የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ጭንቀትን መቋቋም የሚቻለው እንዴት ነው?
ስለ ገንዘብ መጨነቅ
“አገራችን በከፍተኛ የዋጋ ግሽበት በተመታች ጊዜ ምግብ እጅግ ከመወደዱም በላይ እንደ ልብ አይገኝም ነበር” በማለት ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት የሆነው ፖል ተናግሯል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “አብዛኛውን ጊዜ ለሰዓታት ተሰልፈን ከቆምን በኋላ ወረፋችን ከመድረሱ በፊት ምግቡ ያልቃል። ሰዎች ከረሃቡ የተነሳ በጣም ከስተው እንዲሁም አንዳንዶች መንገድ ላይ ተዝለፍልፈው ወድቀው ይታዩ ነበር። መሠረታዊ የሆኑ ነገሮችን ለመግዛት በሚሊዮን አልፎ ተርፎም በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያስፈልግ ነበር። በመጨረሻም የአገሪቱ ገንዘብ ዋጋ አጣ። እኔም በባንክ ያጠራቀምኩትንም ሆነ ለኢንሹራንስና ለጡረታ ብዬ ያስቀመጥኩትን ገንዘብ አጣሁ።”
ፖል ቤተሰቡን በሕይወት ለማቆየት ‘የጥበብ’ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ተገነዘበ። (ምሳሌ 3:21) እንዲህ ብሏል፦ “የኤሌክትሪክ ሥራ ተቋራጭ ሆኜ እሠራ የነበረ ቢሆንም የማገኘውን ማንኛውንም ሥራ በዝቅተኛ ክፍያም እንኳ ለመሥራት ፈቃደኛ ነበርኩ። አንዳንዶች የሚከፍሉኝ ምግብ ወይም የቤት ዕቃ ነበር። ለምሳሌ አራት ሳሙና ቢሰጡኝ ሁለቱን እጠቀምበታለሁ፤ የቀረውን ደግሞ እሸጠዋለሁ። ከጊዜ በኋላ 40 የዶሮ ጫጩቶች አገኘሁ። እነሱ ሲያድጉ ሸጥኳቸውና 300 ተጨማሪ ጫጩቶች ገዛሁ። ከዚያም 50 ኪሎ ግራም የሚመዝን ሁለት ከረጢት የበቆሎ ዱቄት በ50 ዶሮዎች መለወጥ ቻልኩ። በዚህ ሁለት ከረጢት የበቆሎ ዱቄት ቤተሰቤንና ሌሎች ቤተሰቦችን ረዘም ላለ ጊዜ መመገብ ቻልኩ።”
በተጨማሪም ፖል ከሁሉ የተሻለው የጥበብ እርምጃ በአምላክ መታመን እንደሆነ ያውቅ ነበር። አምላክ የሚለንን የምናደርግ ከሆነ እሱ ይረዳናል። ኢየሱስ ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ማግኘትን በተመለከተ “አትጨነቁ፤ . . . አባታችሁ እነዚህ ነገሮች እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል” በማለት ተናግሯል።—ሉቃስ 12:29-31
የሚያሳዝነው ነገር የአምላክ ቀንደኛ ጠላት የሆነው ሰይጣን አብዛኞቹን ሰዎች፣ ሕይወታቸው በቁሳዊ ነገሮች ላይ ብቻ ያተኮረ እንዲሆን በማድረግ አታሏቸዋል። ሰዎች አሁን የሚያስፈልጓቸውንም ሆነ ገና ለገና ሊያስፈልጓቸው እንደሚችሉ አድርገው የሚያስቧቸውን ነገሮች ስለማግኘት ከልክ በላይ ይጨነቃሉ፤ አልፎ ተርፎም እምብዛም የማያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማግኘት ምሳሌ 22:7
ይዋትታሉ። ብዙዎች ዕዳ ውስጥ ይዘፈቁና “ተበዳሪም የአበዳሪው ባሪያ ነው” የሚለውን ሐቅ ከመከራ ይማራሉ።—አንዳንዶች ለችግር የሚዳርጋቸውን ውሳኔ ይወስናሉ። ፖል “በአካባቢያችን ያሉ ብዙ ሰዎች የተሻለ ነገር ፍለጋ ቤተሰባቸውንና ወዳጅ ዘመዳቸውን ጥለው ወደ ውጭ አገር ሄደዋል” በማለት ተናግሯል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “አንዳንዶቹ ከአገር የወጡት ሕጋዊ በሆነ መንገድ ስላልሆነ ሥራ ማግኘት አልቻሉም። ብዙውን ጊዜ የሚንቀሳቀሱት ከፖሊስ ተደብቀው ሲሆን የሚተኙትም በየጎዳናው ነው። አምላክ እንዲረዳቸው ወደ እሱ ዞር አላሉም። እኛ ግን ያጋጠመንን የኢኮኖሚ ችግር አምላክ በሚሰጠን እርዳታ በመታገዝ በቤተሰብ አንድ ላይ ሆነን ለመጋፈጥ ቆርጠን ነበር።”
የኢየሱስን ምክር መከተል
ፖል በመቀጠል እንዲህ ይላል፦ “ኢየሱስ ‘ስለ ነገ ፈጽሞ አትጨነቁ፤ ምክንያቱም ነገ የራሱ የሆኑ የሚያስጨንቁ ነገሮች አሉት። እያንዳንዱ ቀን የራሱ የሆነ በቂ ችግር አለው’ ብሏል። በመሆኑም በየዕለቱ ወደ አምላክ የምጸልየው ‘የዕለቱን ምግባችንን እንዲሰጠንና’ በሕይወት መቀጠል እንድንችል ብቻ ነው። ደግሞም ኢየሱስ በገባው ቃል መሠረት ይሖዋ ረድቶናል። እርግጥ ሁልጊዜ የምንፈልገውን እናገኝ ነበር ማለት አይደለም። አንድ ቀን፣ ምን እየተሸጠ እንዳለ ሳላውቅ ምግብ ለመግዛት ተሰለፍኩ። ወረፋዬ ሲደርስ የሚሸጠው ነገር እርጎ መሆኑን አወቅኩ። እኔ ደግሞ እርጎ አልወድም። ይሁንና እርጎም ቢሆን ምግብ ስለሆነ ያን ዕለት እሱን በልተን አደርን። በዚያ አስቸጋሪ ወቅት ቤተሰቤ ጾሙን አድሮ ስለማያውቅ አምላክን አመሰግናለሁ።” *
አምላክ “ፈጽሞ አልተውህም፤ በምንም ዓይነት አልጥልህም” በማለት ቃል ገብቷል።—ዕብራውያን 13:5
“እርግጥ አሁን የገንዘብ ችግራችን በተወሰነ መጠን ተቃሏል። ይሁን እንጂ ከሁሉ የተሻለው የጭንቀት ማርከሻ በአምላክ መታመን እንደሆነ ካሳለፍነው ተሞክሮ ተምረናል። ይሖዋ * ፈቃዱን ለማድረግ ጥረት እስካደረግን ድረስ ምንጊዜም ይረዳናል። ‘ይሖዋ ጥሩ መሆኑን ቅመሱ፤ እዩም፤ እሱን መጠጊያ የሚያደርግ ሰው ደስተኛ ነው’ የሚለው በመዝሙር 34:8 ላይ የሚገኘው ሐሳብ እውነት መሆኑን ተመልክተናል። በመሆኑም ዳግመኛ የኢኮኖሚ ችግር ቢያጋጥመን አንፈራም።
“ሰዎች በሕይወት ለመኖር የሚያስፈልጋቸው ሥራ ወይም ገንዘብ ሳይሆን ምግብ እንደሆነ አሁን በግልጽ ገብቶናል። ‘በምድር ላይ እህል ይትረፈረፋል’ የሚለው አምላክ የሰጠው ተስፋ የሚፈጸምበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን። እስከዚያው ድረስ ‘ምግብና ልብስ ካለን በእነዚህ ነገሮች ረክተን መኖር ይገባናል።’ የሚከተለው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ያበረታታናል፦ ‘አኗኗራችሁ ከገንዘብ ፍቅር ነፃ ይሁን፤ ባሏችሁ ነገሮች ረክታችሁ ኑሩ። እሱ “ፈጽሞ አልተውህም፤ በምንም ዓይነት አልጥልህም” ብሏልና። ስለዚህ በሙሉ ልብ “ይሖዋ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም”’ እንላለን።” *
ፖልና ቤተሰቡ እንዳደረጉት ‘ከአምላክ ጋር መሄድ’ ጠንካራ እምነት ይጠይቃል። (ዘፍጥረት 6:9) በአሁኑ ጊዜ ከባድ የኢኮኖሚ ችግር አጋጥሞን ከሆነ አሊያም ወደፊት ካጋጠመን፣ ፖል በአምላክ በመታመንና ጥበብ የታከለበት እርምጃ በመውሰድ ረገድ ከተወው ምሳሌ ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት እንችላለን።
ይሁን እንጂ እያስጨነቀን ያለው የቤተሰብ ችግር ቢሆንስ?
^ አን.9 ማቴዎስ 6:11, 34ን ተመልከት።
^ አን.10 መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የአምላክ የግል ስም ይሖዋ ነው።
^ አን.11 መዝሙር 72:16ን፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:8ን እና ዕብራውያን 13:5, 6ን ተመልከት።