አምላክ በሁሉም ቦታ ይገኛል?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
አምላክ ሁሉንም ነገር ማየት ይችላል፤ እንዲሁም በሚፈልግበት ቦታ እርምጃ መውሰድ ይችላል። (ምሳሌ 15:3፤ ዕብራውያን 4:13) ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በሁሉም ቦታ አሊያም በሁሉም ነገር ውስጥ እንደሚገኝ አያስተምርም። ከዚህ ይልቅ አምላክ የራሱ አካል እንዲሁም የተወሰነ መኖሪያ ቦታ እንዳለው ያስተምራል።
አምላክ ምን ዓይነት አካል አለው? አምላክ መንፈሳዊ አካል ነው። (ዮሐንስ 4:24) ሰዎች አምላክን ሊያዩት አይችሉም። (ዮሐንስ 1:18) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት ስለ አምላክ የታዩ ራእዮች በሙሉ አምላክ የተወሰነ መኖሪያ ሥፍራ እንዳለው ያሳያሉ። በሁሉም ቦታ እንደሚገኝ ተደርጎ የተገለጸበት አንድም ዘገባ የለም።—ኢሳይያስ 6:1, 2፤ ራእይ 4:2, 3, 8
አምላክ የሚኖረው የት ነው? አምላክ የሚኖረው ከግዑዝ ፍጥረታት ውጭ በሆነ መንፈሳዊ ዓለም ውስጥ ነው። አምላክ በዚህ መንፈሳዊ ዓለም ውስጥ ‘በሰማያት ባለ ማደሪያው’ ይኖራል። (1 ነገሥት 8:30) መጽሐፍ ቅዱስ መንፈሳዊ ፍጥረታት “በይሖዋ ፊት ለመቆም” የገቡበት ወቅት እንደነበር ይናገራል፤ a ይህም አምላክ የሚኖርበት የተወሰነ ሥፍራ እንዳለው ያሳያል።—ኢዮብ 1:6
አምላክ በሁሉም ቦታ የማይገኝ ከሆነ በግለሰብ ደረጃ ትኩረት ሊሰጠኝ የሚችለው እንዴት ነው?
አምላክ ለእያንዳንዳችን በግለሰብ ደረጃ ትኩረት ይሰጠናል። የሚኖረው በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ቢሆንም በምድር ላይ ያሉ እሱን የማስደሰት ልባዊ ፍላጎት ያላቸው ሰዎችን ትኩረት ሰጥቶ ይመለከታል፤ እንዲሁም እነሱን ለመርዳት ሲል እርምጃ ይወስዳል። (1 ነገሥት 8:39፤ 2 ዜና መዋዕል 16:9) ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ያለውን አሳቢነት የሚያሳየው እንዴት እንደሆነ ተመልከት፦
በምትጸልይበት ጊዜ፦ ይሖዋ ወደ እሱ በምትጸልይበት ቅጽበት ጸሎትህን ይሰማል።—2 ዜና መዋዕል 18:31
በጭንቀት በምትዋጥበት ጊዜ፦ “ይሖዋ ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የተደቆሰባቸውንም ያድናል።”—መዝሙር 34:18
መመሪያ በሚያስፈልግህ ጊዜ፦ ይሖዋ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ‘ጥልቅ ማስተዋል ይሰጥሃል፤ እንዲሁም ያስተምርሃል።’—መዝሙር 32:8
ብዙዎች የአምላክን መገኛ በተመለከተ ያላቸው የተሳሳተ አመለካከት
የተሳሳተ አመለካከት፦ አምላክ በሁሉም ፍጥረታት ውስጥ ይገኛል።
እውነታው፦ አምላክ በምድርም ሆነ በግዑዙ ጽንፈ ዓለም ውስጥ በሚገኝ በየትኛውም ቦታ አይኖርም። (1 ነገሥት 8:27) እርግጥ ነው፣ ከዋክብትን ጨምሮ የአምላክ የፍጥረት ሥራዎች “የአምላክን ክብር ይናገራሉ።” (መዝሙር 19:1) ሆኖም አንድ ሠዓሊ በሥዕሉ ውስጥ ሊኖር እንደማይችል ሁሉ አምላክም በፍጥረታቱ ውስጥ ሊኖር አይችልም። ነገር ግን አንድን ሥዕል በመመልከት ስለ ሠዓሊው አንዳንድ ነገሮችን ማወቅ እንችላለን። በተመሳሳይም ግዑዙን ዓለም በመመልከት የፈጠረው አካል ስላሉት ‘የማይታዩ ባሕርያት’ ለምሳሌ ስለ ኃይሉ፣ ስለ ጥበቡ እንዲሁም ስለ ፍቅሩ ማወቅ እንችላለን።—ሮም 1:20
የተሳሳተ አመለካከት፦ አምላክ ሁሉን ነገር ሊያውቅ እንዲሁም ሁሉንም ነገር ሊያደርግ የሚችለው በሁሉም ቦታ የሚገኝ ከሆነ ብቻ ነው።
እውነታው፦ መንፈስ ቅዱስ በሥራ ላይ ያለ የአምላክ ኃይል ነው። አምላክ በአካል መገኘት ሳያስፈልገው በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት፣ በየትኛውም ቦታና ጊዜ እየተከናወነ ያለን ነገር ማየት እንዲሁም ማንኛውንም ነገር ማድረግ ይችላል።—መዝሙር 139:7
የተሳሳተ አመለካከት፦ በመዝሙር 139:8 ላይ የሚገኘው “ወደ ሰማይ ብወጣ አንተ በዚያ አለህ፤ በመቃብር አልጋዬን ባነጥፍም እነሆ፣ አንተ በዚያ ትኖራለህ” የሚለው ሐሳብ አምላክ በሁሉም ቦታ እንደሚገኝ ያመለክታል።
እውነታው፦ ይህ ጥቅስ የሚናገረው አምላክ ስለሚገኝበት ቦታ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ጥቅሱ አምላክ ለእኛ ሲል እርምጃ እንዳይወስድ ሊያግደው የሚችል ምንም ርቀት እንደሌለ ማራኪ በሆነ መንገድ ይገልጻል።
a መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የአምላክ ስም ይሖዋ ነው።