ሽብርተኝነት የሚወገድበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?
የሽብር ጥቃት በሚደርስበት ወቅት እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎች ይፈጠሩብህ ይሆናል፦ ‘አምላክ ይህ ጉዳይ ያሳስበዋል? እንዲህ ያሉት ነገሮች የሚደርሱት ለምንድን ነው? ሽብርተኝነት a የሚወገድበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? የሚሰማኝን ፍርሃት መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?’ መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ይሰጣል።
አምላክ ስለ ሽብርተኝነት ምን ይሰማዋል?
አምላክ ዓመፅንና ሽብርተኝነትን ይጠላል። (መዝሙር 11:5፤ ምሳሌ 6:16, 17) የአምላክ ወኪል የሆነው ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱ የዓመፅ ድርጊት በፈጸሙበት ወቅት ተግሣጽ ሰጥቷቸዋል። (ማቴዎስ 26:50-52) አንዳንዶች የዓመፅ ድርጊት የሚፈጽሙት በአምላክ ስም እንደሆነ ቢናገሩም አምላክ እንዲህ ያለውን ድርጊት እንዲፈጽሙ አይፈልግም። እንዲያውም ጸሎታቸውን እንኳ አይመልስም።—ኢሳይያስ 1:15
አምላክ የሽብር ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሰዎችን ጨምሮ መከራ ለሚደርስባቸው ሰዎች በሙሉ ያስባል። (መዝሙር 31:7፤ 1 ጴጥሮስ 5:7) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ዓመፅን ለማጥፋት እርምጃ እንደሚወስድ ይገልጻል።—ኢሳይያስ 60:18
የሽብርተኝነት ዋነኛ መንስኤ
ሽብርተኝነት የሚወገድበት ጊዜ
አምላክ ፍርሃትንና ዓመፅን እንደሚያስወግድ እንዲሁም በመላው ምድር ላይ ሰላም እንደሚያሰፍን ቃል ገብቷል።—ኢሳይያስ 32:18፤ ሚክያስ 4:3, 4
አምላክ የሽብርተኝነትን ዋነኛ መንስኤ ያስወግዳል። አሁን ያሉትን መንግሥታት አስወግዶ እሱ ባቋቋመው ዓለም አቀፋዊ መንግሥት ይተካቸዋል። የዚህ መንግሥት ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉንም ሰው በፍትሕ ይይዛል፤ እንዲሁም ጭቆናንና ግፍን ያስወግዳል። (መዝሙር 72:2, 14) በዚያ ወቅት ማንም ሰው ሽብርተኛ የሚሆንበት ምክንያት አይኖርም። ሁሉም ሰዎች “በብዙ [ሰላም] እጅግ ደስ ይላቸዋል።”—መዝሙር 37:10, 11
አምላክ ሽብርተኝነት ያስከተላቸውን ጉዳቶች በሙሉ ያስተካክላል። አምላክ፣ በሽብር ጥቃቶች ምክንያት አካላዊ ጉዳትም ሆነ የስሜት ቀውስ የደረሰባቸውን ሰዎች ይፈውሳል። (ኢሳይያስ 65:17፤ ራእይ 21:3, 4) ሙታንን እንኳ በማስነሳት ሰላም በሰፈነበት ምድር ላይ እንዲኖሩ እንደሚያደርጋቸው ቃል ገብቷል።—ዮሐንስ 5:28, 29
መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ እርምጃ የሚወስደው በቅርቡ እንደሆነ የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች ይዟል። ይሁንና ‘አምላክ ሽብርተኝነትን እስካሁን ያላስወገደው ለምንድን ነው?’ የሚል ጥያቄ ይፈጠርብህ ይሆናል። የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው? የሚለውን ቪዲዮ እንድትመለከት እንጋብዝሃለን።
a አብዛኛውን ጊዜ “ሽብርተኝነት” የሚለው ቃል፣ በሰዎች ላይ ሽብር ለመንዛትና ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊ ወይም ማኅበራዊ ዓላማ ለማራመድ ሲባል በተለይ በንጹሓን ዜጎች ላይ የዓመፅ ጥቃት መሰንዘርን ወይም ለመሰንዘር ማስፈራራትን ያመለክታል። ይሁንና በሽብርተኝነት መፈረጅ ያለባቸውን ድርጊቶች በተመለከተ ሰዎች የተለያየ አመለካከት ሊኖራቸው ይችላል።