የመጽሐፍ ቅዱስን ዘገባ ትክክለኛነት የሚያሳይ በግብፅ የሚገኝ ጥንታዊ የተቀረጸ ምስል
ይህ ግድግዳ የሚገኘው በካርናክ ውስጥ ባለው አሙን ለተባለው የግብፃውያን አምላክ የተሠራ ጥንታዊ ቤተ መቅደስ መግቢያ አካባቢ ነው፤ ግድግዳው ስምንት ሜትር ከፍታ ያለው ሲሆን የግብፅ ሥዕላዊ ጽሑፍ ተቀርጾበታል። ምሁራን እንደሚናገሩት ከሆነ የተቀረጸው ምስል ፈርዖን ሺሻቅ ይሁዳንና ሰሜናዊውን የእስራኤል መንግሥት ጨምሮ ከግብፅ በስተ ሰሜን ምሥራቅ በሚገኙ አገሮች ላይ ያደረገውን ወረራ የሚያሳይ ነው።
ምስሉ አሙን ለሺሻቅ ወይም ለሼሾንቅ a ከ150 በላይ እስረኞችን ሲሰጠው ያሳያል። እያንዳንዱ እስረኛ ሺሻቅ ድል ያደረገውን ከተማ ወይም ሕዝብ ይወክላል። የከተሞቹ ስም በእያንዳንዱ እስረኛ ምስል ላይ ተቀርጾ ይገኛል። ብዙዎቹ ስሞች አሁንም ይነበባሉ፤ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡ ሰዎች አንዳንዶቹን ከተሞች ያውቋቸዋል። ከእነዚህ መካከል ቤትሼን፣ ገባኦን፣ መጊዶ እና ሹነም ይገኙበታል።
ሺሻቅ በይሁዳ ላይ ያደረገው ወረራ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሷል። (1 ነገሥት 14:25, 26) እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ የሺሻቅን ወረራ በተመለከተ ዝርዝር መረጃ ይሰጠናል። ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “ንጉሥ ሮብዓም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የግብፅ ንጉሥ ሺሻቅ በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ። እሱም 1,200 ሠረገሎችና 60,000 ፈረሰኞች አስከትሎ ነበር፤ ከእሱም ጋር ከግብፅ የመጡት . . . ወታደሮች ስፍር ቁጥር አልነበራቸውም። እሱም የይሁዳን የተመሸጉ ከተሞች ያዘ፤ በመጨረሻም ኢየሩሳሌም ደረሰ።”—2 ዜና መዋዕል 12:2-4
ሺሻቅ በእስራኤል ምድር ላይ ወረራ ማድረጉን የሚያረጋግጠው አርኪኦሎጂያዊ ማስረጃ በካርናክ የሚገኘው ምስል ብቻ አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተጠቀሰው የመጊዶ ከተማ ውስጥ የተገኘ የሐውልት ቁራጭም “ሼሾንቅ” የሚለውን ስም ይዟል።
መጽሐፍ ቅዱስ ሺሻቅ በይሁዳ ላይ ያደረገውን ወረራ በትክክል መዘገቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ያላቸውን ሐቀኝነት የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ነው። ጸሐፊዎቹ በራሳቸው ብሔር ላይ ስለተደረጉት ወረራዎች እና ስለደረሰባቸው ሽንፈት በሐቀኝነት ዘግበዋል። ብዙዎቹ ጥንታዊ ታሪክ ጸሐፊዎች እንዲህ ያለ ሐቀኝነት አላሳዩም።
a “ሺሻቅ” የሚለው አጻጻፍ የዕብራይስጡን አነባበብ የተከተለ ነው።