በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብን አስደሳች ማድረግ

መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ መጀመር የምችለው እንዴት ነው

መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ መጀመር የምችለው እንዴት ነው

መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ አስደሳች እንዲሆንልህና ከንባብህ ይበልጥ ጥቅም ማግኘት እንድትችል ምን ሊረዳህ ይችላል? ብዙ ሰዎች ውጤታማ ሆነው ያገኟቸውን አምስት ነጥቦች ተመልከት።

ለማንበብ አመቺ የሆነ ቦታ ምረጥ። ጸጥ ያለ ቦታና ጊዜ ለማግኘት ሞክር። በምታነበው ነገር ላይ ትኩረት ማድረግ እንድትችል ሐሳብ የሚከፋፍሉ ነገሮችን አስወግድ። በቂ ብርሃንና ንጹሕ አየር ያለበት ቦታ ሆነህ ማንበብህ ከንባብህ የተሻለ ጥቅም እንድታገኝ ሊረዳህ ይችላል።

አእምሮህን ክፍት አድርገህ አንብብ። መጽሐፍ ቅዱስ በሰማይ ካለው አባታችን ያገኘነው ስጦታ ነው፤ አንድ ልጅ አፍቃሪ ከሆነ ወላጁ ለመማር እንደሚጓጓ ሁሉ አንተም እንዲህ ዓይነት ዝንባሌ ይዘህ ማንበብህ ከንባብህ የተሻለ ጥቅም እንድታገኝ ይረዳሃል። አምላክ እንዲያስተምርህ ከፈለግክ በቅድሚያ መጽሐፍ ቅዱስን በተመለከተ ያሉህን አሉታዊ አመለካከቶች ከአእምሮህ ማውጣት አለብህ።—መዝሙር 25:4

ማንበብ ከመጀመርህ በፊት ጸልይ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የአምላክ ሐሳብ ነው፤ በመሆኑም ሐሳቡን መረዳት እንድንችል የአምላክ እርዳታ የሚያስፈልገን መሆኑ አያስገርምም። አምላክ ‘ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንደሚሰጣቸው’ ቃል ገብቷል። (ሉቃስ 11:13) መንፈስ ቅዱስ የአምላክን አስተሳሰብ እንድትረዳ ያግዝሃል። በጊዜ ሂደት፣ ‘የአምላክን ጥልቅ ነገሮችም’ ሳይቀር መረዳት እንድትችል አእምሮህን ይከፍትልሃል።—1 ቆሮንቶስ 2:10

የምታነበውን ነገር ለመረዳት ሞክር። የተወሰኑ ገጾችን ለመሸፈን ብቻ ብለህ አታንብብ። የምታነበውን ነገር ለማስተዋል ጥረት አድርግ። ራስህን እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን ጠይቅ፦ ‘በዘገባው ላይ የተጠቀሰው ግለሰብ ምን ጥሩ ባሕርያት አሉት? እነዚህን ባሕርያት በሕይወቴ ውስጥ ማንጸባረቅ የምችለው እንዴት ነው?’

ግብ አውጣ። መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ ለራስህ አንድ ጠቃሚ ትምህርት ለማግኘት ግብ አድርግ። ለምሳሌ ስለ አምላክ ይበልጥ ለማወቅ ግብ አድርገህ ልታነብ ትችላለህ። አሊያም ደግሞ የተሻለ ሰው ወይም ባል መሆን የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ለመማር ግብ ማውጣት ትችላለህ። ከዚያም ያወጣኸው ግብ ላይ ለመድረስ የሚረዱህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ምረጥ። *

እነዚህ አምስት ነጥቦች መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ እንድትጀምር ይረዱሃል። ሆኖም ንባብህ ይበልጥ አስደሳች እንዲሆን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? የሚቀጥለው ርዕስ በዚህ ረገድ የሚረዱህን አንዳንድ ሐሳቦች ይዟል።

^ አን.8 ያወጣኸው ግብ ላይ ለመድረስ የሚረዳህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የቱ እንደሆነ ካላወቅክ የይሖዋ ምሥክሮች ሊረዱህ ፈቃደኞች ናቸው።