የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው
ገላትያ 6:9—“መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት”
“ካልታከትን ጊዜው ሲደርስ ስለምናጭድ ተስፋ ቆርጠን መልካም ሥራ መሥራታችንን አንተው።”—ገላትያ 6:9 አዲስ ዓለም ትርጉም
“ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት።”—ገላትያ 6:9 የ1954 ትርጉም
የገላትያ 6:9 ትርጉም
ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖች በአምላክ ፊት መልካም ወይም ጥሩ የሆነውን ነገር ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ ማበረታቻ ሰጥቷል። እንዲህ ካደረጉ አምላክ እንደሚክሳቸው እርግጠኛ መሆን ይችላሉ።
“ተስፋ [አንቁረጥ]።” ይህ አገላለጽ “አንዛል” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። በኩረ ጽሑፉ ላይ የተሠራበት ቃል፣ ወደኋላ አለማለትን ወይም ቅንዓት አለማጣትንም ሊያመለክት ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ “እኛ” የሚል አገላለጽ በመጠቀም እሱም ከተስፋ መቁረጥ ስሜት ጋር መታገል የሚያስፈልገው ጊዜ እንዳለ ሳይሸሽግ ተናግሯል።—ሮም 7:21-24
“መልካም ሥራ” ወይም ጥሩ ሥራ የሚለው አገላለጽ አንድ ክርስቲያን በአምላክ አገልግሎት ሊያከናውናቸው የሚገቡ ነገሮችን በሙሉ ያጠቃልላል። ይህም አንድ ሰው የእምነት ባልንጀሮቹን ወይም ሌሎችን ለመርዳት ሲል የሚሠራቸውን ሥራዎች ይጨምራል።—ገላትያ 6:10
“ካልታከትን ጊዜው ሲደርስ [እናጭዳለን]።” ጳውሎስ አንባቢዎቹን አንድ ገበሬ ሰብሉ እስኪያድግ ድረስ መጠበቅ እንደሚያስፈልገው ሁሉ እነሱም መልካም ሥራቸው የሚያስገኘውን ውጤት ለማየት መጠበቅ ሊያስፈልጋቸው እንደሚችል አሳስቧቸዋል። ጳውሎስ ስለ ማጨድ በመናገር ይህን ጥቅስ በቁጥር 7 ላይ ከሚገኘው መሠረታዊ እውነት ጋር አያይዞታል፦ “አንድ ሰው ምንም ዘራ ምን ያንኑ መልሶ ያጭዳል።” በሌላ አባባል አንድ ክርስቲያን በአምላክ ፊት መልካም የሆነውን ነገር ሲያደርግ የዘላለም ሕይወትን ጨምሮ ትልቅ በረከት ያጭዳል።—ሮም 2:6, 7፤ ገላትያ 6:8
የገላትያ 6:9 አውድ
ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ደብዳቤ በገላትያ ላሉ ክርስቲያኖች የጻፈላቸው ከ50-52 ዓ.ም. ገደማ ነው። ይህን ደብዳቤ የጻፈው ክርስቲያን እንደሆኑ ቢናገሩም ስለ ኢየሱስ የሚገልጸውን እውነት የሚያጣምሙ ሰዎች ከሚያሳድሩት ተጽዕኖ ክርስቲያኖችን ለመጠበቅ ነው። (ገላትያ 1:6, 7) እነዚህ የሐሰት አስተማሪዎች፣ ክርስቲያኖች አምላክ በሙሴ አማካኝነት ለጥንቱ የእስራኤል ብሔር የሰጠውን ሕግ መታዘዝ እንዳለባቸው በመግለጽ ይከራከሩ ነበር። (ገላትያ 2:15, 16) ጳውሎስ ሕጉ ዓላማውን ዳር እንዳደረሰና የአምላክ አገልጋዮች በሕጉ ሥር መሆናቸው እንዳበቃ ገልጿል።—ሮም 10:4፤ ገላትያ 3:23-25
ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹን ‘መልካም ሥራ መሥራታቸውን’ እንዲቀጥሉ ሲያበረታታቸው የሙሴን ሕግ መታዘዝ እንዳለባቸው መናገሩ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ‘የክርስቶስን ሕግ እንዲፈጽሙ’ ማለትም ኢየሱስ ለሌሎች መልካም ስለማድረግ ያስተማራቸውን ነገሮች በሙሉ ሥራ ላይ እንዲያውሉ ማበረታታቱ ነበር።—ገላትያ 6:2፤ ማቴዎስ 7:12፤ ዮሐንስ 13:34
የገላትያ መጽሐፍን አጠቃላይ ይዘት ለማየት ይህን አጭር ቪዲዮ ተመልከት።