የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
የፍርድ ቀን ምንድን ነው?
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አምላክ መሳፍንትን በማስነሳት ሕዝቡን ከሚደርስባቸው ፍትሕ የጎደለው ድርጊት ያድን ነበር። (መሳፍንት 2:18) መጽሐፍ ቅዱስ የወደፊቱ የፍርድ ቀን የምድር ሁሉ ፈራጅ የሆነው ይሖዋ የሰው ዘርን ከፍትሕ መጓደል የሚያድንበት አስደሳች ጊዜ እንደሚሆን ይናገራል።—መዝሙር 96:12, 13ን እና ኢሳይያስ 26:9ን አንብብ።
አምላክ ፈራጅ አድርጎ የሾመው ኢየሱስ ሕያዋንም ሆኑ ሙታን ፍትሕ እንዲያገኙ ያደርጋል። (የሐዋርያት ሥራ 10:42፤ 17:31) ብዙ ሰዎች አምላክን ሳያውቁ ሞተዋል። በፍርድ ቀን ኢየሱስ እንዲህ ያሉትን ሰዎች ዳግመኛ ሕይወት እንዲያገኙ በማድረግ እውነተኛውን አምላክ ማወቅና መውደድ የሚችሉበት አጋጣሚ ይሰጣቸዋል።—የሐዋርያት ሥራ 24:15ን አንብብ።
የፍርድ ቀን ለአንድ ሺህ ዓመት የሚዘልቀው ለምንድን ነው?
ሙታን በሺው ዓመት ግዛት ውስጥ ይነሳሉ። (ራእይ 20:4, 12) የአምላክን መንገዶች አውቀው እሱን ለመታዘዝ ጊዜ ያስፈልጋቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ፍርድ የሚሰጣቸው ከትንሣኤ በኋላ በሚያደርጓቸው ነገሮች እንደሆነ ይነግረናል፤ ይህ ደግሞ ብዙዎች ካላቸው አመለካከት የተለየ ነው።—ሮም 6:7ን አንብብ።
መጽሐፍ ቅዱስ ሺው ዓመት ከመጀመሩ በፊት በድንገት የሚከሰት የፍርድ ቀን እንዳለም ይነግረናል። በዚህ መጽሔት መግቢያ ላይ ያሉት ርዕሶች ይህ ቀን መጨረሻው ተብሎም እንደሚጠራ ይናገራሉ። በዚያን ቀን ይሖዋ ፈሪሃ አምላክ የሌላቸውን ክፉ ሰዎች በሙሉ ያጠፋል። (2 ጴጥሮስ 3:7) በመሆኑም ለአምላክ ያለንን ፍቅር በተግባር ለማሳየት ጥረት እናድርግ።—2 ጴጥሮስ 3:9, 13ን አንብብ።