በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ዮሴፍ፣ ፈርዖን ፊት ከመቅረቡ በፊት የተላጨው ለምንድን ነው?

በአንድ ጥንታዊ የግብፃውያን ግድግዳ ላይ አንድ ፀጉር አስተካካይ ፀጉር ሲያስተካክል የሚያሳይ ሥዕል

የዘፍጥረት ዘገባ እንደሚያሳየው ፈርዖን ያስጨነቁትን ሕልሞች እንዲፈታለት በእስር ላይ የነበረው ዕብራዊው ዮሴፍ በአስቸኳይ እሱ ፊት እንዲቀርብ ትእዛዝ አስተላለፈ። በዚህ ጊዜ ዮሴፍ እስር ቤት ከገባ በርከት ያሉ ዓመታት ተቆጥረው ነበር። የፈርዖን ትእዛዝ አስቸኳይ ቢሆንም ዮሴፍ ጊዜ ወስዶ ፀጉሩን ተላጭቷል። (ዘፍጥረት 39:20-23፤ 41:1, 14) የታሪኩ ጸሐፊ ብዙም አስፈላጊ የማይመስለውን ይህን ጉዳይ መጥቀሱ የግብፃውያንን ባሕል በደንብ እንደሚያውቅ ያሳያል።

በጥንት ዘመን ዕብራውያንን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ብሔራት ጢም የማሳደግ ልማድ ነበራቸው። በሌላ በኩል ግን “ከምሥራቅ ሕዝቦች መካከል ጢማቸውን የማያሳድጉት የጥንቶቹ ግብፃውያን ብቻ ነበሩ” በማለት በማክሊንቶክና በስትሮንግ የተዘጋጀው ሳይክሎፒዲያ ኦቭ ቢብሊካል፣ ቲኦሎጂካል ኤንድ ኤክለዚያስቲካል ሊትሬቸር ገልጿል።

ለመሆኑ የሚላጩት ጢማቸውን ብቻ ነበር? ቢብሊካል አርኪኦሎጂ ሪቪው የተባለው መጽሔት እንደገለጸው ከሆነ አንድ ሰው ወደ ቤተ መቅደሱ ሊገባ ሲል እንደሚያደርገው ሁሉ ፈርዖን ፊት ከመቅረቡም በፊት የግብፃውያን ባሕል የሚጠይቀውን ልማድ እንዲያሟላ ይጠበቅበት ነበር። በዚህ ምክንያት ዮሴፍ በራሱም ሆነ በሰውነቱ ላይ ያለውን ፀጉር በሙሉ መላጨት ነበረበት።

የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የጢሞቴዎስ አባት ግሪካዊ እንደሆነ ይናገራል። እንዲህ ሲባል ግን የግሪክ አገር ሰው ነበር ማለት ነው?

እንደዚያ ማለት ላይሆን ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት በጻፋቸው መልእክቶች ላይ አይሁዳውያንን ከግሪካውያን ወይም ከሄለናውያን ጋር እያነጻጸረ ተናግሯል፤ ግሪካዊ የሚለውን ቃል አይሁዳዊ ያልሆኑ ሰዎችን በአጠቃላይ ለማመልከት የተጠቀመበት ይመስላል። (ሮም 1:16፤ 10:12) ለዚህ አንዱ ምክንያት፣ ጳውሎስ በሰበከበት ቦታ ሁሉ የግሪክ ቋንቋና ባሕል እጅግ ተስፋፍቶ የነበረ መሆኑ ነው።

በጥንት ጊዜ ግሪካዊ የሚባለው ምን ዓይነት ሰው ነበር? ለምሳሌ፣ በአራተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የኖረውና የላቀ የንግግር ችሎታ የነበረው የአቴንሱ አይሶቅራጥስ በመላው ዓለም የግሪክ ባሕል መስፋፋቱን በኩራት ተናግሯል። በመሆኑም “ግሪካውያን የሚባሉት በትውልድ ግሪካውያን የሆኑት ብቻ ሳይሆኑ የእኛን ትምህርት የቀሰሙ ሰዎች ጭምር ናቸው” በማለት ገልጿል። ስለዚህ አይሁዳዊ ያልነበረው የጢሞቴዎስ አባት እንዲሁም ጳውሎስ ግሪካውያን እንደሆኑ የጠቀሳቸው ሌሎች ሰዎች ግሪካዊ የሆኑት በትውልድ ሳይሆን ባሕሉን በመቀበላቸው ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም እንዲህ ብሎ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም።—የሐዋርያት ሥራ 16:1