በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ስለ ንጽሕና የሰጣቸው ሕጎች ከዘመኑ የቀደሙ ናቸው

አምላክ ስለ ንጽሕና የሰጣቸው ሕጎች ከዘመኑ የቀደሙ ናቸው

 የዛሬ 3,500 ዓመት ገደማ የእስራኤል ብሔር ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባቱ በፊት አምላክ ሕዝቡን በግብፅ ሳሉ ያውቋቸው ከነበሩ “አሰቃቂ በሽታዎች” እንደሚጠብቃቸው ነግሯቸው ነበር። (ዘዳግም 7:15) ይህን ያደረገበት አንዱ መንገድ በሽታን ከመከላከልና ከንጽሕና ጋር የተያያዙ ዝርዝር ሕጎችን በመስጠት ነው። አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።

  •   ለእስራኤል ብሔር የተሰጠው ሕግ ሕዝቡ ገላቸውን እንዲታጠቡና ልብሳቸውን እንዲያጥቡ ያዝዝ ነበር።—ዘሌዋውያን 15:4-27

  •   ከመጸዳዳት ጋር በተያያዘ አምላክ የሚከተለውን መመሪያ ሰጥቷቸው ነበር፦ “ለመጸዳጃ የሚሆን ቦታ ከሰፈሩ ውጭ አዘጋጅ፤ አንተም መሄድ ያለብህ ወደዚያ ነው። ከመሣሪያዎችህም ጋር መቆፈሪያ ያዝ። ውጭ በምትጸዳዳበትም ጊዜ በመቆፈሪያው ጉድጓድ ቆፍር፤ ከዚያም በዓይነ ምድርህ ላይ አፈሩን መልስበት።”—ዘዳግም 23:12, 13

  •   ተላላፊ በሽታ እንዳለባቸው የተጠረጠሩ ሰዎች ለተወሰነ ጊዜ ከሌሎች ሰዎች ተለይተው እንዲቆዩ ይደረግ ነበር። እንዲህ ያለ በሽታ ያለበት ሰው ሲድን እንደ “ንጹሕ” ተቆጥሮ ከማኅበረሰቡ ጋር ከመቀላቀሉ በፊት ልብሶቹን ማጠብና ገላውን በውኃ መታጠብ ነበረበት።—ዘሌዋውያን 14:8, 9

  •   በድን የነካ ሰው ከሰዎች ተለይቶ እንዲቆይ ይደረግ ነበር።—ዘሌዋውያን 5:2, 3፤ ዘኁልቁ 19:16

 ለእስራኤላውያን የተሰጡት ሕጎች ከሕክምናና ከንጽሕና ጋር በተያያዘ ከዘመኑ እጅግ የቀደሙ ነበሩ።

 ሌሎች ሕዝቦች ግን ከሥልጣኔ የራቁ የንጽሕና ደንቦች ነበሯቸው። አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።

  •   ቆሻሻ መንገድ ላይ ይጣል ነበር። የተበከለ ምግብና ውኃ እንዲሁም ሌሎች ቆሻሾች ለተለያዩ በሽታዎችና ለበርካታ ሕፃናት ሞት ምክንያት ይሆኑ ነበር።

  •   ጥንት የነበሩ ሐኪሞች ስለ በሽታ አምጪ ተሕዋስያን ምንም እውቀት አልነበራቸውም ሊባል ይችላል። ግብፃውያን የእንሽላሊት ደም፣ የሻላ ኩስ፣ የሞቱ አይጦች፣ ሽንትና የሻገተ ዳቦ ለመድኃኒትነት ይጠቀሙ ነበር። አልፎ ተርፎም የሰዎችና የእንስሳት እዳሪ ለሕክምና አገልግሎት ይውል ነበር።

  •   የጥንቶቹ ግብፃውያን በአባይ ወንዝና በመስኖ ቦዮች ውስጥ በሚገኙት ተሕዋስያን የተነሳ ይታመሙ ነበር። በተጨማሪም በግብፅ የነበሩ በርካታ ሕፃናት በተበከለ ምግብ ምክንያት በሚመጡ የተለያዩ ሕመሞችና በተቅማጥ ይሞቱ ነበር።

 እስራኤላውያን ግን አምላክ በሰጣቸው ሕጎች ውስጥ ያሉትን መመሪያዎች በመከተላቸው በአካባቢያቸው ከነበሩ ሕዝቦች የተሻለ ጤንነት ነበራቸው።