በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ኢየሱስ ያድናል—ከምን?

የኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ለአንተ ምን ትርጉም አለው?

የኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ለአንተ ምን ትርጉም አለው?

‘በጌታ ኢየሱስ እመን፤ ትድናለህ።’—የሐዋርያት ሥራ 16:31

ይህ ከአእምሮ የማይጠፋ ሐሳብ፣ ሐዋርያው ጳውሎስና ሲላስ የመቄዶንያ ከተማ በነበረችው በፊልጵስዩስ ለሚገኝ የእስር ቤት ጠባቂ የተናገሩት ነው። ለመሆኑ የዚህ ጥቅስ ትርጉም ምንድን ነው? በኢየሱስ ማመን ከሞት የሚያድነን እንዴት እንደሆነ ለመረዳት በቅድሚያ የምንሞተው ለምን እንደሆነ ማወቅ አለብን። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚል እስቲ እንመልከት።

ሰዎች የተፈጠሩት እንዲሞቱ አይደለም

“አምላክ ሰውን ወስዶ እንዲያለማትና እየተንከባከበ እንዲጠብቃት በዔድን የአትክልት ስፍራ አስቀመጠው። እግዚአብሔር አምላክ ሰውን እንዲህ በማለት አዘዘው፤ ‘በአትክልት ስፍራው ውስጥ ከሚገኝ ከማንኛውም ዛፍ ፍሬ ትበላለህ። ነገር ግን መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ አትብላ፤ ምክንያቱም ከእርሱ በበላህ ቀን በእርግጥ ትሞታለህ።’”—ዘፍጥረት 2:15-17

አምላክ የመጀመሪያውን ሰው አዳምን በኤደን የአትክልት ስፍራ ውስጥ አስቀመጠው፤ በምድር ላይ የሚገኘው ይህ ገነት በዱር እንስሳት የተሞላ ከመሆኑም ሌላ ውብ ልምላሜ ነበረው። አዳም በዚህ ገነት ውስጥ ከሚገኙ ፍሬ የሚያፈሩ ዛፎች እንደፈለገው መመገብ ይችል ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ አምላክ አንድን ዛፍ ለይቶ በመጥቀስ ከዚያ ዛፍ ፍሬ እንዳይበላ ለአዳም ነገረው፤ ከበላ ግን እንደሚሞት አስጠነቀቀው።

አዳም ይህን ማስጠንቀቂያ ተረድቶት ነበር? አዳም ሞት ምን እንደሆነ ያውቅ ነበር፤ ምክንያቱም እንስሳት ሲሞቱ አይቷል። አዳም የተፈጠረው ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እንዲሞት ቢሆን ኖሮ አምላክ የሰጠው ማስጠንቀቂያ ምንም ትርጉም አይኖረውም ነበር። ከዚህ ይልቅ አዳም አምላክን ከታዘዘና ከተከለከለው ዛፍ ፍሬ ካልበላ ፍጻሜ ለሌለው ጊዜ እንደሚኖር እንጂ እንደማይሞት ተገንዝቦ መሆን አለበት።

አንዳንዶች ዛፉ የሚያመለክተው የፆታ ግንኙነትን እንደሆነ ያምናሉ፤ ይህ ግን ሊሆን አይችልም። እንዲያውም አዳምና ሔዋን ‘እንዲበዙ እንዲሁም ምድርን እንዲሞሏትና እንዲገዟት’ ይሖዋ ይፈልግ ነበር። (ዘፍጥረት 1:28) በመሆኑም አዳምና ሔዋን የተከለከሉት በገነት ውስጥ ከነበረ አንድ እውነተኛ ዛፍ እንዳይበሉ ነው። ዛፉ፣ ለሰዎች መልካምና ክፉ የሆነው ነገር ምን እንደሆነ የመወሰን መብት ያለው ይሖዋ እንደሆነ የሚያመለክት በመሆኑ ‘መልካምና ክፉን የሚያሳውቅ ዛፍ’ ተብሎ ተጠርቷል። አዳም ከዚህ ዛፍ ፍሬ አለመብላቱ ታዛዥ እንደሆነ ብቻ ሳይሆን ለፈጠረውና እጅግ አብዝቶ ለባረከው አምላክ አድናቆት እንዳለው የሚያሳይ ነበር።

አዳም የሞተው አምላክን ባለመታዘዙ ነው

ምላክ አዳምን እንዲህ አለው፦ “‘ከእርሱ አትብላ’ ብዬ ያዘዝሁህን ዛፍ በልተሃል፣ . . . ከምድር ስለ ተገኘህ፣ ወደ መጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ እንጀራህን በፊትህ ላብ ትበላለህ፤ ዐፈር ነህና ወደ ዐፈር ትመለሳለህ።”—ዘፍጥረት 3:17, 19

አዳም፣ እንዳይበላ ከተከለከለው ዛፍ በላ። የእሱ አለመታዘዝ በቀላሉ የሚታለፍ ነገር አልነበረም። አዳም የፈጸመው ድርጊት ዓመፅ ነው፤ እንዲሁም ይሖዋ ለእሱ ያደረገለትን መልካም ነገሮች ሁሉ ከምንም እንዳልቆጠራቸው በግልጽ ያሳያል። አዳም ከተከለከለው ፍሬ መብላቱ ይሖዋን እንደ ገዢው አድርጎ እንደማይቀበልና በራሱ መመራት እንደሚፈልግ የሚጠቁም ነው፤ ይህም አስከፊ መዘዞችን አስከትሏል።

ይሖዋ አስቀድሞ በተናገረው መሠረት አዳም ከጊዜ በኋላ ሞተ። አምላክ አዳምን የፈጠረው “ከምድር ዐፈር” ሲሆን ‘ወደ ዐፈር እንደሚመለስም’ ነግሮት ነበር። አዳም ከሞተ በኋላ ሌላ ዓይነት አካል ይዞ ወይም በሌላ ዓለም ውስጥ መኖሩን አልቀጠለም። ሲሞት ልክ ሲፈጠር እንደተሠራበት አፈር ሕይወት አልባ ሆነ።—ዘፍጥረት 2:7፤ መክብብ 9:5, 10

የምንሞተው የአዳም ዘሮች ስለሆንን ነው

“በአንድ ሰው አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ።”—ሮም 5:12

የአዳም አለመታዘዝ ወይም ኃጢአት ብዙ መዘዞች አስከትሏል። ኃጢአት በመሥራቱ ያጣው አሁን እንደምንኖረው የ70 ወይም የ80 ዓመት ሕይወትን ሳይሆን ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያለውን ሕይወት ነው። ከዚህም በላይ አዳም ኃጢአት ሲሠራ ፍጹም ያልሆነ ሰው ሆነ፤ በመሆኑም ዘሮቹ በሙሉ ፍጽምና የሌላቸው ሆኑ።

ሁላችንም የአዳም ዘሮች ነን። በመሆኑም ኃጢአተኛ የሆነና ውሎ አድሮ የሚሞት አካል ከአዳም ወርሰናል፤ እርግጥ ይህ የሆነው በራሳችን ምርጫ አይደለም። የወደቅንበትን አሳዛኝ ሁኔታ ጳውሎስ ጥሩ አድርጎ ገልጾታል። እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ለኃጢአት የተሸጥኩ ሥጋዊ ነኝ። እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ! እንዲህ ወዳለው ሞት ከሚመራኝ ሰውነት ማን ይታደገኛል?” ጳውሎስ ራሱ ላነሳው ጥያቄ መልስ ሲሰጥ “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሚታደገኝ አምላክ የተመሰገነ ይሁን!” ብሏል።—ሮም 7:14, 24, 25

ኢየሱስ እኛ ለዘላለም መኖር እንድንችል ሕይወቱን ሰጥቷል

“አብ ልጁን የዓለም አዳኝ አድርጎ [ልኮታል]።”1 ዮሐንስ 4:14

ይሖዋ አምላክ ኃጢአት ያስከተላቸውን ውጤቶች ለማስወገድና እኛን ከዘላለማዊ ሞት ፍርድ ነፃ ለማውጣት አንድ ዝግጅት አደረገ። እንዴት? ውድ ልጁን ከሰማይ በመላክ ልክ እንደ አዳም ፍጹም ሰው ሆኖ እንዲወለድ በማድረግ ነው። ይሁንና ከአዳም በተለየ መልኩ ኢየሱስ “ምንም ኃጢአት አልሠራም።” (1 ጴጥሮስ 2:22) ኢየሱስ ፍጹም ሰው ስለነበረ ሰዎች ከተፈረደባቸው የሞት ፍርድ ነፃ ነው፤ በመሆኑም ፍጹም ሰው ሆኖ ለዘላለም መኖር ይችል ነበር።

ይሁን እንጂ ይሖዋ፣ ኢየሱስ በጠላቶቹ እንዲገደል ፈቀደ። ከሦስት ቀናት በኋላ ይሖዋ ኢየሱስን ከሞት አስነሳው፤ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ኢየሱስ መንፈሳዊ አካል ሆኖ ወደ ሰማይ ተመለሰ። ከዚያም ኢየሱስ፣ አዳም ለራሱም ሆነ ለዘሮቹ ያሳጣውን ነገር መልሶ ለመግዛት ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱ ያለውን ዋጋ ለአምላክ ቤዛ አድርጎ አቀረበ። ይሖዋም ይህን መሥዋዕት የተቀበለ ሲሆን በኢየሱስ የሚያምኑ ሰዎች የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚችሉበት መንገድ ተከፈተላቸው።—ሮም 3:23, 24፤ 1 ዮሐንስ 2:2

ኢየሱስ ቤዛውን በመክፈል አዳም ያጣውን ነገር መልሶ ገዝቶታል። እኛ ለዘላለም መኖር እንችል ዘንድ እሱ የሞትን ጽዋ ተጎነጨ። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ መከራ ተቀብሏል፤ እሱ በአምላክ ጸጋ ለእያንዳንዱ ሰው ሲል ሞትን ቀምሷል’ ይላል።—ዕብራውያን 2:9

ይህ ዝግጅት ስለ ይሖዋ ብዙ የሚያሳውቀን ነገር አለ። ይሖዋ ካወጣቸው ላቅ ያሉ የፍትሕ መሥፈርቶች የተነሳ ፍጹም ያልሆኑ የሰው ልጆች ለራሳቸው ቤዛ ሊሆኑ አይችሉም ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ መሐሪና የፍቅር አምላክ በመሆኑ ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍለው ቢሆንም እንኳ ራሱ ያወጣውን መሥፈርት ለማሟላት ሲል የገዛ ልጁን ቤዛ አድርጎ ሰጥቷል።—ሮም 5:6-8

ኢየሱስ ከሞት ስለተነሳ ሌሎችም ከሞት ይነሳሉ

“ክርስቶስ በሞት ካንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሞት ተነስቷል። ሞት የመጣው በአንድ ሰው በኩል ስለሆነ የሙታን ትንሣኤም በአንድ ሰው በኩል ነው። ምክንያቱም ሁሉም በአዳም እንደሚሞቱ ልክ እንደዚሁም ሁሉም በክርስቶስ ሕያው ይሆናሉ።”1 ቆሮንቶስ 15:20-22

ኢየሱስ በሕይወት እንደነበረና እንደሞተ ምንም የሚያጠራጥር ነገር የለም፤ ሆኖም ከሞት እንደተነሳ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ? በጣም ጠንካራ የሆነው ማስረጃ፣ ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ በተለያዩ አጋጣሚዎችና ቦታዎች ለብዙ ሰዎች የተገለጠላቸው መሆኑ ነው። በአንድ ወቅት ከ500 ለሚበልጡ ሰዎች ታይቷል። ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ስለዚህ ጉዳይ የጠቀሰ ሲሆን ከእነዚህ የዓይን ምሥክሮች መካከል አንዳንዶቹ በወቅቱ በሕይወት እንደነበሩ እንዲሁም ስላዩትና ስለሰሙት ነገር መመሥከር እንደሚችሉ ገልጿል።—1 ቆሮንቶስ 15:3-8

በተጨማሪም ጳውሎስ፣ ክርስቶስ ከሞት ለሚነሱ ሰዎች “በኩራት” እንደሆነ ሲጽፍ ከጊዜ በኋላ ትንሣኤ የሚያገኙ ሌሎች ሰዎችም እንደሚኖሩ ማመልከቱ ነበር። ኢየሱስ ራሱም ‘በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ ድምፁን ሰምተው የሚወጡበት’ ጊዜ እንደሚመጣ ተናግሯል።—ዮሐንስ 5:28, 29

ለዘላለም ለመኖር በኢየሱስ ማመን አለብን

“አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።”—ዮሐንስ 3:16

በመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ ገጾች ላይ ሞት ስለመጣበትና ገነት ስለጠፋበት መንገድ እናነባለን። የመጨረሻዎቹ ገጾች ደግሞ ሞት ስለሚደመሰስበትና አምላክ ምድርን መልሶ ገነት ስለሚያደርግበት ጊዜ ይናገራሉ። በዚያን ጊዜ ሰዎች ለዘላለም አስደሳችና እርካታ ያለው ሕይወት መኖር ይችላሉ። ራእይ 21:4 “ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም” ይላል። ቁጥር 5 ደግሞ ይህ ተስፋ መፈጸሙ እንደማይቀር ሲያረጋግጥ “እነዚህ ቃላት እምነት የሚጣልባቸውና እውነት” እንደሆኑ ይናገራል። ይሖዋ ቃል የገባውን ነገር ሙሉ በሙሉ መፈጸም ይችላል።

ታዲያ አንተ “እነዚህ ቃላት እምነት የሚጣልባቸውና እውነት” እንደሆኑ ታምናለህ? ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መማርህን እንድትቀጥልና በእሱ ላይ እምነት እንዲኖርህ እናበረታታሃለን። እንዲህ ካደረግህ በይሖዋ ዘንድ ሞገስ ታገኛለህ። ይህም በአሁኑ ጊዜ የተትረፈረፈ በረከት እንድታገኝ ያስችልሃል፤ ወደፊት ምድር ገነት ስትሆን ደግሞ ሞት እንዲሁም ‘ሐዘን፣ ጩኸትና ሥቃይ በማይኖሩበት’ ዓለም ውስጥ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ያስገኝልሃል።