በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .

የገና በዓል ልማዶችን መከተል ስህተት አለው?

የገና በዓል ልማዶችን መከተል ስህተት አለው?

ገና የኢየሱስ ልደት የሚከበርበት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ክርስቲያናዊ በዓል እንደሆነ ሲነገር ቆይቷል። ሆኖም በዚህ በዓል ላይ የሚከናወኑት በርካታ ልማዶች ከኢየሱስ ልደት ጋር እንዴት ሊያያዙ እንደቻሉ ጥያቄ ይፈጠርብን ይሆናል።

በመጀመሪያ ደረጃ ስለ ገና አባት የሚነገረው አፈ ታሪክ አለ። በአሁኑ ጊዜ የምናውቀው ዘናጭ፣ ነጭ ጢምና የቀላ ጉንጭ ያለው እንዲሁም ቀይ ሙሉ ልብስ የለበሰው የገና አባት በ1931 ለአንድ የሰሜን አሜሪካ የለስላሳ መጠጥ ፋብሪካ የተዘጋጀ የተዋጣለት ማስታወቂያ እንደነበር ይታወሳል። በ1950ዎቹ አንዳንድ ብራዚላውያን የገና አባትን በአገራቸው በሚታወቀው ግራንድፓ ኢንዲያን ተብሎ በሚጠራው አፈ ታሪክ የወለደው ሰው ለመተካት ሞክረዋል። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? የገና አባት፣ ከግራንድፓ ኢንዲያን ብቻ ሳይሆን “ከሕፃኑ ከኢየሱስ የበለጠ ገናና በመሆን ታኅሣሥ 25 ላይ የሚከበረው በዓል መለያ ሆነ” በማለት ፕሮፌሰር ካርሎስ ፋንቲናቲ ተናግረዋል። ይሁንና ከገና በዓል ጋር በተያያዘ እንደ ስህተት የሚቆጠሩት እንደ ገና አባት ያሉ አፈ ታሪኮች ብቻ ናቸው? መልሱን ለማግኘት እስቲ የጥንቱን ክርስትና እንመልከት።

ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንዲህ ብሏል፦ “ክርስትና ከተቋቋመ በኋላ ባሉት ሁለት መቶ ዓመታት የሰማዕታትን ሌላው ቀርቶ የኢየሱስን ልደት ማክበር ፈጽሞ ተቀባይነት አልነበረውም።” ለምን? ክርስቲያኖች ልደት ማክበር የአረማውያን ልማድ እንደሆነና ሙሉ በሙሉ ሊርቁት የሚገባ ነገር መሆኑን ተገንዝበው ስለነበር ነው። እንዲያውም ኢየሱስ የተወለደበት ቀን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጠቀሰም።

የጥንት ክርስቲያኖች ልደት ማክበርን ይቃወሙ የነበረ ቢሆንም በአራተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የገናን በዓል አቋቋመች። ቤተ ክርስቲያኒቷ ከተጋረጡባት ችግሮች መካከል ዋነኛውን በማስወገድ ኃይሏን ለማጠናከር ፈለገች፤ ይህን ለማድረግ አረማዊ የሆኑት የሮማውያን ሃይማኖቶችና የክረምቱን ማብቃት አስመልክቶ የሚያከብሯቸውን በዓላት ገናናነት ማስወገድ ነበረባት። ክሪስማስ ኢን አሜሪካ የተሰኘው በፔኒ ሬስታድ የተዘጋጀው ጽሑፍ እንደገለጸው በየዓመቱ ከታኅሣሥ 17 እስከ ጥር 1 ድረስ “አብዛኞቹ ሮማውያን ድግስ ይደግሱ፣ ይጫወቱ፣ ይፈነጥዙ፣ ሰልፍ ይወጡ እንዲሁም ለአማልክቶቻቸው አክብሮት ለመስጠት የተለያዩ ድርጊቶችን ይፈጽሙ ነበር።” እንዲሁም ሮማውያን ታኅሣሥ 25 ላይ የማትበገረዋን ፀሐይ ልደት ያከብሩ ነበር። በመሆኑም ቤተ ክርስቲያኒቱ በዚያን ቀን የገናን በዓል በማቋቋም በርካታ ሮማውያን የፀሐይን ልደት ከማክበር ይልቅ የኢየሱስን ልደት እንዲያከብሩ ማግባባት ችላለች። ሳንታ ክላውስኤ ባዮግራፊ የተባለው በጌሪ ቦውለር የተዘጋጀ ጽሑፍ እንደገለጸው ሮማውያን “በዚህ በክረምት ወራት አጋማሽ የሚዘጋጁት በዓላት ወጥመድ ሆነውባቸው ነበር።” እንደ እውነቱ ከሆነ “አዲሱን በዓል በድሮው መንገድ ማክበራቸውን ቀጥለው ነበር።”

በግልጽ መመልከት እንደሚቻለው ከገና በዓል ጋር በተያያዘ ያለው ዋና ችግር በዓሉ ከጅምሩ አንስቶ በተሳሳቱ ልማዶች ላይ የተመሠረተ መሆኑ ነው። ስቲቨን ኒሳንቦም በጻፈው ዘ ባትል ፎር ክሪስማስ በተባለው መጽሐፍ ላይ ገናን “የክርስትናን ጭምብል ያጠለቀ አረማዊ በዓል ነው” በማለት ገልጾታል። እንግዲያው ገና አምላክንም ሆነ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን የማያስከብር በዓል ነው። ታዲያ ይህ አቅልለን ልንመለከተው የሚገባ ጉዳይ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ኅብረት አለው? ወይስ ብርሃን ከጨለማ ጋር ምን ያገናኘዋል?” በማለት ይጠይቃል። (2 ቆሮንቶስ 6:14) አንድ ዛፍ ተጣሞ ካደገ ሊቃና እንደማይችል ሁሉ የገና በዓልም ከመሠረቱ የተጣመመ ስለሆነ “ሊቃና አይችልም።”—መክብብ 1:15