መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል
“የምኖረው ጎዳና ላይ ነበር”
የትውልድ ዘመን፦ 1955
የትውልድ አገር፦ ስፔን
የኋላ ታሪክ፦ የዕፅና የአልኮል ሱሰኛ እንዲሁም ዓመፀኛ የነበረ
የቀድሞ ሕይወቴ
አንዳንድ ሰዎች ከደረሱባቸው ችግሮች ለመማር ረጅም ጊዜ ይወስድባቸዋል። እኔም እንደዚያ ነበርኩ። ተወልጄ ያደግሁት የስፔን ሁለተኛ ትልቅ ከተማ በሆነችው በባርሴሎና ነው። ቤተሰቦቼ የሚኖሩት በባሕር ዳርቻ በሚገኝ ሶሞሮስትሮ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ነበር። ሶሞሮስትሮ በወንጀልና በዕፅ ዝውውር የታወቀ ቦታ ነበር።
ወላጆቼ ዘጠኝ ልጆች የነበሯቸው ሲሆን እኔ የመጀመሪያ ልጅ ነኝ። በጣም ድሆች ስለነበርን አባቴ በአካባቢው በሚገኝ የቴኒስ መጫወቻ ቦታ ላይ ኳስ አቀባይ ሆኜ እንድሠራ አደረገኝ። የአሥር ዓመት ልጅ የነበርኩ ቢሆንም በየቀኑ ለአሥር ሰዓት ያህል እሠራ ነበር። በዚህም የተነሳ እንደ እኩዮቼ ትምህርት ቤት ገብቼ መማር አልቻልኩም። አሥራ አራት ዓመት ሲሆነኝ በአንድ የብረታ ብረት ሱቅ ውስጥ ማሽን ላይ መሥራት ጀመርኩ።
በወቅቱ ስፔን ውስጥ ወታደራዊ አገልግሎት መስጠት ግዳጅ ነበር፤ እኔም በ1975 ይህን አገልግሎት እንድሰጥ ተጠራሁ። በሕይወቴ አንድ ዓይነት ጀብዱ መሥራት እፈልግ ስለነበር በሜሊላ የሚገኘውን የስፔን የውጭ አገር ክፍለ ጦር በፈቃደኝነት ተቀላቀልኩ፤ ሜሊላ በሰሜን አፍሪካ የምትገኝ የስፔን ይዞታ ናት። እዚያ በነበርኩበት ወቅት በዕፅና በአልኮል ሱስ ውስጥ ተዘፈቅኩ።
ከክፍለ ጦሩ ስወጣ ወደ ባርሴሎና ተመልሼ አንድ የወሮበሎች ቡድን አቋቋምኩ። ያገኘነውን ነገር ሁሉ እንሰርቅ ነበር። ከዚያም የዕፅ ሱሳችንን ለማርካት የሚያስችል ገንዘብ ለማግኘት የሰረቅናቸውን ነገሮች እንሸጥ ነበር። ኤል ኤስ ዲ እና አምፊታሚን የሚባሉትን ዕፆች መውሰድ የጀመርኩ ከመሆኑም ሌላ ከልክ በላይ አልኮል እጠጣ፣ ቁማር እጫወት እንዲሁም የፆታ ብልግና እፈጽም ነበር። እንዲህ ያለውን ጎጂ አኗኗር መከተሌ ይበልጥ ዓመፀኛ እንድሆን አደረገኝ። ምንጊዜም ጩቤ፣ ፋስ ወይም ቆንጨራ ይዤ እንቀሳቀስ የነበረ ሲሆን አስፈላጊ መስሎ ከታየኝ በእነዚህ መሣሪያዎች ከመጠቀም ፈጽሞ ወደ ኋላ አልልም ነበር።
በአንድ ወቅት ከወሮበሎች ቡድኔ አባላት ጋር ሆነን መኪና ሰረቅን፤ በዚህም የተነሳ ፖሊሶች እያሳደዱን ነበር። ሁኔታው ልክ ፊልሞች ላይ የሚታየውን ዓይነት ይመስል ነበር። የሰረቅነውን መኪና 30 ኪሎ ሜትር ያህል ከነዳን በኋላ ፖሊሶቹ ይተኩሱብን ጀመር። በመጨረሻም ሹፌሩ መኪናውን አጋጨው፤ ከዚያም ሁላችንም ሮጠን ከአካባቢው ተሰወርን። አባቴ የሆነውን ነገር ሲሰማ ከቤት አባረረኝ።
ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የምኖረው ጎዳና ላይ ነበር። የምተኛውም በቤቶች ደጃፍ፣ በጭነት መኪናዎች ውስጥ፣ በመናፈሻ ቦታዎች ባሉ ወንበሮች ላይና በመቃብር ቦታዎች ነበር። በዋሻ ውስጥ የኖርኩበት ጊዜም አለ። ሕይወቴ ምንም ዓላማ ስላልነበረው ብኖርም ብሞትም ምንም ልዩነት እንደሌለው ይሰማኝ ነበር። በዕፅ ግፊት የእጆቼን አንጓዎችና ክንዴን ለመቁረጥ ሞክሬ እንደነበር አስታውሳለሁ። ጠባሳዎቹ አሁንም ድረስ አልጠፉም።
መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?
ሃያ ስምንት ዓመት ሲሆነኝ እናቴ ወዳለሁበት መጥታ ወደ ቤት እንድመለስ ጠየቀችኝ። እኔም ወደ ቤት ለመመለስ ተስማማሁ፤ እንዲሁም ሕይወቴን እንደማስተካክል ቃል ገባሁላት፤ ይሁን እንጂ ቃሌን ለመፈጸም ረዘም ያለ ጊዜ ወስዶብኛል።
አንድ ቀን ከሰዓት በኋላ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ቤታችንን አንኳኩ። እያዳመጥኳቸው ሳለ አባቴ ቤት ውስጥ ሆኖ በሩን ዘግቼባቸው እንድመለስ በጩኸት ይናገር ነበር። ድሮውኑም ቢሆን ትእዛዝ መቀበል ስለማልወድ አባቴን ችላ ብዬ እነሱን ማዳመጤን ቀጠልኩ። እነሱም ሦስት ትናንሽ መጻሕፍት ሰጡኝ፤ እኔም በደስታ ተቀበልኳቸው። ከዚያም የስብሰባ ቦታቸው የት እንደሆነ ጠየቅኋቸው፤ ከጥቂት ቀናት በኋላ ወደ ስብሰባ አዳራሹ ሄድኩ።
በመጀመሪያ ያስተዋልኩት፣ ሁሉም ሰው ንጹሕና ሥርዓታማ አለባበስ ያለው መሆኑን ነው። እኔ ደግሞ ረጅም ፀጉርና የተንጨባረረ ጺም የነበረኝ ሲሆን የተዝረከረከ ልብስ ለብሼ ነበር። ሁኔታዬ ለቦታው እንደማይመጥን ስለተሰማኝ ከአዳራሹ ውጭ ቆየሁ። የሚገርመው ግን፣ አዳራሹ ውስጥ ሁዋን የሚባል የቀድሞ ጓደኛዬ ሙሉ ልብስ ለብሶ አየሁ፤ ሁዋን ቀደም ሲል የወሮበሎች ቡድን አባል ነበር። በኋላ እንደተረዳሁት ሁዋን የይሖዋ ምሥክር ከሆነ አንድ ዓመት ሆኖት ነበር። እሱን ሳይ ወደ ውስጥ ገብቼ ስብሰባውን ለመከታተል ድፍረት አገኘሁ። ሕይወቴ የተለወጠው ከዚያ ጀምሮ ነበር።
መጽሐፍ ቅዱስን እንዳጠና የቀረበልኝን ግብዣ ተቀበልኩ፤ እንዲሁም የአምላክን ሞገስ ማግኘት ከፈለግኩ የጠበኝነት ባሕሪዬንና ሥነ ምግባር የጎደለው አኗኗሬን መተው እንደሚያስፈልገኝ ወዲያውኑ ተገነዘብኩ። እነዚያን ለውጦች ማድረግ ቀላል አልነበረም። ሆኖም ይሖዋ አምላክን ማስደሰት እንድችል ‘አእምሮዬን በማደስ መለወጥ’ እንደሚያስፈልገኝ ተረዳሁ። (ሮም 12:2) አምላክ ያሳየኝ ምሕረት ልቤን በጥልቅ ነካው። ብዙ መጥፎ ነገሮችን የፈጸምኩ ቢሆንም ሕይወቴን ሙሉ ለሙሉ ለመለወጥ የሚያስችል አጋጣሚ እንደሰጠኝ ተሰማኝ። ስለ ይሖዋ አምላክ የተማርኩት ነገር ልቤ ውስጥ ዘልቆ ገባ። በመጨረሻም፣ ስለ እኔ የሚያስብ ፈጣሪ እንዳለ በሚገባ ማስተዋል ቻልኩ።—1 ጴጥሮስ 5:6, 7
ይህም ለውጥ ለማድረግ አነሳስቶኛል። ለምሳሌ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ ላይ ስለ ትንባሆ ስማር ‘ይሖዋ በሁሉም ነገር ንጹሕና ያልረከስኩ እንድሆን የሚፈልግ ከሆነ ሲጋራ ማጨሴን ማቆም አለብኝ!’ ብዬ አሰብኩ። (2 ቆሮንቶስ 7:1) ከዚያም ሲጋራዎቹን ወደ ቆሻሻ ማጠራቀሚያው ጣልኳቸው!
በተጨማሪም ዕፆችን መውሰድና መሸጥ ማቆም ነበረብኝ። እርግጥ ይህን ለማድረግ ረዘም ያለ ጊዜና ከፍተኛ ጥረት ጠይቆብኛል። ይህን ግቤን ማሳካት ከፈለግኩ ከቀድሞ ጓደኞቼ ጋር ያለኝን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ማቋረጥ እንደሚያስፈልገኝ ተረድቼ ነበር። የእነሱ ተጽዕኖ መንፈሳዊ እድገት እንዳላደርግ እንቅፋት ሆኖብኝ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ይበልጥ በአምላክ መታመንና በጉባኤ ውስጥ ያገኘኋቸው አዳዲስ ጓደኞቼ የሚያደርጉልኝን እርዳታ መቀበል ጀመርኩ። እነዚህ ወዳጆቼ በሕይወቴ አግኝቼ የማላውቀውን ዓይነት ፍቅር ያሳዩኝ ከመሆኑም በላይ በግለሰብ ደረጃ ልዩ ትኩረት ሰጥተውኛል። ከተወሰኑ ወራት በኋላ ዕፅ መውሰዴን ሙሉ በሙሉ ማቆምና የአምላክን ሞገስ የሚያስገኝልኝን “አዲሱን ስብዕና መልበስ” ቻልኩ። (ኤፌሶን 4:24) ነሐሴ 1985 ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ።
ያገኘሁት ጥቅም
መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን ለውጦታል። አካላዊ ጤንነቴን ከሚጎዳውና ክብሬን እንዳጣ ከሚያደርገኝ ጎጂ አኗኗር ነፃ አውጥቶኛል። እንዲያውም ከቀድሞ ጓደኞቼ መካከል ከ30 በላይ የሚሆኑት በኤድስ አሊያም በዕፅ ምክንያት በሚከሰቱ ሌሎች ሕመሞች ሳቢያ በአጭሩ ተቀጭተዋል። እኔ ግን የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በተግባር በማዋሌ በእነሱ ላይ ከደረሰው አሳዛኝ መዘዝ መዳን ችያለሁ፤ ለዚህም በጣም አመስጋኝ ነኝ።
ዓመፀኛ ወጣት ሳለሁ ጩቤና ፋስ ይዤ እንቀሳቀስ ነበር፤ አሁን እሱ ያለፈ ታሪክ ሆኗል። በእነዚያ መሣሪያዎች ምትክ መጽሐፍ ቅዱስ የምይዝበትና መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅሜ ሰዎችን የምረዳበት ጊዜ ይመጣል ብዬ አላሰብኩም ነበር። በአሁኑ ወቅት እኔና ባለቤቴ ሙሉ ጊዜያችንን የምናሳልፈው ይሖዋን በማገልገል ነው።
ወላጆቼ የይሖዋ ምሥክሮች አልሆኑም፤ ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቴ ያስገኘልኝን ጥቅም ማየታቸው አስደንቋቸዋል። እንዲያውም አባቴ በሥራ ባልደረቦቹ ፊት የይሖዋ ምሥክሮችን ደግፎ እስከመከራከር ደርሷል። አዲሱ እምነቴ፣ ሕይወቴ በአስደናቂ ሁኔታ እንዲለወጥ እንዳደረገ በግልጽ መረዳት ችሏል። እናቴም፣ አስቀድሜ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምሬ ቢሆን ኖሮ በጣም የተሻለ ይሆን እንደነበር በተደጋጋሚ ትናገራለች። እኔም በዚህ አባባሏ ሙሉ በሙሉ እስማማለሁ!
ዕፅ በመውሰድና በሌሎች መጥፎ ድርጊቶች በመካፈል ደስታ ለማግኘት መጣር ምን ያህል ሞኝነት እንደሆነ ከሕይወት ተሞክሮዬ ተምሬያለሁ። በአሁኑ ጊዜ፣ ሕይወቴን ያተረፉልኝን በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙ ትምህርቶች ለሌሎች በማስተማር እውነተኛ ደስታ ማግኘት ችያለሁ።