የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?
ኢንተርኔት በሌለባቸው ቦታዎችም የሚደርሰው የJW ሳተላይት ቻናል
ሚያዝያ 1, 2021
በየወሩ JW ብሮድካስቲንግ ላይ የሚወጡትን መንፈሳዊ ፕሮግራሞችና ቪዲዮዎች በጉጉት እንጠብቃለን። ይሁንና በአፍሪካ ያሉ ብዙ ወንድሞቻችን በኢንተርኔት አማካኝነት እነዚህን ፕሮግራሞች ማግኘት አይችሉም። ለምን?
አፍሪካ ውስጥ በብዙ አካባቢዎች ኢንተርኔት እንደ ልብ አይገኝም። ኢንተርኔት ባለባቸው አካባቢዎችም እንኳ ብዙውን ጊዜ አዝጋሚ ወይም በጣም ውድ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በማዳጋስካር የሚኖር አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች ኢንተርኔት ካፌ ገብቶ አንድ የJW ብሮድካስቲንግ ወርሃዊ ፕሮግራም አውርዶ ነበር። ከዚያም 16 ዶላር እንዲከፍል ተጠየቀ፤ ይህ ገንዘብ አንዳንድ ሰዎች በሳምንት ከሚያገኙት ገቢ ይበልጣል! a
እነዚህ እንቅፋቶች ቢኖሩም፣ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ የሚኖሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ኢንተርኔት መጠቀም ሳያስፈልጋቸው JW ብሮድካስቲንግን መመልከት ችለዋል። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?
ከ2017 አንስቶ JW ብሮድካስቲንግ ከሰሃራ በታች ላሉ የአፍሪካ አገሮች በሳተላይት የቴሌቪዥን ጣቢያ አማካኝነት እንዲተላለፍ ተደረገ። ይህ ቻናል ክፍያ የለውም፤ በ16 ቋንቋዎች፣ ሳምንቱን በሙሉ በቀን 24 ሰዓት ይተላለፋል።
የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ መንገድ ፕሮግራማቸውን በሳተላይት አማካኝነት ለማስተላለፍ ለአገልግሎቱ የሚያስፈልገውን ክፍያ መፈጸም አለባቸው። የምንጠቀምበት ሳተላይት ከሰሃራ በታች ያሉ 35 ገደማ የአፍሪካ አገሮችን ይሸፍናል። ለአገልግሎቱ የምንከፍለው ገንዘብ በወር ከ12,000 ዶላር በላይ ነው። አልፎ አልፎ ደግሞ ለየት ያሉ ዝግጅቶችን በሌላ ቻናል በቀጥታ ለማስተላለፍ ተጨማሪ ገንዘብ እንከፍላለን። በዚህ ዝግጅት አማካኝነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የክልል ስብሰባዎችን ወይም ከቅርንጫፍ ቢሮ ጉብኝት ጋር ተያይዘው የሚደረጉ ልዩ ፕሮግራሞችን መከታተል ችለዋል።
የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎችን ጨምሮ ብዙዎች፣ ቤታቸው ሆነው JW ቻናልን በቴሌቪዥናቸው ይመለከታሉ። ይሁንና ለሳተላይት ቻናሉ የሚያስፈልገውን መሣሪያ ለመግዛት አቅማቸው የማይፈቅድላቸው ብዙ ወንድሞቻችን አሉ። እነዚህን ወንድሞች ለመርዳት ሲባል ከ3,670 የሚበልጡ የስብሰባ አዳራሾች ሳተላይት ዲሽ እና ሪሲቨር እንዲሟላላቸው ተደርጓል፤ ይህም ወንድሞችና እህቶች እዚያ ሄደው JW ብሮድካስቲንግን እንዲመለከቱ አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። አዳራሹ ቴሌቪዥን ወይም ፕሮጀክተር ካለው፣ የመሣሪያው ግዢ (የዕቃ ማጓጓዣውን ጨምሮ) ወጪው 70 ዶላር ገደማ ይደርሳል። ይህ ካልሆነ ግን ወጪው እስከ 530 ዶላር ሊደርስ ይችላል።
ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ለዚህ ቻናል ከፍተኛ አድናቆት አላቸው። በካሜሩን የሚኖር አንድ ሽማግሌ “ለቤተሰባችን፣ ጭልጥ ባለ በረሃ መና እንደ ማግኘት ሆኖልናል” ብሏል። በናይጄሪያ የሚኖር ኦዴቦዲ የተባለ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “በሳምንት ሦስቴ በቤተሰብ አንድ ላይ ሆነን ይህን ቻናል እንመለከታለን። ልጆቻችን እንዲህ የምናደርግበትን ጊዜ ሁሌም በጉጉት ነው የሚጠብቁት። እንዲያውም በሌሎች ጊዜያትም እንኳ ቻናሉን ወደ JW ብሮድካስቲንግ እንድንቀይርላቸው ይጠይቁናል።” በናይጄሪያ የምትኖረው ሮዝ የተባለች እህትም እንዲህ ብላለች፦ “ዜና የማየት ሱስ ነበረብኝ፤ አሁን ግን ደስ የሚለው JW ቻናል እሱን ተክቶልኛል። ዜና ሳይ የሚያበሳጨኝ ነገር አይጠፋም፤ ስለዚህ ደሜ ከፍ ይል ነበር። JW ብሮድካስቲንግን መመልከት ግን የሚያበረታታና መንፈስን የሚያድስ ነው! በጣም የምወደው ቻናል ነው። ውድ የሆነ የይሖዋ ስጦታ ነው።”
በሞዛምቢክ ያለ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሪፖርት እንዳደረገው፣ በወረዳው ውስጥ ያሉ የስብሰባ አዳራሾች የሳተላይት ቻናሉን ለማየት የሚያስፈልገው መሣሪያ ተሟልቶላቸዋል። በእነዚህ ጉባኤዎች ውስጥ ያሉ ወንድሞች፣ በሳተላይት አማካኝነት JW ብሮድካስቲንግ ለማየት ስብሰባ ከሚደረግበት ሰዓት አንድ ሰዓት ወይም ከዚያ በላይ ቀድመው ወደ አዳራሹ ይመጣሉ።
በ2019 ጆሃንስበርግ፣ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ በተደረገበት ወቅት የበላይ አካል አባል የሰጠውን ጨምሮ ዋና ዋናዎቹን ንግግሮች በዚህ ቻናል አማካኝነት ወደ ዘጠኝ ቦታዎች በቀጥታ ማስተላለፍ ተችሏል። በደቡብ አፍሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ የአካባቢ ብሮድካስቲንግ ዲፓርትመንት ውስጥ የሚሠራው ስፑሜሌሌ እንዲህ ብሏል፦ “ከዚህ በፊት ንግግሮችን የምናስተላልፈው በኢንተርኔት ነበር። ይህ ግን አስተማማኝ ኢንተርኔት የሚጠይቅ ከመሆኑም ሌላ ወጪ ያስወጣል። JW ሳተላይት ቻናል ከወጪም ሆነ ከአስተማማኝነት አንጻር የተሻለ አማራጭ ሆኖ ተገኝቷል።”
እናንተ ለዓለም አቀፉ ሥራ በልግስና በምታደርጉት መዋጮ የተነሳ፣ በአፍሪካ ያሉ ብዙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን JW ብሮድካስቲንግን በሳተላይት አማካኝነት ማየት ችለዋል። donate.mt1130.com ላይ ያሉትን የተለያዩ አማራጮች በመጠቀም የምታደርጉትን መዋጮ በእጅጉ እናደንቃለን።
a በዚህ ርዕስ ውስጥ ሁሉም ገንዘቦች የተጠቀሱት በአሜሪካ ዶላር ነው።