁ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት መካከል አብዛኞቹ በአምስተኛው መቶ ዘመን ወይም ከዚያ ወዲህ ብዙ ቆይቶ የተዘጋጁ ነበሩ። በዚህም ምክንያት እንደ ላቲን ቩልጌት እና ሲሪያክ ፐሺታ ያሉት ጥንታዊ ትርጉሞች የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራንን ትኩረት ስበው ነበር። በወቅቱ አንዳንዶች፣ ፐሺታ ከሌላ ጥንታዊ የሲሪያክ ትርጉም ተሻሽሎ የወጣ እንደሆነ ያምኑ ነበር። ይሁን እንጂ በወቅቱ እንዲህ ያለ ጥንታዊ ጽሑፍ አልተገኘም። በሲሪያክ ቋንቋ ለተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስ መሠረት የሆነው ትርጉም በሁለተኛው መቶ ዘመን አካባቢ እንደተዘጋጀ ስለሚገመት ይህ ትርጉም ቢገኝ ለመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ትልቅ ጥቅም እንደሚያስገኝ ጥርጥር የለውም፤ ምክንያቱም ይህ ትርጉም ቀደም ሲል ስለተዘጋጁት ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ብርሃን ይፈነጥቅ ነበር! ይሁንና እንዲህ ያለ ጥንታዊ የሲሪያክ ትርጉም ነበር?

ሳይናይቲክ ሲሪያክ የተባለው ቅጂ። ከወንጌሎቹ ሳይፋቅ የቀረው ክፍል በኅዳጉ ላይ ይታያል

አዎን! እንዲያውም በእጅ የተገለበጡ ሌሎች ሁለት ጥንታዊ የሲሪያክ ቅጂዎች መገኘታቸው እንዲህ ዓይነት ትርጉም እንደነበረ ያረጋግጣል። አንደኛው ቅጂ በአምስተኛው መቶ ዘመን የተዘጋጀ ነው። ይህ ቅጂ በ1842 የብሪትሽ ሙዚየም በግብፅ በኒትሪያን በረሃ ካለው ገዳም ካገኛቸው በርካታ ቁጥር ያላቸው በእጅ የተገለበጡ የሲሪያክ ጽሑፎች መካከል አንዱ ነው። ጽሑፉን ያገኘውና ለኅትመት ያበቃው በሙዚየሙ የጥንታዊ ጽሑፎች ረዳት ኃላፊ የሆነው ዊልያም ኪዩርተን በመሆኑ ቅጂው ኪዩርተኒያን ሲሪያክ ተብሎ ተጠርቷል። ይህ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሰነድ አራቱን ወንጌሎች የያዘ ሲሆን መጽሐፎቹ የተቀመጡት ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ዮሐንስና ሉቃስ በሚለው ቅደም ተከተል ነው።

እስከ ዘመናችን ሳይጠፋ የቆየው ሁለተኛው በእጅ የተገለበጠ ቅጂ ደግሞ ሳይናይቲክ ሲሪያክ ይባላል። የዚህ ጥንታዊ ቅጂ መገኘት በመግቢያው ላይ ከተጠቀሱት ደፋር መንትያ እህትማማቾች ጋር የተያያዘ ነው። አግነስ የዩኒቨርሲቲ ዲግሪ ባይኖራትም ስምንት የውጭ ቋንቋዎችን ተምራለች፤ ከእነዚህ አንዱ ሲሪያክ ነበር። በ1892 አግነስ በግብፅ በሴይንት ካተሪና ገዳም ውስጥ አንድ አስደናቂ ነገር አገኘች።

 አግነስ በዚያ በአንድ ጠባብ ጨለማ ክፍል ውስጥ በእጅ የተገለበጠ የሲሪያክ ጽሑፍ አገኘች። አግነስ በታሪኳ ላይ እንደገለጸችው መጽሐፉ “የሚያስጠላ መልክ ነበረው፤ ምክንያቱም በጣም ቆሽሾ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ገጾቹም [ለብዙ መቶ ዘመናት] ሳይገለጡ በመኖራቸው እርስ በርሳቸው ተጣብቀው ነበር።” በዚህ ቅጂ ላይ የነበረው የመጀመሪያ ጽሑፍ ተፍቆ በላዩ ላይ ስለ እንስት ቅዱሳን የሚናገር ታሪክ በሲሪያክ ቋንቋ ተጽፎበት ነበር። ይሁን እንጂ አግነስ በቅጂው ላይ በአንዳንድ ቦታዎች ከሥር የሚታየውን ጽሑፍ እንዲሁም በገጾቹ አናት ላይ “የማቴዎስ”፣ “የማርቆስ”፣ ወይም “የሉቃስ” የሚሉትን ቃላት መመልከት ችላ ነበር። በእጇ የያዘችው ጽሑፍ የአራቱን ወንጌሎች አብዛኛውን ክፍል የያዘ ሙሉው ሲሪያክ ኮዴክስ ነበር! በአሁኑ ጊዜ ምሁራን ይህ ኮዴክስ በአራተኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ እንደተጻፈ ደርሰውበታል።

ሳይናይቲክ ሲሪያክ፣ በግሪክኛ ከተጻፉት እንደ ኮዴክስ ሳይናይቲከስ እና ኮዴክስ ቫቲካነስ ካሉ እጅግ ከፍ ያለ ግምት የሚሰጣቸው በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ተርታ የሚመደብ ነው። የኪዩርተኒያን እና የሳይናይቲክ ቅጂዎች በሁለተኛው መቶ ዘመን መጨረሻ ወይም በሦስተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ከተጻፉት ጥንታዊ የሲሪያክ ወንጌሎች ላይ የተገለበጡ ቅጂዎች እንደሆኑ ይታመናል።

“የአምላካችን ቃል . . . ለዘላለም ይኖራል”

እነዚህ በእጅ የተገለበጡ ጽሑፎች በዛሬው ጊዜ ላሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ይጠቅማሉ? ምን ጥያቄ አለው! ለምሳሌ ያህል፣ በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ ከማርቆስ 16:8 በኋላ የሚገኘውን ረጅም መደምደሚያ ተብሎ የሚጠራውን ክፍል እንመልከት። ይህ ክፍል በአምስተኛው መቶ ዘመን በተዘጋጀው የግሪክኛ ኮዴክስ አሌክሳንድሪነስ፣ በላቲን ቩልጌት እና በሌሎች ትርጉሞችም ላይ ይገኛል። ይሁን እንጂ በአራተኛው መቶ ዘመን በግሪክኛ የተዘጋጁት ኮዴክስ ሳይናይቲከስ እና ኮዴክስ ቫቲካነስ የተባሉት እምነት የሚጣልባቸው ትርጉሞች የማርቆስን ወንጌል የሚደመድሙት ማርቆስ 16:8 ላይ ነው። ይህ ረጅም መደምደሚያ በሳይናይቲክ ሲሪያክ ላይም ቢሆን አልተካተተም፤ ይህም ረጅሙ መደምደሚያ ከጊዜ በኋላ የተጨመረ እንጂ በመጀመሪያው የማርቆስ ወንጌል ውስጥ ያልነበረ ለመሆኑ ተጨማሪ ማስረጃ ይሆናል።

አንድ ሌላ ምሳሌም እንመልከት። በ19ኛው መቶ ዘመን የተዘጋጁት አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በ1 ዮሐንስ 5:7 ላይ ስለ ሥላሴ የሚገልጽ የተሳሳተ ሐሳብ ጨምረው ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ተጨማሪ ሐሳብ ጥንታዊ በሆኑት በእጅ የተገለበጡ ግሪክኛ ጽሑፎች ውስጥ የለም። ይህ ሐሳብ በፐሺታ ትርጉም ውስጥ አለመገኘቱም በ1 ዮሐንስ 5:7 ላይ የሚገኘው ተጨማሪ ሐሳብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ የሆነ የተሳሳተ ሐሳብ እንደሆነ ያረጋግጣል።

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ይሖዋ አምላክ ቃል በገባው መሠረት ቅዱስ ቃሉ እንዲጠበቅ አድርጓል። “ሣሩ ይደርቃል፤ አበባውም ይረግፋል፤ የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” የሚል ማረጋገጫ በቃሉ ውስጥ እናገኛለን። (ኢሳይያስ 40:8፤ 1 ጴጥሮስ 1:25) ፐሺታ የተባለው ትርጉም የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ለሰው ዘር በትክክል እንዲተላለፍ ትንሽ ሆኖም የማይናቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል።