ኦሪት ምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
“ኦሪት” የሚለው ቃል ቶራ ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል የተወሰደ ሲሆን “መመሪያ፣” “ትምህርት” ወይም “ሕግ” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። a (ምሳሌ 1:8፤ 3:1፤ 28:4) ቀጥሎ የተጠቀሱት ምሳሌዎች ይህ የዕብራይስጥ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዴት እንደተሠራበት ያሳያሉ።
አብዛኛውን ጊዜ ቶራ የሚለው ቃል የሚያመለክተው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን የመጀመሪዎቹን አምስት መጻሕፍት ማለትም ዘፍጥረት፣ ዘፀአት፣ ዘሌዋውያን፣ ዘኁልቁና ዘዳግምን ነው። እነዚህ መጻሕፍት ፔንታቱክ በመባልም ይታወቃሉ፤ ይህ ቃል “ባለ አምስት ጥራዝ” የሚል ትርጉም ካለው የግሪክኛ ቃል የተወሰደ ነው። ኦሪትን የጻፈው ሙሴ እንደመሆኑ መጠን ‘የሙሴ የሕግ መጽሐፍ’ በመባልም ይታወቃል። (ኢያሱ 8:31፤ ነህምያ 8:1) ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው ኦሪት በመባል የሚታወቁት አምስት መጻሕፍት መጀመሪያ ላይ አንድ መጽሐፍ የነበሩ ሲሆን ከጊዜ በኋላ ለአጠቃቀም እንዲመች ሲባል ተከፋፍለዋል።
ቶራ የሚለው ቃል በአንድ ጉዳይ ላይ ለእስራኤላውያን የተሰጡ ሕጎችን ለማመልከትም ተሠርቶበታል፤ ‘የኃጢአት መባን ሕግ [ቶራ]፣” ‘የሥጋ ደዌን የሚመለከተውን ሕግ’ ወይም ‘ናዝራዊን የሚመለከተውን ሕግ’ እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።—ዘሌዋውያን 6:25፤ 14:57፤ ዘኁልቁ 6:13
ቶራ የሚለው ቃል ከወላጆች፣ ጥበበኛ ከሆኑ ሰዎች ወይም ከአምላክ የተሰጠን መመሪያ እና ትምህርት ለማመልከት የተሠራበትም ጊዜ አለ።—ምሳሌ 1:8፤ 3:1፤ 13:14፤ ኢሳይያስ 2:3 የግርጌ ማስታወሻ
ኦሪት ወይም ፔንታቱክ በውስጡ ምን ነገሮችን ይዟል?
ከፍጥረት አንስቶ ሙሴ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ አምላክ ከሰዎች ጋር ስለነበረው ግንኙነት የሚገልጸውን ታሪክ።—ዘፍጥረት 1:27, 28፤ ዘዳግም 34:5
በሙሴ ሕግ ውስጥ የሚገኙትን ትእዛዛት። (ዘፀአት 24:3) የሙሴ ሕግ ከ600 የሚበልጡ ደንቦችን ይዟል። ከእነዚህ መካከል በሰፊው የሚታወቀው ሽማ የሚባለው የአይሁዳውያን የእምነት መግለጫ ነው። የሽማ አንዱ ክፍል እንዲህ ይላል፦ “አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ ኃይልህ ውደድ።” (ዘዳግም 6:4-9) ኢየሱስ ይህ ትእዛዝ “ከሁሉ የሚበልጠውና የመጀመሪያው ትእዛዝ” እንደሆነ ተናግሯል።—ማቴዎስ 22:36-38
ይሖዋ የሚለው የአምላክ ስም ወደ 1,800 ጊዜያት ያህል ተጠቅሶ ይገኛል። ኦሪት የአምላክን ስም መጠቀምን ከመከልከል ይልቅ የአምላክ ሕዝቦች ስሙን መጥራት እንዲኖርባቸው የሚያደርጉ ትእዛዛትን ይዟል።—ዘኁልቁ 6:22-27፤ ዘዳግም 6:13፤ 10:8፤ 21:5
ሰዎች ኦሪትን በተመለከተ ያላቸው የተሳሳተ አመለካከት
የተሳሳተ አመለካከት፦ በኦሪት ውስጥ የሚገኙት ሕጎች መቼም ቢሆን የማይሻሩና ዘላለማዊ ናቸው።
እውነታው፦ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ከሰንበት፣ ከክህነት ሥርዓት እንዲሁም ከስርየት ቀን ጋር የተያያዙትን ደንቦች ጨምሮ በኦሪት ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ደንቦች “የዘላለም” ሥርዓት እንደሆኑ ይጠቅሳሉ። (ዘፀአት 31:16፤ 40:15፤ ዘሌዋውያን 16:33, 34 የ1954 ትርጉም) ሆኖም በእነዚህ ጥቅሶች ላይ የተሠራበት የዕብራይስጥ ቃል የሚያመለክተው ለዘላለም የሚቀጥል ነገርን ብቻ አይደለም፤ ቃሉ ላልተወሰነ ጊዜ የሚቀጥልን ነገርም ሊያመለክት ይችላል። b የሙሴ ሕግ ለ900 ዓመታት ያህል ጥቅም ላይ ከዋለ በኋላ አምላክ ይህን ሕግ ‘በአዲስ ቃል ኪዳን’ እንደሚተካው ትንቢት ተናግሯል። (ኤርምያስ 31:31-33) “[አምላክ] ‘አዲስ ቃል ኪዳን’ [በማለት] የቀድሞውን ቃል ኪዳን ጊዜ ያለፈበት አድርጎታል።” (ዕብራውያን 8:7-13) ከ2,000 ዓመታት ገደማ በፊት በኢየሱስ ሞት አማካኝነት የተቋቋመው አዲሱ ቃል ኪዳን የቀድሞውን ቃል ኪዳን ተክቶታል።—ኤፌሶን 2:15
የተሳሳተ አመለካከት፦ የአይሁዳውያን ወጎችና ታልሙድ በጽሑፍ ከሰፈረው ኦሪት እኩል ተቀባይነት ሊኖራቸው ይገባል።
እውነታው፦ አምላክ ለሙሴ በጽሑፍ ከሰፈረው ኦሪት ጋር አብሮ የቃል ሕግ እንደሰጠው የሚናገር ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ሙሴን “እነዚህን ቃላት ጻፍ” እንዳለው ይናገራል። (ዘፀአት 34:27) በኋላ ላይ በጽሑፍ የሰፈረውና ሚሽና በመባል የሚታወቀው የቃል ሕግ ለታልሙድ መሠረት የሆነ ሲሆን ፈሪሳውያን የፈጠሯቸውን የአይሁድ ወጎች ይዟል። እነዚህ ወጎች በአብዛኛው ከኦሪት ጋር ይቃረናሉ። በዚህም ምክንያት ኢየሱስ ፈሪሳውያኑን “ለወጋችሁ ስትሉ የአምላክን ቃል ሽራችኋል” ብሏቸዋል።—ማቴዎስ 15:1-9
የተሳሳተ አመለካከት፦ ሴቶች ኦሪትን መማር የለባቸውም።
እውነታው፦ በሙሴ ሕግ ውስጥ ሕጉ ሴቶችንና ልጆችን ጨምሮ ለእስራኤል ሕዝብ በሙሉ እንዲነበብ የሚያዝ መመሪያ ይገኛል። ለምን? “ስለ [አምላካቸው] ስለ ይሖዋ ይሰሙና ይማሩ እንዲሁም እሱን ይፈሩ ዘንድ ብሎም የዚህን ሕግ ቃላት በሙሉ በጥንቃቄ እንዲፈጽሙ” ነው።—ዘዳግም 31:10-12 c
የተሳሳተ አመለካከት፦ ኦሪት ድብቅ መልእክቶችን ይዟል።
እውነታው፦ ኦሪትን የጻፈው ሙሴ የኦሪት መልእክት ሚስጥራዊ ሳይሆን ግልጽና ማንኛውም ሰው ሊረዳው የሚችል እንደሆነ ተናግሯል። (ዘዳግም 30:11-14) በኦሪት ውስጥ ድብቅ መልእክቶች አሉ የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ካባላ ተብሎ በሚጠራው ልማዳዊ የአይሁድ ሚስጥራዊ አምልኮ ውስጥ ያለ ትምህርት ሲሆን ቅዱሳን መጻሕፍትን ለመተርጎም “ብልሃት” የሚንጸባረቅባቸውን ዘዴዎች ይጠቀማል። d—2 ጴጥሮስ 1:16
a ተሻሽሎ የቀረበውን ዘ ስትሮንገስት ስትሮንግስ ኤግዞስቲቭ ኮንኮርዳንስ ኦቭ ዘ ባይብል “ሂብሩ አረማይክ ዲክሽነሪ ኢንዴክስ ቱ ዚ ኦልድ ቴስታመንት” በሚለው ክፍል ሥር የገባውን 8451ኛ ነጥብ ተመልከት።
b ቲኦሎጂካል ወርድቡክ ኦቭ ዚ ኦልድ ቴስታመንት የተባለውን መጽሐፍ ጥራዝ 2 ከገጽ 672-673 ተመልከት።
c ኦሪት ራሱ ከሚያስተምረው በተቃራኒ የአይሁድ ወግ ሴቶች ኦሪትን እንዳይማሩ ይከለክል ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ሚሽና የተባለው ጽሑፍ ኤሊዔዘር ቤን ኸርኬነስ የተባለው ረቢ “ለሴት ልጁ ኦሪትን የሚያስተምር ሰው ብልግና እያስተማራት ነው” በማለት የተናገረውን ሐሳብ ይዟል። (ሶታ 3:4) ዘ ጀሩሳሌም ታልሙድም የሚከተለውን ንግግር ጨምሮ ይጠቅሳል፦ “የኦሪትን ቃላት ለሴቶች ከማስተማር ይልቅ በእሳት ማቃጠል ይሻላል።”—ሶታ 3:19ሀ
d ለምሳሌ ያህል፣ ኢንሳይክሎፔዲያ ጁዳይካ የካባላ ትምህርት ከኦሪት ጋር በተያያዘ ያለውን አመለካከት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ኦሪት ይህ ነው የሚባል ቀጥተኛ ትርጉም የለውም፤ የተለያዩ ሰዎች በተለያየ መንገድ ሊተረጉሙት ይችላሉ።”—ሁለተኛ እትም፣ ጥራዝ 2፣ ገጽ 659