የይሖዋ ምሥክሮች አገልግሎታቸውን ለማከናወን የሚሠለጥኑት እንዴት ነው?
የይሖዋ ምሥክሮች ከሁሉም የክርስቲያናዊ ሕይወታቸው ዘርፎች ጋር በተያያዘ ሁልጊዜ ሥልጠና ያገኛሉ፤ ሥልጠናው ሕዝባዊ አገልግሎታቸውንም ያካትታል። ይህ አገልግሎት ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ እንዲያከናውኑ ያዘዛቸው ሥራ ይኸውም የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጅና ማስተማር ነው። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) ሥልጠናውን የምናገኘው በየሳምንቱ በምናደርጋቸው ስብሰባዎች እንዲሁም ዓመታዊ በሆኑት ትላልቅ ስብሰባዎቻችን ላይ ነው። በጉባኤ ውስጥም ሆነ በድርጅቱ ውስጥ ኃላፊነት ያላቸው የይሖዋ ምሥክሮች ደግሞ ለየት ያለ ተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥልጠና የሚያገኙባቸው ትምህርት ቤቶች አሉ።
በዚህ ርዕስ ውስጥ
የይሖዋ ምሥክሮች የሚሠለጥኑት እንዴት ነው?
የጉባኤ ስብሰባዎች። በየሳምንቱ በስብሰባ አዳራሾቻችን ውስጥ ለአምልኮ ሁለት ጊዜ እንሰበሰባለን። አንደኛው ስብሰባ በአብዛኛው የሚከናወነው በሳምንቱ መሃል ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በሳምንቱ መጨረሻ ነው። ስብሰባዎቻችን ለሕዝብ ክፍት ናቸው፤ ሙዳየ ምጽዋት አይዞርም።
በሳምንቱ መሃል የሚደረግ ስብሰባ። በዚህ ስብሰባ ላይ ከንባብ፣ ከውይይት ክህሎት፣ ለሕዝብ ከሚቀርብ ንግግር እንዲሁም ከስብከትና ከማስተማር ጋር የተያያዙ ሥልጠናዎችን እናገኛለን። ሥልጠናው በንግግሮች፣ በጋራ በሚደረጉ ውይይቶች፣ በሠርቶ ማሳያዎችና በቪዲዮዎች መልክ ይቀርባል። ይህ ሥልጠና የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለሰዎች በመናገርም ሆነ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ በማስጠናት ረገድ ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን ያስችለናል። በስብሰባዎቻችን ላይ የሚገኙ ሁሉ ከእነዚህ ሥልጠናዎች ይጠቀማሉ። ከሁሉ በላይ ደግሞ ስብሰባዎቻችን በአምላክ ላይ ያለንን እምነት እንዲሁም ለእሱና ለእምነት አጋሮቻችን ያለንን ፍቅር ያጠናክሩልናል።
በሳምንቱ መጨረሻ የሚደረግ ስብሰባ። ይህ ስብሰባ ሁለት ክፍሎች አሉት። የመጀመሪያው፣ በተለይ የይሖዋ ምሥክር ላልሆኑ ሰዎች ታስቦ የተዘጋጀ ንግግር ነው። ሁለተኛው ክፍል ደግሞ በመጠበቂያ ግንብ የጥናት እትም ላይ በወጣ ርዕስ ላይ የተመሠረተ በጥያቄና መልስ የሚሸፈን ውይይት ነው። a መጠበቂያ ግንብ ላይ የሚወጡት ርዕሶች በአገልግሎታችንም ሆነ በግል ሕይወታችን የሚጠቅሙንን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐሳቦችና መመሪያዎች ያብራራሉ።
ትላልቅ ስብሰባዎች። በየዓመቱ ሦስት ትላልቅ ስብሰባዎች የምናደርግ ሲሆን በእነዚህም ላይ ብዙ ጉባኤዎች አንድ ላይ ይሰበሰባሉ። በእነዚህ አስደሳች ስብሰባዎች ላይ አንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጭብጥ የሚብራራ ሲሆን ትምህርቱ ንግግሮችን፣ ሠርቶ ማሳያዎችን፣ መነባንቦችንና ቃለ መጠይቆችን እንዲሁም ቪዲዮዎችን ያካተተ ነው። እንደ ጉባኤ ስብሰባዎቻችን ሁሉ ትላልቅ ስብሰባዎቻችንም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለንን እውቀት እንድናሳድግና የተሻልን የምሥራቹ ሰባኪዎች እንድንሆን ይረዱናል። በእነዚህ ስብሰባዎችም ላይ ማንኛውም ሰው መገኘት ይችላል፤ ሙዳየ ምጽዋት አይዞርም።
የይሖዋ ምሥክሮች የሚሠለጥኑባቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ቤቶች
አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች ተጨማሪ ሥልጠና እንዲያገኙ ሲባል በተለያዩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ቤቶች እንዲካፈሉ ይጋበዛሉ። እነዚህ ትምህርት ቤቶች የትኞቹ ናቸው? የትምህርት ቤቶቹ ዓላማ ምንድን ነው? ሥልጠናው ምን ያህል ጊዜ ይወስዳል? በትምህርት ቤቶቹ መካፈል የሚችሉት እነማን ናቸው?
የአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤት
ዓላማው፦ አቅኚዎች b ተብለው የሚጠሩት የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ መርዳት። ሥልጠናው የክፍል ውስጥ ውይይቶችን፣ ሠርቶ ማሳያዎችን፣ መነባንቦችን፣ ንግግሮችንና የልምምድ ፕሮግራሞችን ያካተተ ነው።
የሚወስደው ጊዜ፦ ስድስት ቀን።
መሥፈርት፦ በአቅኚነት ለአንድ ዓመት ያገለገሉ የይሖዋ ምሥክሮች በትምህርት ቤቱ እንዲካፈሉ ግብዣ ይቀርብላቸዋል። በተጨማሪም በትምህርት ቤቱ ከተካፈሉ አምስት ዓመት ያለፋቸውና ለረጅም ዓመታት ያገለገሉ አቅኚዎች በድጋሚ ወደ ትምህርት ቤቱ ሊጋበዙ ይችላሉ።
የመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት
ዓላማው፦ ተሞክሮ ላካበቱ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ልዩ ሥልጠና መስጠት። ተማሪዎች የመስበክና የማስተማር ችሎታቸውን እንዲያሻሽሉ የሚረዳቸው ከመሆኑም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ርዕሶችን በጥልቀት ያጠናሉ። ብዙዎቹ ተመራቂዎች፣ ወንጌላውያን ይበልጥ በሚያስፈልጉባቸው ቦታዎች እንዲያገለግሉ ይጋበዛሉ።
የሚወስደው ጊዜ፦ ሁለት ወር።
መሥፈርት፦ ብቃቶቹን ያሟሉና ወንጌላውያን በሚያስፈልጉባቸው ቦታዎች ለማገልገል ሁኔታቸው የሚፈቅድላቸው አቅኚዎች በትምህርት ቤቱ ለመካፈል ማመልከት ይችላሉ።
የጉባኤ ሽማግሌዎች ትምህርት ቤት
ዓላማው፦ የጉባኤ ሽማግሌዎች c እንደ ማስተማርና እረኝነት ማድረግ የመሳሰሉ የጉባኤ ኃላፊነቶቻቸውን መወጣት እንዲችሉ እንዲሁም ለአምላክና ለእምነት አጋሮቻቸው ያላቸውን ፍቅር እንዲያሳድጉ መርዳት።—1 ጴጥሮስ 5:2, 3
የሚወስደው ጊዜ፦ አምስት ቀን።
መሥፈርት፦ አዲስ የተሾሙ የጉባኤ ሽማግሌዎች እንዲሁም ላለፉት አምስት ዓመታት በትምህርት ቤቱ ያልተካፈሉ ተሞክሮ ያዳበሩ ሽማግሌዎች ወደ ትምህርት ቤቱ ይጋበዛሉ።
ለወረዳ የበላይ ተመልካቾችና ለሚስቶቻቸው የተዘጋጀ ትምህርት ቤት
ዓላማው፦ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች d ተብለው የሚጠሩት ተጓዥ አገልጋዮች ኃላፊነቶቻቸውን ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲወጡ መርዳት። (1 ጢሞቴዎስ 5:17) ሥልጠናው እነዚህ ክርስቲያን ሽማግሌዎችና ሚስቶቻቸው ስለ ቅዱሳን መጻሕፍት ጥልቀት ያለው እውቀት እንዲኖራቸውም ያግዛቸዋል።
የሚወስደው ጊዜ፦ አንድ ወር።
መሥፈርት፦ አዲስ የተሾሙ የወረዳ የበላይ ተመልካቾችና ሚስቶቻቸው አገልግሎታቸውን ከጀመሩ ከአንድ ዓመት በኋላ ወደ ትምህርት ቤቱ ይጋበዛሉ። ከዚያ በኋላም በየአምስት ዓመቱ በትምህርት ቤቱ በድጋሚ እንዲካፈሉ ይጋበዛሉ።
የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት
ዓላማው፦ የጉባኤ ሽማግሌዎችና አገልጋዮች e የጉባኤ ኃላፊነቶቻቸውን ሲወጡ ወቅታዊ ሁኔታዎችን፣ እየታዩ ያሉ አዝማሚያዎችን ወይም ትኩረት የሚያሻቸው ጉዳዮችን ከግምት እንዲያስገቡ ሥልጠና መስጠት። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ትምህርት ቤቱ በየተወሰነ ዓመቱ ይካሄዳል።
የሚወስደው ጊዜ፦ የተለያየ ነው፤ በአብዛኛው አንድ ቀን።
መሥፈርት፦ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች፣ የጉባኤ ሽማግሌዎችና አገልጋዮች።
የቤቴል አገልግሎት ትምህርት ቤት
ዓላማው፦ የቤቴል f ቤተሰብ አባላት ሥራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ እንዲሁም ለአምላክና አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን ፍቅር እንዲያሳድጉ መርዳት።
የሚወስደው ጊዜ፦ አምስት ቀን ተኩል።
መሥፈርት፦ አዳዲስ ቤቴላውያን በትምህርት ቤቱ እንዲካፈሉ ይጠበቅባቸዋል። ለረጅም ጊዜ ያገለገሉና ላለፉት አምስት ዓመታት በትምህርት ቤቱ ያልተካፈሉ ቤቴላውያን እንደገና ሊጋበዙ ይችላሉ።
ጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት
ዓላማው፦ ተማሪዎቹ በጽሑፍ ለሰፈረው የአምላክ ቃል ጥልቅ አድናቆት እንዲያድርባቸውና የተማሩትን ተግባራዊ እንዲያደርጉ መርዳት። (1 ተሰሎንቄ 2:13) በመንፈሳዊ በሳል የሆኑት ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች በጊልያድ የሚያገኙት ሥልጠና፣ ለይሖዋ ድርጅት ይበልጥ ጠቃሚ ሀብት እንዲሆኑ ብሎም ለዓለም አቀፉ የማስተማር ሥራ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ይረዳቸዋል። ተመራቂዎቹ በአገራቸው ውስጥ ወይም በሌላ አገር ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ አሊያም መስክ ላይ እንዲያገለግሉ ሊመደቡ ይችላሉ።
የሚወስደው ጊዜ፦ አምስት ወር።
መሥፈርት፦ ቅርንጫፍ ቢሮዎች የሙሉ ጊዜ አገልጋዮችን መርጠው ለትምህርት ቤቱ እንዲያመለክቱ ይጋብዛሉ። ሥልጠናው የሚሰጠው በፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የትምህርት ማዕከል ውስጥ ነው።
ለቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላትና ለሚስቶቻቸው የተዘጋጀ ትምህርት ቤት
ዓላማው፦ የቅርንጫፍ ኮሚቴ g አባላት በቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የሚካሄደውን ሥራ በበላይነት እንዲከታተሉ ማሠልጠን፤ እነዚህ የጎለመሱ ወንድሞች ባሉበት አገር ወይም በቅርንጫፍ ቢሯቸው ሥር በተካተቱ አገራት ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያካሂዷቸውን መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችም ያስተባብራሉ።
የሚወስደው ጊዜ፦ ሁለት ወር።
መሥፈርት፦ የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላትንና ሚስቶቻቸውን ወደ ትምህርት ቤቱ ይጋብዛል፤ ሥልጠናው የሚሰጠው በፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የትምህርት ማዕከል ውስጥ ነው።
የይሖዋ ምሥክሮች የሚያገኙት ሥልጠና በምን ላይ የተመሠረተ ነው?
የይሖዋ ምሥክሮች የሚያገኟቸው ሥልጠናዎች ሁሉ በዋነኝነት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ መሪነት እንደተጻፈና በሁሉም የክርስቲያናዊ ሕይወታችን ዘርፎች የሚጠቅሙን የላቁ መመሪያዎችን እንደያዘ እናምናለን።—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17
የይሖዋ ምሥክሮች ለሚያገኙት ሥልጠና እንዲከፍሉ ይጠበቅባቸዋል?
አይጠበቅባቸውም። ሥልጠናው የሚሰጠው በነፃ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴዎች የሚደገፉት በፈቃደኝነት በሚደረጉ መዋጮዎች ነው።—2 ቆሮንቶስ 9:7
a መጽሐፍ ቅዱስና መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት እንዲረዱ የምናዘጋጃቸው ጽሑፎችና ቪዲዮዎች jw.org በተባለው ድረ ገጻችን ላይ ይገኛሉ።
b አቅኚ የሚባለው የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለሰዎች በመስበኩ ሥራ በየወሩ የተወሰነ ሰዓት ለማሳለፍ ፈቃደኛ የሆነና ጥሩ አርዓያ ተደርጎ የሚታይ የተጠመቀ የይሖዋ ምሥክር (ወንድ ወይም ሴት) ነው።
c የጉባኤ ሽማግሌዎች፣ በሳል ክርስቲያን ወንዶች ሲሆኑ ቅዱሳን መጻሕፍትን ያስተምራሉ፤ እንዲሁም ለይሖዋ ሕዝብ ማበረታቻ በመስጠት እረኝነት ያደርጋሉ።ለሚያከናውኑት ሥራ አይከፈላቸውም።
d የወረዳ የበላይ ተመልካች የሚባለው በተመደበበት ወረዳ ውስጥ የሚገኙ ጉባኤዎችን የሚጎበኝ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ነው። ይህ ወንድም በሳምንት አንድ ጉባኤ የሚጎበኝ ሲሆን በጉብኝቱ ወቅት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ንግግሮችን በማቅረብና ከጉባኤው ጋር በስብከቱ ሥራ በመካፈል መንፈሳዊ ወንድሞቹንና እህቶቹን ያበረታታል።
e የጉባኤ አገልጋዮች ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን የሚጠቅሙ የተለያዩ አገልግሎቶችን ያከናውናሉ። ይህም የጉባኤ ሽማግሌዎች ለማስተማሩና ለእረኝነቱ ሥራ የበለጠ ጊዜ እንዲያገኙ ይረዳቸዋል።
f ቤቴል የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮዎች የሚጠሩበት ስም ነው። በዚያ የሚያገለግሉት የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች በቅርንጫፍ ቢሮው ክልል ውስጥ የሚከናወነውን የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ ይደግፋሉ።
g ቅርንጫፍ ኮሚቴ የሚባለው ሦስት ወይም ከዚያ የሚበልጡ መንፈሳዊ ብቃት ያላቸው ወንድሞችን የያዘ ቡድን ነው።