“ጥልቅ ማስተዋል ሰውን ቶሎ እንዳይቆጣ ያደርገዋል”
የአንድ ኮሌጅ የቅርጫት ኳስ ቡድን አሠልጣኝ ንዴቱን መቆጣጠር ባለመቻሉ ከሥራ ተባረረ።
አንድ ትንሽ ልጅ የፈለገውን ነገር ስላላገኘ እየጮኸ ማልቀስ ጀመረ።
አንዲት እናት ልጇ ክፍሉን በማዝረክረኩ ከእሱ ጋር መጯጯህ ጀመረች።
ሁላችንም ሌሎች ሰዎች ሲቆጡ አይተን እናውቃለን፤ እኛ ራሳችንም የተቆጣንበት ጊዜ እንደሚኖር ጥርጥር የለውም። ቁጣ ልንቆጣጠረው የሚገባ አሉታዊ ስሜት እንደሆነ ይሰማን ይሆናል፤ ይሁንና ፍትሕ እንደተጓደለ ሲሰማን ወይም በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ፣ መቆጣት እንዳለብን የምናስብበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። እንዲያውም የአሜሪካ የሥነ አእምሮ ማኅበር ያዘጋጀው አንድ ጽሑፍ “ቁጣ ሙሉ በሙሉ ተፈጥሯዊና አብዛኛውን ጊዜም ጤናማ የሆነ ስሜት ነው” ብሏል።
ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ የጻፈውን ሐሳብ ስንመለከት ይህ ዓይነቱ አመለካከት ትክክል ሊመስለን ይችላል። ጳውሎስ ልንቆጣ የምንችልበት አጋጣሚ እንደሚኖር ሲገልጽ “ተቆጡ፤ ነገር ግን ኃጢአት አትሥሩ፤ ተቆጥታችሁ እያለ ፀሐይ አይጥለቅባችሁ” ብሏል። (ኤፌሶን 4:26) ታዲያ ከዚህ አንጻር ቁጣን መልቀቅ ተገቢ ነው? ወይስ አንድ ሰው ቁጣውን ለመቆጣጠር የቻለውን ሁሉ ማድረግ ይኖርበታል?
መቆጣት ይኖርብሃል?
ጳውሎስ ስለ ቁጣ ከላይ የተጠቀሰውን ምክር የሰጠው “ስትቈጡ ኀጢአት አትሥሩ” በማለት አንድ መዝሙራዊ የጻፈውን ሐሳብ በአእምሮው ይዞ መሆን አለበት። (መዝሙር 4:4) ይሁንና ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ እንዲህ ያለ ምክር የሰጠው ለምንድን ነው? በመቀጠል “የመረረ ጥላቻ፣ ቁጣ፣ ንዴት፣ ጩኸትና ስድብ ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ መካከል ይወገድ” በማለት ገልጿል። (ኤፌሶን 4:31) የጳውሎስ ዓላማ ክርስቲያኖች ቁጣቸውን እንዲቆጣጠሩ ማበረታታት ነበር። የአሜሪካ የሥነ አእምሮ ማኅበር ያዘጋጀው አንድ ጽሑፍ የገለጸው ሐሳብ ትኩረት የሚስብ ነው፤ እንዲህ ብሏል፦ “በመስኩ የተደረገው ጥናት እንዳረጋገጠው ‘በቁጣ መገንፈል’ ይበልጥ እንድንቆጣና ጠብ እንዲፈጠር ከማድረግ በቀር . . . ችግሩን ለመፍታት የሚፈይደው ነገር የለም።”
ታዲያ ቁጣንና ቁጣ የሚያስከትለውን መዘዝ ‘ማስወገድ’ የምንችለው እንዴት ነው? የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ጠቢቡ ሰሎሞን “ጥልቅ ማስተዋል ሰውን ቶሎ እንዳይቆጣ ያደርገዋል፤ በደልንም መተዉ ውበት ያጎናጽፈዋል” በማለት ጽፏል። (ምሳሌ 19:11 NW) አንድ ሰው “ጥልቅ ማስተዋል” ያለው መሆኑ በቁጣ እንዳይገነፍል የሚረዳው እንዴት ነው?
ማስተዋል ቶሎ እንዳንቆጣ የሚረዳን እንዴት ነው?
ማስተዋል አንድን ነገር ጠለቅ ብሎ የማየት ችሎታ ነው። አንድ ሰው ማስተዋል አለው የሚባለው ከአንድ ሁኔታ በስተ ጀርባ ያለውን ነገር መመልከት ሲችል ነው። የሚያስቆጣ ወይም የሚያበሳጭ ነገር ሲያጋጥመን እንዲህ ዓይነቱ ችሎታ የሚረዳን እንዴት ነው?
ፍትሕ እንደተጓደለ ሲሰማን ልንቆጣ እንችል ይሆናል። ይሁን እንጂ በስሜት ተገፋፍተን አጸፋውን የምንመልስ ወይም የኃይል እርምጃ የምንወስድ ከሆነ ራሳችንን ወይም ሌሎችን መጉዳታችን አይቀርም። ከቁጥጥር ውጭ የሆነ እሳት አንድን ቤት ሙሉ በሙሉ እንደሚያቃጥለው ሁሉ ቁጣም በሌሎች ዘንድ ያለንን መልካም ስም እንዲሁም ከሰዎች ጋር ሌላው ቀርቶ ከአምላክ ጋር ያለንን ግንኙነት ሊያበላሽብን ይችላል። በመሆኑም እንድንቆጣ የሚያደርግ ነገር ሲያጋጥመን ሁኔታውን ጠለቅ ብለን ለማየት ጥረት ማድረግ አለብን። ስለተፈጠረው ሁኔታ የተሟላ ግንዛቤ ካለን ስሜታችንን መቆጣጠር ይበልጥ ቀላል እንደሚሆንልን ጥርጥር የለውም።
የሰለሞን አባት የሆነው ንጉሥ ዳዊት፣ ናባል ከተባለ ሰው ጋር በተያያዘ በተፈጠረው ሁኔታ ደም ከማፍሰስ የተቆጠበው ለጥቂት ነበር፤ ይህም የሆነው ስለ ሁኔታው ቆም ብሎ እንዲያስብ የሚያስችል እርዳታ ስላገኘ ነው። ዳዊትና ከእሱ ጋር የነበሩት ሰዎች በይሁዳ ምድረ በዳ ሳሉ ለናባል በጎች ጥበቃ ያደርጉላቸው ነበር። በጎቹ የሚሸለቱበት ጊዜ ሲደርስ ዳዊት ናባልን ምግብ እንዲልክለት ጠየቀው። በዚህ ጊዜ ናባል ‘እንጀራዬንና ውሃዬን እንዲሁም በጎቼን ለሚሸልቱልኝ ሰዎች ያረድሁትን ፍሪዳ ከየት እንደመጡ ለማይታወቁ ሰዎች የምሰጠው ለምንድን ነው?’ የሚል መልስ ሰጠ። እንዴት ያለ የሚያቃልል ንግግር ነው! ዳዊት ናባል የተናገረውን ሲሰማ 400 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ይዞ ናባልንና ቤተሰቡን ለማጥፋት ጉዞ ጀመረ።—1 ሳሙኤል 25:4-13
የናባል ሚስት አቢግያ ስለ ሁኔታው ስትሰማ ወደ ዳዊት ሄደች። ዳዊትንና ሰዎቹን ስታገኛቸው የዳዊት እግር ላይ ወድቃ “እባክህ አገልጋይህ ታናግርህ፤ የምትልህንም ስማ” አለችው። ከዚያም ናባል ማስተዋል የሌለው ሰው እንደሆነ እንዲሁም ዳዊት የበቀል እርምጃ በመውሰድ ደም ቢያፈስስ በኋላ ላይ እንደሚጸጽተው ተናገረች።—1 ሳሙኤል 25:24-31
አቢግያ የተናገረችው ሐሳብ ዳዊት ምን ማስተዋል እንዲያገኝ አስችሎታል? አንደኛ፣ ናባል በተፈጥሮው ማስተዋል የሌለው ሰው እንደሆነ ተገነዘበ፤ ሁለተኛ፣ የበቀል እርምጃ መውሰዱ በደም ማፍሰስ ድርጊት ተጠያቂ እንደሚያደርገው ተረዳ። እንደ ዳዊት ሁሉ አንተም በሆነ ነገር ልትናደድ ትችላለህ። ታዲያ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ማዮ ክሊኒክ ቁጣን ስለ መቆጣጠር ያዘጋጀው አንድ ጽሑፍ “ለአፍታ በረጅሙ ተንፍስና ከ1 እስከ 10 ቁጠር” በማለት ይመክራል። አዎን፣ ችግሩ ምን እንደሆነና አንተ ልትወስድ ያሰብከው እርምጃ ምን እንደሚያስከትል ቆም ብለህ አስብ። ማስተዋል ቁጣህን እንዲያበርድልህ ብሎም ሙሉ በሙሉ ስሜቱን እንዲያጠፋልህ ፍቀድ።—1 ሳሙኤል 25:32-35
በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ቁጣቸውን ለመቆጣጠር የሚያስችል እርዳታ አግኝተዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ሴባስቲያን የተባለ አንድ ሰው በ23 ዓመቱ በፖላንድ እስር ቤት ውስጥ ሳለ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ፤ ይህም የግልፍተኝነት ባሕርዩን መቆጣጠር የሚችለው እንዴት እንደሆነ እንዲማር ረድቶታል። ሴባስቲያን እንዲህ ብሏል፦ “መጀመሪያ፣ ስለተፈጠረው ችግር አስባለሁ። ከዚያም የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ እጥራለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ ከሁሉ የተሻለ መመሪያ የያዘ መጽሐፍ መሆኑን ተረድቻለሁ።”
ሴትሱኦ የተባለ ሰውም ተመሳሳይ ነገር አድርጓል። እንዲህ ብሏል፦ “በሥራ ቦታ ሰዎች ሲያናድዱኝ እጮህባቸው ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ካጠናሁ በኋላ ግን ከመጮኽ ይልቅ ‘ጥፋተኛው ማን ነው? ለተፈጠረው ችግር ምክንያቱ እኔ አይደለሁም?’ እያልኩ ማሰብ ጀመርኩ።” ሴትሱኦ እንዲህ እያለ ማሰቡ ቁጣው እንዲበርድለት እንዲሁም የሚያናድድ ነገር ሲያጋጥመው ስሜቱን መቆጣጠር እንዲችል ረድቶታል።
የቁጣ ስሜት ኃይለኛ ነው፤ ከአምላክ ቃል የሚገኘው ምክር ግን ከዚህ የሚበልጥ ኃይል አለው። የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ተግባራዊ የምታደርግና አምላክ እንዲረዳህ የምትጸልይ ከሆነ ማስተዋል ቶሎ እንዳትቆጣ ወይም ቁጣህን መቆጣጠር እንድትችል ይረዳሃል።