ሰዎች የሚሞቱት ለምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
በተለይ የቅርብ ወዳጆቻችንን በሞት ስናጣ ሰዎች ለምን እንደሚሞቱ መጠየቃችን የተለመደ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ሞት የሚያስከትለው መንደፊያ ኃጢአት ነው” ይላል።—1 ቆሮንቶስ 15:56
ሁሉም ሰዎች ኃጢአተኛ የሆኑትና የሚሞቱት ለምንድን ነው?
የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን የሆኑት አዳምና ሔዋን በአምላክ ላይ ኃጢአት በመሥራታቸው ምክንያት ሞተዋል። (ዘፍጥረት 3:17-19) አምላክ “የሕይወት ምንጭ” በመሆኑ በእሱ ላይ ማመፅ ሞት ማስከተሉ ሳይታለም የተፈታ ነው።—መዝሙር 36:9፤ ዘፍጥረት 2:17
አዳም የነበረበትን ኃጢአት ለዘሮቹ በሙሉ አስተላልፏል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “በአንድ ሰው አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ።” (ሮም 5:12) ሁሉም ሰዎች የሚሞቱት ኃጢአተኞች በመሆናቸው ነው።—ሮም 3:23
ሞት የሚወገደው እንዴት ነው?
አምላክ ‘ሞትን ለዘላለም የሚውጥበት’ ጊዜ እንደሚመጣ ቃል ገብቷል። (ኢሳይያስ 25:8) ሞትን ለማስወገድ ግን መጀመሪያ ምንጩን ማለትም ኃጢአትን ማጥፋት ያስፈልገዋል። አምላክ ይህን የሚያደርገው ‘የዓለምን ኃጢአት በሚያስወግደው’ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ነው።—ዮሐንስ 1:29፤ 1 ዮሐንስ 1:7