ጥር 26, 2021
ዚምባብዌ
የይሖዋ ምሥክሮች የማቴዎስ ወንጌልን በዚምባብዌ ምልክት ቋንቋ አወጡ
ጥር 24, 2021 መጽሐፍ ቅዱስ—የማቴዎስ ወንጌል በዚምባብዌ ምልክት ቋንቋ ወጣ። መጽሐፍ ቅዱሱ መውጣቱን አስቀድሞ በተቀረጸ ንግግር አማካኝነት ያበሰረው የዚምባብዌ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ታውራይ ማዛሩራ ነው።
በዚምባብዌ ምልክት ቋንቋ ጉባኤዎች የሚያገለግሉት 401 አስፋፊዎች ይህን መጽሐፍ በቅርቡ በማግኘታቸው በጣም ተደስተዋል። እነዚህ አስፋፊዎች የማቴዎስ ወንጌልን በግል ጥናታቸውና በአገልግሎታቸው ለመጠቀም ጓጉተዋል።
በአሁኑ ወቅት ያለው ወረርሽኝ የዚምባብዌ ምልክት ቋንቋ ቡድን የሚያከናውነው ሥራ ይበልጥ ተፈታታኝ እንዲሆን አድርጎ ነበር። ተርጓሚዎቹ የቋንቋ ችሎታቸውን ለማሻሻል የዚምባብዌ ምልክት ቋንቋ ከሚጠቀሙ ሌሎች ሰዎች ጋር አዘውትረው ይገናኙ ነበር። ሆኖም ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ የተጣሉት ገደቦች በማኅበረሰቡ ውስጥ ካሉ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ጋር መገናኘት እንዳይችሉ አገዷቸው። ተርጓሚዎቹ መስማት ከተሳናቸው ሰዎች ጋር በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት በመገናኘት ይህን ተፈታታኝ ሁኔታ መወጣት ችለዋል። ተርጓሚዎቹ ይህን ማድረጋቸው በዚምባብዌ የሚገኙ መስማት የተሳናቸው ሰዎች በሙሉ ሊረዱት የሚችሉ ትርጉም ለማዘጋጀት አስችሏቸዋል።
የዚምባብዌ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ጆን ሃንጉካ እንዲህ ብሏል፦ “የይሖዋ ምሥክሮች የማቴዎስ ወንጌልን በዚምባብዌ ምልክት ቋንቋ ካወጡ በኋላ ግባቸው ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ቋንቋ ማውጣት ነው። ይህ ፕሮጀክት እስከ አሥር ዓመት ድረስ ሊወስድ እንደሚችል እንገምታለን።”
ይህ ፕሮጀክት ይሖዋ ለሁሉም ሕዝቦች ያለውን ፍቅር የሚያሳይ ነው። እኛም ‘ለብሔር፣ ለነገድ፣ ለቋንቋና ለሕዝብ ሁሉ ምሥራቹን ለማብሰር’ ጥረት ስናደርግ ይሖዋ ይባርከናል።—ራእይ 14:6