መጥምቁ ዮሐንስ በእርግጥ በሕይወት የኖረ ሰው ነው?
የወንጌል ዘገባዎች ስለ አምላክ መንግሥት በይሁዳ የሚሰብክ መጥምቁ ዮሐንስ የተባለ ሰው እንደነበር ይገልጻሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መጥምቁ ዮሐንስ የሚናገረው ሐሳብ ትክክለኛ ነው? የሚከተሉትን ነጥቦች ተመልከት፦
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “መጥምቁ ዮሐንስ በይሁዳ ምድረ በዳ እየሰበከ መጣ፤ ‘መንግሥተ ሰማያት ስለቀረበ ንስሐ ግቡ’ ይል ነበር።” (ማቴዎስ 3:1, 2) የታሪክ ምሁራን የዚህን ሐሳብ ትክክለኝነት ይመሠክራሉ? በሚገባ።
ፍላቪየስ ጆሴፈስ የተባለው የመጀመሪያው መቶ ዘመን የታሪክ ምሁር ‘መጥምቁ ዮሐንስ የተባለ ሰው አይሁዳውያን የጽድቅ ሥራዎችን እንዲሠሩ፣ አምላክን እንዲያመልኩና እንዲጠመቁ ያስተምር’ እንደነበር ገልጿል።—ጁዊሽ አንቲኩዊቲስ፣ ጥራዝ 18
መጽሐፍ ቅዱስ ዮሐንስ የገሊላና የፔሪያ አውራጃ ገዢ የሆነውን ሄሮድስ አንቲጳስን እንደገሠጸው ይናገራል። ሄሮድስ የአይሁድ እምነት ተከታይ እንደሆነና የሙሴን ሕግ እንደሚያከብር ይናገር ነበር። ሄሮድስ የወንድሙ ሚስት የሆነችውን ሄሮድያዳን በማግባቱ ምክንያት ዮሐንስ ገሥጾት ነበር። (ማርቆስ 6:18) ይህ ሐሳብም ከታሪክ አንጻር ተቀባይነት አለው።
የታሪክ ምሁር የሆነው ጆሴፈስ፣ አንቲጳስ ‘ሄሮድያዳን እንደወደዳትና እንድታገባው ዓይን አውጥቶ እንደጠየቃት’ ገልጿል። ሄሮድያዳም ጥያቄውን በመቀበል ባሏን ትታ አንቲጳስን አገባችው።
መጽሐፍ ቅዱስ “በኢየሩሳሌምና በመላዋ ይሁዳ እንዲሁም በዮርዳኖስ ዙሪያ ባለው ክልል ሁሉ የሚኖሩ ሰዎች ወደ [ዮሐንስ] ይመጡ ነበር፤ ደግሞም . . . ዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ በእሱ ይጠመቁ ነበር” ይላል።—ማቴዎስ 3:5, 6
ጆሴፈስም ይህን ሐሳብ ደግፏል፤ ‘ብዙ ሰዎች ወደ ዮሐንስ ይመጡ እንዲሁም በስብከቱ በእጅጉ ይበረታቱ እንደነበር’ ጽፏል።
በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የመጀመሪያው መቶ ዘመን የታሪክ ምሁር የሆነው ጆሴፈስ መጥምቁ ዮሐንስ በሕይወት እንደኖረ እርግጠኛ ነበር። እኛም እርግጠኞች መሆን እንችላለን።