ለቤተሰብ
ልጆች ሽንፈትን በጥሩ ሁኔታ እንዲወጡ መርዳት
ልጆቻችሁ በሚያደርጉት ነገር ሁሉ ስኬታማ ይሆናሉ ብሎ መጠበቅ የማይቻል ነገር ነው፤ አንዳንድ ነገሮች ሳይሳኩላቸው የሚቀሩበት ጊዜ ይኖራል። ታዲያ በዚህ ጊዜ ተስፋ እንዳይቆርጡ ልትረዷቸው የምትችሉት እንዴት ነው?
ማወቅ የሚኖርባችሁ ነገር
ስህተት የማይሠራ ማንም ሰው የለም። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሁላችንም እንሰናከላለን’ ይላል። (ያዕቆብ 3:2) ልጆችም ቢሆኑ የሚሰናከሉበት ጊዜ ይኖራል። እንዲያውም አንዳንድ ነገሮች ሳይሳኩላቸው መቅረታቸው አዎንታዊ ጎን ሊኖረው ይችላል፤ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ልጆች ችግሮችን የመቋቋም ችሎታ የሚያዳብሩበት አጋጣሚ ይሰጧቸዋል። ልጆች በተፈጥሯቸው ይህን ችሎታ ይዘው አይወለዱም፤ ከዚህ ይልቅ ሊያዳብሩት ይገባል። ሎራ የተባለች እናት እንዲህ ብላለች፦ “እኔና ባለቤቴ፣ ልጆቻችን ስህተት በሚሠሩበት ጊዜ ጉዳዩን አድበስብሰን ከማለፍ ይልቅ ሁኔታውን እንዲጋፈጡ ማድረግ የተሻለ እንደሆነ አስተውለናል። ምክንያቱም እንዲህ ማድረጋችን፣ አንድ ነገር ሳይሳካላቸው ሲቀር ቶሎ ተስፋ እንዳይቆርጡ ይረዳቸዋል።”
ብዙ ልጆች አንድ ነገር ሳይሳካላቸው ሲቀር ሁኔታውን በተገቢው መንገድ መወጣት ይከብዳቸዋል። ይህ የሆነበት አንዱ ምክንያት ወላጆች፣ ልጆቹ ምንም ጥፋት እንደሌለባቸው እንዲሰማቸው ስለሚያደርጉ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ልጆች በትምህርት ቤት መጥፎ ውጤት ሲያመጡ አንዳንድ ወላጆች ወዲያውኑ ጥፋቱን በአስተማሪው ላይ ያላክካሉ። አሊያም ደግሞ አንድ ልጅ ከጓደኛው ጋር ቢጣላ ወላጆቹ ጥፋቱ የጓደኛው እንጂ የልጃቸው እንዳልሆነ ሊናገሩ ይችላሉ።
እስቲ አስቡት፤ ልጆች ለጥፋታቸው ተጠያቂ እንዳይሆኑ ሁሌ ከለላ የሚደረግላቸው ከሆነ ለስህተታቸው ኃላፊነት መውሰድን እንዴት ሊማሩ ይችላሉ?
ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
ልጆቻችሁ ድርጊታቸው የሚያስከትለው ውጤት እንዳለ እንዲገነዘቡ እርዷቸው።
መጽሐፍ ቅዱስ “አንድ ሰው ምንም ዘራ ምን ያንኑ መልሶ ያጭዳል” ይላል።—ገላትያ 6:7
ማንኛውም ድርጊት የሆነ ውጤት ማስከተሉ አይቀርም። የተሳሳተ እርምጃ መጥፎ ውጤት ይኖረዋል። ጉዳት ከደረሰ ካሳ መከፈል አለበት። ልጆች የመንስኤንና የውጤትን መርሕ ማወቅ እንዲሁም ለተፈጠረው ነገር በተወሰነ መጠንም ቢሆን ተጠያቂ እንደሆኑ መገንዘብ ይኖርባቸዋል። በመሆኑም ጥፋቱን በሌላ ሰው ላይ ከማላከክ ወይም ልጆቻችሁን ጥፋተኛ ላለማድረግ ሰበብ አስባብ ከመደርደር ተቆጠቡ። ከዚህ ይልቅ ዕድሜያቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት ድርጊታቸው ያስከተለውን ውጤት እንዲቀበሉ አድርጉ። ልጆች በአንድ ጥፋትና በሚያስከትለው መዘዝ መካከል ያለው ተዛማጅነት በግልጽ ሊታያቸው ይገባል።
ልጆቻችሁ መፍትሔ የመፈለግ ችሎታ እንዲያዳብሩ እርዷቸው።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ጻድቅ ሰባት ጊዜ ቢወድቅ እንኳ መልሶ ይነሳል።”—ምሳሌ 24:16
አንድ ነገር ሳይሳካልን ሲቀር በጣም እንደምናዝን የታወቀ ነው፤ ሆኖም አንድ ነገር አልተሳካልንም ማለት ሁሉ ነገር አበቃለት ማለት አይደለም። ልጆቻችሁ ባለፈው ነገር ከመበሳጨት ይልቅ መፍትሔ በመፈለግ ላይ እንዲያተኩሩ እርዷቸው። ለምሳሌ ልጃችሁ ፈተና ከወደቀ ለወደፊቱ ጠንክሮ በማጥናት ውጤቱን ማሻሻል እንደሚችል እንዲያስተውል ልትረዱት ትችላላችሁ። (ምሳሌ 20:4) ልጃችሁ ከጓደኛዋ ጋር ከተጣላች ጥፋተኛው ማንም ይሁን ማን ቅድሚያውን ወስዳ ሰላም መፍጠር የምትችለው እንዴት እንደሆነ እንድታስተውል እርዷት።—ሮም 12:18፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:24
ልጆቻችሁ ለራሳቸው የተጋነነ አመለካከት እንዳይኖራቸው እርዷቸው።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “እያንዳንዱ ሰው ከሚገባው በላይ ስለ ራሱ በማሰብ ራሱን ከፍ አድርጎ አይመልከት።”—ሮም 12:3
ለልጃችሁ ‘አንተ ላይ ሊደርስብህ የሚችል ማንም ሰው የለም’ ብላችሁ መንገራችሁ ከእውነታው የራቀ ከመሆኑም ሌላ ልጃችሁን ምንም አይጠቅመውም። ምክንያቱም በትምህርታቸው በጣም ጎበዝ የሆኑ ልጆች እንኳ ውጤታቸው ዝቅ የሚልበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። እንዲሁም በአንድ ዓይነት ስፖርት በጣም ጎበዝ የሆኑ ልጆች ሁሌም በውድድር ያሸንፋሉ ማለት አይደለም። ለራሳቸው ሚዛናዊ አመለካከት ያላቸው ልጆች አንድ ነገር ሳይሳካላቸው ሲቀር ሁኔታውን በተሻለ መንገድ መወጣት ይችላሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ የሚደርስብን መከራ ይበልጥ ጠንካሮች እንደሚያደርገንና ጽናትን እንድናዳብር እንደሚረዳን ይናገራል። (ያዕቆብ 1:2-4) በመሆኑም አንድ ነገር ሳይሳካ መቅረቱ በራሱ የሚያሳዝን ቢሆንም ልጆቻችሁ ለጉዳዩ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲያዳብሩ እርዷቸው።
አንድ ሙያ ማስተማር ጊዜና ጥረት እንደሚጠይቅ ሁሉ ልጆች ችግሮችን የመቋቋም ችሎታ እንዲያዳብሩ መርዳትም ጊዜና ጥረት ይጠይቃል። ሆኖም እንዲህ ማድረጋችሁ ልጆቻችሁ የተሻሉ ወጣቶች እንዲሆኑ ስለሚረዳ ልፋታችሁ ፈጽሞ አያስቆጭም። ሌቲንግ ጎ ዊዝ ላቭ ኤንድ ኮንፊደንስ የተባለው መጽሐፍ “ችግሮችን የመቋቋም ችሎታ ያዳበሩ ወጣቶች፣ ካጋጠማቸው አስጨናቂ ሁኔታ ለመገላገል ሲሉ አጉል ነገር የሚያደርጉበት አጋጣሚ ዝቅተኛ ነው” ብሏል። አክሎም “አዲስ ወይም ያልጠበቁት ነገር ሲያጋጥማቸው አብዛኛውን ጊዜ ሁኔታውን በተሳካ መንገድ ይወጡታል” በማለት ገልጿል። ልጆች ችግሮችን የመቋቋም ችሎታን ማዳበራቸው አዋቂ ከሆኑ በኋላም እንደሚጠቅማቸው የታወቀ ነው።
ጠቃሚ ምክር፦ ጥሩ ምሳሌ ሁኑ። ልጆቻችሁ አንድ ነገር ሳይሳካላቸው ሲቀር ጉዳዩን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው የሚማሩት እናንተ በሕይወታችሁ ውስጥ አንድ መሰናክል ሲያጋጥማችሁ ጉዳዩን የምትይዙበትን መንገድ በማየት እንደሆነ አትዘንጉ።